የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አክሲዮን ማህበር ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ3.4 ሚሊዮን ቶን በላይ የወጪና ገቢ ዕቃዎችን ማጓጓዙን አስታውቋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አ.ማ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሰርካ እንደገለጹት፤ በመጀመሪያ ዓመት 8 መቶ ሺህ፣ በሁለተኛ ዓመት 1.2 ሚሊዮን፣ በሶስተኛ ዓመት 1.4 ሚሊዮን ቶን እቃ ማጓጓዝ ተችሏል።
ይህም አክሲዮን ማህበሩ በአጠቃላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ3.4 ሚሊዮን ቶን በላይ ዕቃ አጓጉዟል ነው የተባለው።
በዚህም አገልግሎት አሰጣጡ በየአመቱ ከ25 እስከ 30 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና የሶስት ዓመታት ጉዞውም ጤነኛና ስኬታማ እንደነበር አስታውቀዋል።
የልማት መሳሪያዎች፣ የንግድ ሸቀጦች፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅትና የግሉ ዘርፍ በኮንቴነር የሚያስመጧቸውን ሸቀጦች በማጓጓዝም ስኬታማ እንደነበር አመልክተዋል።
የባቡር አገልግሎት ፋይዳ እየሰፋ በመምጣቱ የወጪና ገቢ ንግዳችንን በማሳለጥ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ያሉት ኢንጂነር ጥላሁን፤ ተደራሽነቱን ለማስፋት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከቻይና ወደ ሀገራችን እያመጣን ነው ብለዋል ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
ቅጽ 3 ቁጥር 137 ሠኔ 12 2013


