የጉራማይሌ ነገር፦ “Doing Business” እንዴት ይዟችኋል?

0
828

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ሌሎችም ባለሥልጣናት እንዲሁም ዜጎች ቋንቋ አጠቃቀም ጉራማይሌ የበዛበት መሆኑን ያስተዋሉ ቤተልሔም ነጋሽ ጉዳዩ በቀላሉ ታይቶ ሊታለፍ የማይገባው የአገር ጉዳይ መሆኑን በዚህ መጣጥፋቸው ያሳስባሉ።

 

 

“የDoing Business ማሻሻያ ትግበራ” በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካይነት ለከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የወደፊቱን አካሔድ አቅጣጫ ለማሳየት የቀረበ ገለጻ ርዕስ ሲሆን፥ በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ትዊተር ገጽ ላይ አጠር ካለ ገለጻ ጋር ከነፎቶው ሲቀርብ “ምነው?” ያላለ የትዊተር ገጹ ተከታይ ጥቂት ነበር። ግማሹ በዙሪያቸው ያሉ ባለሙያዎችን ሲተች፣ ሌላው በደፈናው እንዴት ያለ መዝረክረክ ነው ብሏል። የአገሪቱ ኦፊሴላዊ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ሆኖ ሳለ የሚተካ ቃል የጠፋ ይመስል በአማርኛ በተዘጋጀ ገለጻ ላይ እንግሊዝኛ ቃል ድንቅር ብሎ ማየት ይከብዳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን በሚያነቃቁ ንግግሮቻቸው የምናደንቃቸውን ያህል፣ በውጪ አገራት ጉዟቸው በአማርኛ ቋንቋ ንግግር በማድረግ ተክብረው አስከበሩን ብለን ያመሰገናቸውን ያህል፣ በአማርኛ ቋንቋ ሲናገሩ የእንግሊዝኛ ቃላትን አብዝተው መጠቀማቸውን ግን በተለይ ካላቸው ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት አንፃር ወትሮም ችግር ላይ ያለውን የአማርኛ ቋንቋ ጉዳይ ወደባሰ ሁኔታ እንዳያስኬደው ያሰጋል።
እንደሚታወቀው በመደበኛው ብዙኀን መገናኛዎች የሚሳተፉ ጋዜጠኞቻችን ሳይቀር በአማርኛ በአግባቡ ለማስረዳት የፈለጉትን ነገር ማስረዳት ሲያቅታቸው ማየት አዲስ አይደለም። ከአርቲስት እስከ አትሌትና ባለሥልጣን እንግሊዝኛ በረባ ባልረባው መደንቀር፣ አገባቡና ትክክለኛ ትርጉሙን የማያውቁትን ቃል እዚህም እዚያም ጣል ማድረግ የአዋቂነት ምልክት ከመሰለ ቆየ። የንግድ ተቋም ሥም ሥያሜዎቻችን ሳይቀሩ ምንም ተዛማጅ የሌለው የእንግሊዝኛ ቃል ለስያሜ መጠቀም አልያም በትንንሽ ቦታዎች ሳይቀር በአማርኛ መጻፍ በቂ ሆኖ ሳለ የተሳሳተ እንግሊዝኛ መደንቀር ከተያያዙ ቆዩ።
ለምሳሌ ይህን ጽሑፍ ባዘጋጀሁበት ዕለት፣ ከሰፈሬ ጠዋት ወደ ሥራ በምመላለስበት መንገድ አዲስ የተተከለ የትራፊክ መብራት ላይ ስቆም ያስተዋልኩት አዲስ ሱቅ ባማረ ደማቅ ቀለም “እገሌ ጫማ” ብሎ በአማርኛ ተጽፎበት፥ ከሥሩ ከዚያ በማያንስ መጠን በእንግሊዝኛ “….Shoce” ተብሎ ተጽፎ ሳይ ደንግጬ ነበር። ቋንቋ እንደተማረ እና በአርትዖት ሥራ ላይ ልምድ እንዳለው ሰው የእንግሊዝኛውን ፊደል ግድፈት በቅፅበት አይቼ የተሰማኝ በየሰፈሩ ካሉ አነስተኛ ምግብ ቤቶች ሳይቀር በተገደፈ እንግሊዝኛ የአበሻ ምግብን ለማስቀመጥ የሚጣጣሩ ሜኑዎች ሲያጋጥሙኝ የሚሰማኝ ዓይነት ነው። ቀልድ ነው ወይስ በእንግሊዝኛ ብቻ የሚግባባ ደንበኛ ከዕለታት ባንዱ ቀን ይመጣል ብለው በቁም ነገር አስበው ነው? እዚህ በአዲስ አበባ አንድ ጥግ አነስተኛዋ የጫማ ሱቅ ሥሟን በእንግሊዝኛም መጻፍ አለባት ብሎ ያሰበ ባለቤት ምናልባትም ዘመነኛ ሊያደርጋት አልያም ራሱን ከአዋቂ ሊያሰልፍባትም ብሎ ያኖራት ይሆናል።
እሱን እያሰብኩ 50 ሜትር ሳላሽከረክር “ፓርቴከርስ ዓለም ዐቀፍ ቤተ ክርስቲያን” የሚል ትልቅ ታፔላ ከመልከ መልካም የቤተክርስቲያኑ “ባለቤት” ጋር ተለጥፏል። ተገርሜ ሳይወጣልኝ ሄደት እንዳልኩ “ማይ ባክ ቦሎ” የምትል በአነስተኛ ጨርቅ ላይ የተጻፈች ማስታወቂያ ገጠመችኝ። ጉዞዬን በቀጠልኩበት ቅኝቴ ቢቀጥል ብዙ አላግባብ የተደነቀሩ ቃላት እንደማገኝ ጥርጥር የለውም።
የቋንቋው መበረዝ የሚያመለክተውን በተለይ ከማንነትና ባሕልና ልማድን እንደ ማኅበረሰብ ከማስቀጠል አንጻር የሚፈጥረውን ችግር ከመዘርዘሬ በፊት አንድ ኹለት ምሳሌዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቅርብ ጊዜ ንግግሮች ላቅርብ፦
አምባሳደሮችን ሲሾሙ ከተናገሩት መካከል “…ባለፉት ጊዜያት የነበሩ አምባሳደሮች ትንሽ ይዋዥቁ ነበር። ምክንያቱም ሚናቸውን ስለማያውቁ ‘አፊሌትድ’ ለሆኑበት ሁኔታ ‘ኢንክላይን’ ያደርጉ ነበር…” ብለው ነበር።
አንድ ተሳታፊ (ምናልባትም አዲስ የተሾሙ) በበኩላቸው እዚያው ስብሰባ ላይ አስተያየት ሲሰጡ፥
“አቅም መገንባት ‘ካፓሲቲ’ የሚለው ነገር በውጪ ጉዳይ ሲነገር የኖረ ጉዳይ ነው። ጥረቶች አሉ። አሁንም ግን የ‘ማይንድሴት’ ችግር አለ፤ ‘ፕሮፌሽናሊዝም’ን መገንባት ላይ ችግር አለ።…” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፦ “…ዕውቀት አዲስ ነገር የለም ላልከው፣ ‘ኖውሌጅ ኢዝ አውት ዜር’ ዕውቀት የትም የሚገኝ ነገር ስለሆነ… አንተ’ጋ በመምጣት የትም የማይገኝ ነገር እየፈጠርክ ከሔድክ አትጠራጠር እዛ ገብቶ ‘ሰርቲፋይድ’ መሆን ‘ኢምፖርታንት’ እንደሆነ ስለሚያምን ይማራል…” ብለዋል።
እነኝህን ያገኘሁት 4 ደቂቃ በሚጠጋ የዩቱብ ቪዲዮ ላይ ሲሆን ትኩረት ሰጥተን ብንሰማ ሌሎችንም እንደምናወጣ ግልጽ ነው። ከቦታ፣ ከጊዜ አንጻር ባይቻልም አንባቢን የምጋብዘው ንግግሮቹን ሰምቶ እንዲፈርድ ነው።
አንባቢ እንግሊዝኛ ቢቀላቀል ምን ችግር አለ? ይሄን ያህል ነቅሶ ማውጣትና መተቸት ለምን ያስፈልጋል? ብሎ ሊያስብ ይችላል። የቋንቋ ሊቃውንትና አጥኚዎች ግን በዚህ አይስማሙም።
ምክንያቱም ቋንቋ የአንድ ማኅበረሰብ ባሕልና የቡድን ማንነት ከሚገለጽባቸው ተጨባጭ ዋነኛ ምልክቶች አንዱ ነው። የአዕምሮ ሀብት ሕያው መገለጫ፣ የባሕል ልዩ መረዳት ማሳያ፣ ያለፈውና የወደፊቱን የሚያገናኝ ድልድይም ጭምር ነው። ከዚህም ሌላ የአንድን አገር ታሪኩንና የያዘውን ምሥጢር የምናውቅበትና ሥም የምንሰጥበት በዚህም የወደፊት ሕልውናው የሚወሰንበት ቁልፍ ነው።
እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ቡድን ወይንም ብሔር የየራሱ የሆኑ እሴቶች፣ እምነቶች ልማድና የአኗኗር ዘይቤዎች አሉት። ቋንቋ ባሕል የሚገለጽበት ተፈጥሯዊ መንገድ ነው። እሴቶችን፣ ልማዶችንና እምነቶችን እንደማስተላለፊያ አንድ መንገድ ቋንቋ አንድነትንና የቡድን ማንነትን መፍጠር ትልቅ ማኅበራዊ ሚና እንዳለው ይነገራል። ከዚህም በላይ ቋንቋ ልማዶችና የጋራ እሴቶችን ለማሳየትና ለማቆየት ወይንም ለማስቀጠል የሚያስችል አንድ ዘዴ ነው።
ባሕል ያለ ቋንቋ ምንም ነው። ለዚህም ነው በአገራችን ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የሚደረገው። ሰዎች የሚያስቡት በተወለዱበት ቋንቋ ነው። “የአፍ መፍቻ ወይም ተፈጥሯዊ ቋንቋ የአንድ ማኅበረሰብ ልምድ፣ ዕውቀትና እምነት የሚጠራቀምበት ማኅደር ነው” የሚባለውም ለዚህ ነው። ቋንቋ የሚጠቀምበትን ማኅበረሰብ አዕምሯዊ ሀብት የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳይ መሣሪያም ነው።
ኹለተኛ ቋንቋ መማር የሚከብደው፣ ምን ያህል የተካንን ብንሆን የአፍ መፍቻ ቋንቋችን ያህል በቀላሉ ልናዝበት የማንችለው። አዘንበታል ብንል እንኳን መናገር ጀምረን ጥቂት እስክንቆይ አቀላጥፈን ለማውራት የሚቸግረን። ሰዎች ራሳቸውን በሚገባ መግለጽ እንዲችሉ የቋንቋቸው በቂ ችሎታ ሊኖራቸው የግድ ይላል።
ኔልሰን ማንዴላ “አንድን ሰው በሚረዳው ቋንቋ ብታዋሩት የምትነግሩት ነገር ወደ ጭንቅላቱ ይሔዳል፤ በራሱ ቋንቋ ግን ብታናግሩት ነገራችሁ ወደ ልቡ ይገባል” ያሉት ለዚህ ነው።
ሌላው የቋንቋ ሊቃውንት ትንታኔ እንደሚያመለክተው ቋንቋ ከማንነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ነው። በራሱ ማንነትን የሚወስን ባይሆንም ማንነታችንን ወይም ነን ብለን የምናስበውን ማንነት እንድንገልጽ ይረዳናል። ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ መሆን የሚፈልጉትን ቡድን ቋንቋ ዘዬ በመጠቀም ከዚያ ቡድን ጋር ለመመደብ ይጥራሉ። ምናልባት የእኛ ማኅበረሰብ አባላት እንግሊዝኛ ቋንቋ በመቀላቀል አዋቂ ወይም “ምሁር” ለመምሰል የመጣራቸው ነገር በዚህ ትርጉም ወይም ትንታኔ መልስ ሊያገኝ ይችል ይሆናል።
ቋንቋ የሕልውናችን ዋነኛ አካል ነው። የባሕል ሚኒስቴርም ይሁን የከፍተኛ ተቋማት የቋንቋ ጥናት ክፍሎች በአገር በቀል ቋንቋዎች ላይ ጥናትና ትንተና ማድረግ፣ የቴክኖሎጂም ይሁን አዲስ ፅንሰ ሐሳብ ሲኖር ተተኪ ቃላትና አቻ ትርጉሞችን በማፈላለግ ማስረፅ ቋንቋዎቹ ደረጃ እንዲኖራቸውና ወጥነት ባለው መልኩ እንዲያድጉ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። የብዙኀን መገናኛ ተቋማትም የቋንቋ ጉዳይ እንደሚታየውና እንደሚመስለው ቀላል ሳይሆን የአገር፣ የሕዝቦች ማንነት፣ ራስን የማወቅና የመግለጽ ጉዳይ መሆኑን አውቀው በጋዜጠኞቻቸው የቋንቋ አጠቃቀም ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።
ምሁራንና ጸሐፍትም ቋንቋ ማወቅ አዋቂነት እንዳልሆነ፣ ይልቁንም የራስን ማወቅና ማክበር ከሁሉ መቅደም እንዳለበት አውቀው አርዓያ ሊሆኑ ይገባል። ካልሆነ እየመጣ እንዳለው የማኅበራዊ መገናኛዎች ወጣት ትውልድ አማርኛም እንግሊዝኛም የማያውቅ ትውልድ በዝቶ የቋንቋ መደበላለቅ እንዳይመጣ ያሰጋል። አሁን ካልተሠራ በኋላ ዋጋውም የሚጠይቀው ጥረትም ብዙ ሊሆን ይችላል።
ኢክታቪዮ ፓዝ በተባለ ሊቅ አባባል ጽሑፌን ስደመድም “በሚጠፋው እያንዳንዱ ቋንቋ የአንድ ሰው አምሳል ከምድረ ገጽ ይጠፋል” ይላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here