“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
በቀደም የቴሌቭዥን መቆጣጠሪያ ‘ሪሞት’ ጥሎኝ አንድ የአውሮፓ ፊልም እያየሁ ነበር። የፊልሙ ርዕስ ‹The Other Women› ነው። ሦስት ሴቶች በዋናነት የሚተውኑበት ይህ ፊልም፤ አንዷ ገፀባህሪ የምትወደውና ለትዳር ያሰበችው ሰው ባለትዳር መሆኑን ስታውቅ ይጀምራል።
አውቃ ግን በንዴትና በእንባ አላለፈችም። ከርሷ አልፎ ሌላ ሴት መኖሯንም እነዚህ የተከዱ ሁለት ሴቶች ያውቃሉ። ሕጋዊ ሚስት «ባሌን ወሰዳችሁ» ብላ ጥላቻ አላሳየችም፤ በመጀመሪያዋ የቀረበውን አንድ ሐሳብ ተቀበለች። በሐሳቡ ሁሉም ተስማሙ፤ የሚዋሻቸው ሰው መተዋወቃቸውን ሳያውቅ ተባብረው ሊቀጡት። በጠቅላላው ፊልሙ የእነዚህን ሦስት ሴቶች ትብብር ያሳያል።
በእውኑ ዓለም ክህደቶችን እንጂ እንዲህ ያለ ትብብርን አንመለከትም። ‹‹ለምን?›› አይታወቅም። በተግባር በሴቶች መካከል እንደዛ ያለ ትብብር ቢኖር በእርግጠኝነት የብዙ ሰዎች ሕይወት ይቀየር ነበር። በትዳር መካከል የተገኙ የብዙ ልጆች ሕይወትም እንደዛው።
ይሄ የሴቶች መተባበር በየትኛው የማኅበረሰብ ክፍል እንደሆነ ባላውቅም፤ እንዳይኖር ተደርጓል። ሴቶች በጋራ ተስማምተው ምንም መሥራት እንደማይችሉ ነው የምናስበው። ወይም እርስ በእርስ መልካም ነገር እንደማይለዋወጡና እንደሚጨካከኑ ነው የምናውቅ የሚመስለን። የምንለውም ይህንኑ ነው፤ «ሴት ለወንድ ትራራለች እንጂ ለሴት ክፉ ናት።»
በየተቋማቱ፣ በየመንገዱ፣ በየመደብሩ፤ ሴቶች ለሴቶች ጥሩ መስተንግዶ አያሳዩም ይባላል። ምንአልባት ከውበት ቁሳቁስ መሸጫ መደብሮች ውጪ ማለት ነው። «ሴት ስለሆነች እሺ አትለኝም፤ አንተ ገብተህ አናግርልኝ» ብለው ወንድሞቻቸውን ወይም ባሎቻቸውን የሚልኩ ሰዎች ገጥመውኛል። የሰው ልጅ ማግኔት አይደለም፤ በተፈጥሮ የሚማሰሉ ነገሮች እንዲገፋፉ ተደርገው አልተፈጠሩም።
«ሴት ሲበዛ ጎመን ጠነዛ» ሲሉን አብረን ስንል፤ «ይሄ የሴት ወጉ አይደለም» ሲባል፤ በዚህ መሠረት እርስ በእርስ ስንገማገም፤ አሉን የምንላቸው የሴቶች ኅብረት ተቋማት እንኳ በቅጡ እንዳይሠሩ ሆነዋል። በሥራ አጋጣሚ ያገኘኋቸውን ሴቶች አስታውሳለሁ፤ ከአረብ አገር የተመለሱና ተደራጅተው እንዲሠሩ ዕድል የተመቻቸላቸው ናቸው። በሚገርም ሁኔታ ግን ከሦስት ወር በላይ በሥራ አልቆዩም፤ ሥራቸው ተዳከመ። የተደራጁትን ሴቶች በዋናነት የሚመሩትን ሴት አናግሬአቸው ነበር፤ «በፊት ያስተባብረን የነበረው ወንድ ነው፤ እርሱ በሥራ ምክንያት ሲለቅ ሴቶቹ አስቸገሩ» አሉኝ።
አለመግባባት ይኖራል፤ እሱ ችግር አይደለም። ፤የለም እንግባባለንኮ!!» በማለት ሊጠፋ አይችልም። መፍትሄ ግን አለው። ይህም ከአመለካከት ለውጥ የሚጀምር ነው። ሴቷ ለራሷ ያላትን አመለካከት ስታቃና፤ ለሌሎች እህቶቿ ያላት ዕይታም ይስተካከላል። የተዋሸች ሴት፣ የተከፋች ሴት፣ የተጎዳች ሴት፣ የተካደች ሴት፣ የተቸገረች ሴት…. እርሷን መሳይዋን ካልተረዳቻት እንግዲህ ማን ሊመጣ? ለውጥን ሁሌም ከወንዶች፣ ከተቋማት፣ ከማኅበራት፣ ከሕግ ወዘተ ይሁንታ መጠበቅ የለብንም፤ ከራስ መጀመር ያስፈልጋል።
መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com
ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011