የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 98ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ከውሳኔዎቹ መካከል የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለማቋቋም የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ አንዱ ሲሆን፣ የመለስ አመራር አካዳሚ የሚለውን በመቀየር የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ሊቋቋም ነው ተብሏል፡፡ በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ረቂቅ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ሲሆን፣ ይህ ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የክፍያ ስነ ምህዳሩን በማዘመን ውስን የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ያለውና የፋይናንስ አካታችነቱ የጎለበተ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ፍኖተ ካርታ በመሆን ያገለግላል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ዲጂታል አሰራር በማሸጋገር የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተሳትፎ ለማሳደግ ከሚካሄዱ አገር በቀል የሪፎርም ተግባራት ጋር በቅንጅት የሚፈጸመው ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ፣ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን አካታች የኢኮኖሚ እድገት፣ የላቀ ብልጽግና እንዲሁም የተሻለ የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ግብ ለማሳካት የሚያግዝ በብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ረቂቅ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ስትራቴጂ ሰነዱ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶች በማከል በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ ምክር ቤቱ በመጨረሻ የተመለከተው የኢትዮጵያ መንግስት ከፈረንሳይ እና ከጣልያን መንግሥታት ጋር ያደረጋቸውን የመከላከያ ትብብር የኹለትዮሽ ስምምነቶች ነው፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013


