ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራና ትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ሰላማዊ ፉክክር የሚስተናገድበትን እግር ኳስ ሳይቀር እስከ መረበሽ መድረሱ ይታወሳል። በአማራ ክልል ያለ የእግር ኳስ ቡድን ወደ ትግራይ አቅንቶ ለመጫወት እንዲሁም በተቃራኒው የትግራዩ ወደ አማራ ለመምጣት እስከ መፍራት ተደርሶ መደበኛ መርሐ ግብሮች ሲታጠፉ ከርመዋል። ከሰሞኑ የኹለቱ ክልል እግር ኳስ ቡድኖች በክልላቸው ተገናኝተው መጫወታቸው እንደብርቅ ሲቆጠርም ተስተውሏል። እንዲያውም አማራ ክልል ትግራይ ሔደው ለተጫወቱ ክለቦቹ የምስጋና ምስክር ወረቀት ልኳል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸውና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ማክሰኞ፣ ጥር 7 ምሽት 2፡00 በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ችግራቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ስለመስማማታቸውና የኹለቱ ክልል ሕዝብም ፀብ እንደሌለው መናገራቸው ይታወሳል።
የአማራ ሕዝብ ከትግራይ አቻው ጋር ሰላምን እንደሚፈልግ የተናገሩት ገዱ የሺሕ ዘመናት የጋራ ዕሴትን የገነቡ፣ ረጅምና አቆራኝ የጋራ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ስለመሆናቸው አክለዋል። ደብረፂዮን በበኩላቸው የኹለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ከሚባለውም በላይ መሆኑን በመጥቀስ በጥቂት ፖለቲከኞች ችግር ሕዝቡ ስለመበደሉ አንስተዋል።
አንዱ በአንዱ የሚኮራ ሕዝብ የነበረ ቢሆንም በጊዜ ሒደት እየተሸረሸረ መምጣቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ገዱ፥ የአማራ ሕዝብ ብዙ አጀንዳዎች እንዳሉት ግን ደግሞ ጥያቄዎቹ በሰላምና ውይይት እንዲፈቱለት እንጂ ከትግራይ ሕዝብ ጋር መታኮስና ግጭት ጀማሪ የመሆን ፍላጎት እንደሌለው መናገራቸው አይዘነጋም። በትግራይ ክልልም ቢሆን ለመጋጨት ራሱ አስተሳሰቡ እንደሌለ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ግፊቶች ቢኖሩም ከትግራይ ክልል በኩል የሚተኮስ ነገር እንደማይኖር ተናግረዋል።
ማን ከማን፣ በምንስ ተጣሉ?
ገዱ ሕዝቡ ተበድያለሁ ብሎ የሚያነሳቸው ጉዳዮች አሉ ይበሉ እንጂ ምንድን ናቸው የሚለውን አላስቀመጡም። ይሁንና አዴፓ ከዚህ ቀደም ወልቃይትና ራያ ላይ የማንነት ጥያቄ (ማንነት በሌላው ገጹ ከመሬት ባለቤትነት ጋር መያያዙን ልብ ይሏል) መኖሩን አንስቶ የትግራይ ክልል እንዲፈታ መጠየቁ ከሕወሓት ጋር የከረረ የቃላት ጦርነት ውስጥ እንዳስገባው ይታወሳል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የማኅበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ ተመስገን ተሰማ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በትግራይ ክልል የተወሰዱበት ርስቶች (የወልቃይትና ራያ) እንዲመለሱለት፣ ሕወሓት የበላይ በነበረበት የሥልጣን ዓመታት ከሌላው ሕዝብ በተለየ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ስለደረሰበት ይቅርታ እንዲጠየቅና አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ የሚሉት ይገኙበታል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ደብረፂዮን በመግለጫቸው “ይቺ መሬት ሔደች፥ እንደዚህ የሚባል አጀንዳ ለእኛ አጀንዳ አይደለም፣ አጀንዳ መሆን የለበትም” ሲሉ ተደምጠዋል። “በቦታ የምንጋጭ አይደለንም፤ እንደሚባለውም አልተጋጨንም” ማለታቸውም ይታወሳል።
ስለዚህ የሚናገሩት ተመስገን የአማራ ሕዝብ የመሬት ወይም ርስት ጥያቄ አለው፤ ስላለውም በራያና ወልቃይት ከፍተኛ ጥያቄ ተነስቶ የግጭትም መንሥኤ ሆኖ መቆየቱን ያብራራሉ።
የአረና ትግራይ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አምዶም ገብረሥላሴ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፤ እንደርሳቸው ከሆነ በኹለቱ ሕዝቦች መካከል የመሬት ጥያቄ የለም፤ ይልቁንም የፖለቲከኞች የሥልጣን ሽኩቻ የፈጠረው ችግር ነው። “የመሬትና ማንነት ጥያቄ ከሌለ እንዴት በራያና ወልቃይት የሕዝብ ተቃውሞና ጥያቄ ዛሬም ድረስ ሊኖር ቻለ?” በሚል ከአዲስ ማለዳ ለተነሳላቸው ጥያቄ አምዶም ሲመልሱ፥ አዴፓና ሕወሓት ልዩ ኃይላቸውንና ፖለቲከኞቻቸውን እየተጠቀሙ ሕዝቡን ያሸብሩታል እንጂ የሕዝቡ ጥያቄ አይደለም ይላሉ። ኹለቱ ሕዝቦች ሰላማዊ ከሆኑ በየክልሉ ያለው በርካታ ጥያቄ ክልሉን ወደሚያስተዳድሩት ፓርቲዎች ስለሚመለስና ፓርቲዎቹ ከሕዝቡ የሚነሱትን የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳዳር ጥያቄዎች የመመለስ አቅም ስለሌላቸው ሕዝቡን አቅጣጫ እያሳቱት ነው የሚል አቋምም አላቸው። በዚህም ኹለቱም ፓርቲዎች የሕዝብ ተቆርቋሪ እንደሆኑ በማስመሰል ፕሮፖጋንዳ እያሰራጩ ነው ሲሉም ይወቅሳሉ። በዚህ ደግሞ ያጡትን ቅቡልነት ለማግኘት በመፈለግ የራሳቸውን ፀብ የሕዝብ ለማስመሰል እየሠሩ ነው ብለው ነው የሚያምኑት።
የአራቱም የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች (አዴፓ፣ ሕወሓት፣ አብንና አረና) በኹለቱ ሕዝቦች መካከል ፀብ የለም በሚለው ይስማሙ እንጂ “ሥምምነት ላይ ደርሰናል፤ ታርቀናል” የሚሉት የማንን ፀብ ፈተው ነው በሚለው ጉዳይ ግን የተለያየ አቋም አላቸው።
በሰሞነኛው መግለጫው አዴፓ ፀቡ (አለመግባባቱ) በማን መሐል ነው የሚለውን በግልጽ ባያስቀምጥም፥ ከዚህ ቀደም ባወጣቸው መግለጫዎች ጠላት የሚላቸውና የጥቂት ፖለቲከኞች አሻጥር ሕዝቡን ሰላም እየነሳ እንደሚገኝ አመልክቷል። ሕወሓት ደግሞ የሚታዩ ልዩነቶች እንዳሉ በመጥቀስ መፈታት ይገባቸው የነበረ ቢሆንም በፖለቲከኞች ድክመት ሳይፈቱ ቀርተዋል ይላል። ይህም ያሳፍራል፣ ያሳዝናል ሲሉ ደብረፂዮን በመግለጫቸው አንስተዋል።
“የፖለቲከኞች ፀብ ነው” የሚለውን አልቀበልም የሚለው አብን፥ ፀቡ በአማራ ሕዝብና በሕወሓት መካከል እንደሆነ ሲገልጽ አረና በበኩሉ ፀቡ የአዴፓና ሕወሓት ነው የሚል አቋም አለው።
ፀቡ ግልጽ ሳይሆን ዕርቁ ከየት?
ታዲያ አለመግባባቱ በግልጽ ምን ላይ እንደሆነ እንኳን ሳይታወቅና መግባባት ሳይደረስበት በሰላም ለመፍታት ተሥማምተናልና ታርቀናል የሚለው መግለጫ እንዴት ይታመናል የሚለውም ትልቁ ጥያቄ ነው።
ደብረፂዮን በመግለጫቸው የፖለቲካ ልዩነቱ ሊቆይ፣ በራሱ ጊዜና ቦታ ሊፈታ እንደሚችል በመጥቀስ የወሰንም ሆነ የአስተዳዳር ጥያቄ ከሰላም በላይ እንዳልሆነ፣ ስለሆነም ቀድሞ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል፤ ለዚህ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል። ይሁንና የወሰንና አስተዳደር ጥያቄ የሚለው በራሱ ‹‹ ይቺ መሬት ሔደች የሚል አጀንዳ የለም›› ከሚለው አባባለቻው ጋር አይጣረስምወይ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡
ገዱ በበኩላቸው አዲስ አበባ ስለ ሰላም ተናግሬ ሔጄ እዚያ ሌላ ብናገር ሕዝቡ ይጠይቀኛል፤ እዚህ የምናገረውም እዚያ ሔጀ የምሠራውም ይህንኑ ነው” ማለታቸው ይታወሳል። ክልላቸው ከትግራይ አቻው ጋር ችግሮቹን በጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚፈታ ከተናገሩም በኋላ “ቃሌ ፊርማዬ ነው፤ ለሰላም እሠራለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
አምዶም ኹለቱ ሕዝቦች ተጣልተው አያውቁም፤ ያልተጣላ ደግሞ አይታረቅም በማለት አባይ ወልዱ የትግራየይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በነበሩ ወቅት የኹለቱም ክልል ልኡካን መቀሌና ጎንደር ተገናኝተው ታርቀናል፣ ተሥማምተናል ብለው እንደነበር፤ ዳሩ ግን ዕርቁ ዘላቂ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። “መጀመሪያውኑ ዕርቁ የአዴፓና ሕወሓት ነበር፤ ኹለቱም ከተሞች ላይ የተገኙት ሽማግሌዎች የፓርዎቹ ካድሬዎች ናቸው” የሚሉት አምዶም ዕርቁን ያፈረሱትም የሥልጠጣን ሽኩቻ ውስጥ የገቡት ኹለቱ ፓርቲዎች ስለመሆናቸው ያምናሉ። ስለዚህ ዕርቅና መግለጫው የተለመደ ነው በማለት ግን ደግሞ የሕዝብ አለመሆኑ ሊሠመርበት እንደሚገባ ያነሳሉ።
ተመስገን ደግሞ “ዕርቅ እንደፈፀሙ ተናግረው መግለጫ የሰጡት ኹለቱም መሪዎች በኹለቱም ሕዝቦች ትግል ላይ ተሳልቀዋል” ሲሉ ይተቻሉ። “የተጋጨነው የራያና ወልቃይት መሬት ስለሔደብን ነው” ሲሉም ያክላሉ። ችግሩ ኹለቱ የክልል መሪዎች የሚፈቱት እንዳልሆነ በመጥቀስ የመሪዎቹ ዕርቅና ሥምምነት የፌደራሉ መንግሥት በትኩረት እንዳይሠራ ማዘናጊያ ነው የሚመስለውም ይላሉ። ኹለቱ የሚፈቱት ቢሆን ኖሮ የፌደራሉ መንግሥት የዕርቅና ወሰን ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ኮሚሽኖችን አቋቁሞ ለመፍታት ሥራ መጀመር አያስፈልገውም ነበር የሚልም አቋም አላቸው። የወልቃይትና ራያ ጥያቄ ሳይፈታ መሪዎቹ ታርቀናል ማለታቸው የኢሕአዴግን አለመለወጥ የሚያሳይ ነው የሚል ሐሳብ የሚያነሱት ተመስገን፤ እውነተኛ ዕርቅ ከተፈለገ ከኹለቱም ክልሎች የተመረጡ ሽማግሌዎች ሊመክሩና ሊያስታርቁ እንደሚገባም ይገልጻሉ።
የኹለቱ መሪዎች ሥምምነት ምናለልባት በኹለቱም ወገን ባለ ስጋት ትጥቅ የማስታጠቅ ዘመቻ ታይቶ ስለነበር ይህን መሰል ነገር ሊያስቆም ይችላል እንጂ የሕዝቡን ጥያቄ አይመልሰውም ሲሉ ነው የአብን ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊው የሚያስረዱት። “ደብረፂዮን ችግሩ እንዲፈታ ይፈልጋሉ ብዬ አላምንም” የሚሉት ተመስገን “መግለጫውን ሰጥተው ከተመለሱ በኋላ እንኳን ‹እናቀምሳቸዋለን› እያሉ ሲዝቱ የሚሳይ የትግርኛ ንግግራቸውን አግኝቻለሁ” ሲሉም ያክላሉ። “ገዱም ቢሆኑ ከዚህ ቀደም ሕዝቡ ከግጭት እንዲቆጠብ መግለጫ ሰጥተው ነበር ግን አልቆመም፣ ያልቆመው ደግሞ ችግሩ ስላልተፈታ ነው” ሲሉም ይናገራሉ። መሪዎቹ የማይፈቱትን ነገር እንፈታለን እያሉ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ችግሩን እንዳይፈታ እየከለከሉት እንዳይሆን አብን ስጋት እንዳለው ተመስገን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ጉዳዩ (የርስት ይመለስ ጥያቄው) በድርድር ሳይሆን በሕግ ሊፈታ ይገባል የሚለው አብን፥ ጥያቄው ሲመለስ እና አዲሱ የዕርቅና ሰላም ኮሚሽንም በአማራው ላይ በተለየ ደርሷል የሚባለውን የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት አጣርቶ እውነት ሆኖ ካገኘው በዳዩ ወገን ሕዝቡን ይቅርታ ሲጠይቅና በሕግ መጠየቅ ያለበትም አካል ሲጠየቅ ብቻ እውነተኛ ዕርቅ እንደሚሆን ይገልጻል። አረና ግን የፀቡ ምክንያትና ዓይነት ይህ ነው ብሎ ስለማያምን በዚህ አይሥማማም።
ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011