“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ሴት የሚለው ቃል በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እይታ ዝቅ ያለ አመለካከት የሚሰጠው ጽንሰ ሃሳብ ነው። ይህን ዝቅተኛ የሆነ አመለካከት እንዲኖር ያደረገው ደግሞ ማሕበረሰቡ ብቻ ሳይሆን እኛ ሴቶችም ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ዝቅ ያለ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ዘንድሮ በተደረገው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የታየው የሴቶች ተሳታፊነት እና ድምጽ ለመስጠት የነበራቸው መነቃቃት ይበል የሚያሰኝ ነው። የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች እውነታ ብንመለከት አብዛኛው ድምጽ ሲሰጥ የነበረው አዛውንት ሴቶች እና ወጣት የሆኑት ሴቶች በስፋት የታዩበት ነበር። እነዚህ ሴቶች ማኅበረሰቡ የሚሰጣቸውን ዝቅተኛ አመለካከት ጥሰው በመውጣት ጀግንነታቸውን አሳይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በገዢው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የታየው የሴቶች አሳታፊነት በዘንድሮ ምርጫ የታየ ነው። ፖለቲካዊ ተሳትፎ ሲባል ባደጉት አገራት እንደሚታየው ሴት አገር የመምራት አቅም እንዳላት የሚያሳይ ትልቅ አስተዋጽኦ ነው። ይህ የሴቶች ንቁ ተሳትፎ በይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኹሉም የማኅበረሰብ ክፍልም ሆነ ራሳችን ሴቶች ንቃተ ህሊናችንን በማዳበር ለሕብረተሰቡም ይህንን መነቃቃት ማሳየት ድርሻችን ሊሆን ይገባል። ሴት ማለት ኹሉንም ሥራዎች መሥራት የምትችል፣ በአመራርነት ደረጃ የምትበቃ እና በማንኛውም ዘርፍ መሳተፍ የሚያስችል የራሷ የሆነ አቅም ያላት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
በማኅበረሰባችን ስለ ሴት ሲነሳ ዝቅ እንድትል የሚያደርጋትን ባህላዊ አመለካከትን ሙሉ በሙሉ መቀየር ያስፈልጋል። የሴቶች ንቁ ተሳትፎ ለአገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በምታከናውናቸው ትልልቅ ሥራዎች ማሳየት አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህ ውጤታማ ሥራ ማሳያ ደግሞ የሚሆነው በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚገኙ እድሎችን መጠቀም ነው። ታዲያ ልክ በዘንድሮ ምርጫ ሴቶች እንዳገኙት ሰፊ የተሳትፎ እድል በሌሎች ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ እድል ይፈጠርላቸው ዘንድ ይገባል።
በየትኛውም የመንግሥትም ይሁን የግል ተቋማ ሴቶችን ለማሳተፍ ዝግጁነት እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይህን የተቋማት ዝግጁነትና መነቃቃት ለመፍጠር የዘንድሮ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ አንዱ ማሳያ መሆን ይችላል። ሴት ልጅ ዕድል የሚሰጣት ከሆነ ከወንዶች እኩል መሳተፍ እና ተወዳድራ ማሸነፍ ትችላለች። ሴት በመሆኗ የምታከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ የሚሆነው ያለባትን የቤት ውስጥ ጫና እና ተፈጥሮአዊ ችግሮችን ተቋቁሟ መሆኑ ይበልጥ ጠንካራ መሆኗ ማሳያ ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013


