የምርጫ ሂደቱ እና የታዛቢዎች ህብረት

በስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሲቪል ማኅበራትን ተሳታፊነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል 176 ማኅበራት በጋራ በመሆን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ኅብረት ለምርጫ የተሰኘ ድርጅት ተመስርቷል። ኅብረቱ ገለልተኛ እና ከፖለቲካ ፓርቲ ነጻ የሆነ ድርጅት ሲሆን ምርጫው አካታችና ግልጽነት የተሞላበት መሆኑን ለማረጋገጥ የሚሰራ ድርጅት ነው።

ኅብረቱ ተመስርቶ ሕጋዊ እውቅናውን ያገኘው በግንቦት 12/2012 ሲሆን በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ሊያከናውናቸው የወጠናቸውን ሥራዎች ለመፈጸም በሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ወቅት የሠራው የትዝብት ሥራ ጠቃሚ ልምድ ሰጥቶታል። በዘንድሮው ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ እና የምዝገባ ሂደትን በተመለከተ ኅብረቱ ምን አይነት ሥራዎችን ሲሠራ እንደቆየ በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ፣ የምርጫ መታዘብ አስተባባሪ የሆነው ቢኒያም አባተ ከአዲስ ማለዳዋ ሰላማዊት መንገሻ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ኅብረቱ ለምን ዓላማ ነው የተቋቋመው?
በዋናነት ለኅብረቱ መሰባሰብ ምክንያት የሆነው በ2010 የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ምርጫ እንደሚካሄድ ቃል መገባቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
በያዝነው ዓመት የተከናወነውን 6ኛው አገራዊ ምርጫ፣ በ2010 ዓ.ም የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ስር እንዲሰድ እንዲሁም በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የተደረገው ጥረት ወሳኝ መሆኑን ተገንዝቧል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ከአባል ድርጅቶቹ የተወጣጡ ታዛቢዎች መልምሎ በማሰልጠንና የምርጫ ሂደቱ አካታች፣ ግልፅ እንዲሁም ተዓማኒነት ያለው መሆኑን እንዲታዘቡ በማድረግ ምርጫው ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ የተቋቋመ ነው።

የምርጫ ትዝብት ዓላማ በምርጫ ሂደት ለዜጎች፣ ለዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ለሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ለተለያዩ የመንግሥት አካላት ከፓርቲ ወገንተኝነት ነፃ የሆነን መረጃ የማሰባሰብ እና የማቅረብ ሲሆን፣ ይህን መረጃ መሰረት በማድረግ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የምርጫውን አካታችነት፣ ግልጽነት እና ተዓማኒነት እንዲገመግም ያስችላል።

ምርጫውም ነጻ፣ፍትሃዊና አሳታፊ እንደሚሆን እምነት በመኖሩ እንዲሁም የሲቪል ማኅበራቱ ሚና ምርጫ ላይ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማበረታት እና የሲቪል ማኅበረሰቡን ለማስተባበር የተቋቋመ ነው።
ይህ ተቋም ከተመሰረተ አንድ አመት ከ10 ወር ጊዜ ያስቆጠረ ሲሆን መነሻ ያደረገው ለውጡንና ምርጫውን ነው። ይህ ኅበረት ለዚህ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት በዲሞክራሲ፣ በምርጫ እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩት ድርጅቶች አንድ የጋራ ኅብረት እንዲፈጥሩ፣ የተሻለ የሆነ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የተደራጀ ነው።

ኅብረቱን ለማቋቋም 7 ከተለያዩ ማለትም በሴቶች፣ በአካል ጉዳተኞች፣የሙያ ማኅበራት እና በምርጫ ዘርፍ ያሉ በማሰባሰብ አስተባባሪ ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር። በመቀጠልም 60 ያህል የሲቪል ድርጅቶች የዚህ ስብስብ አባል መሆን ችለዋል።
በኅብረቱ ምስረታ ሂደት ያጋጠመው ጉዳይ አንዱ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ነበር። ይህ ሕዝበ ውሳኔ በሚካሄድበት ጊዜ ኅብረቱ እውቅና አግኝቶ አልተቋቋመም ነበር። ገና የምዝገባ ሂደት እያከናወነ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘብ ቀጥተኛ ግብዣ ቀርቦለት ነበር። በዚህ ወቅት ኅብረቱ ያደረገው ተግባር ጥንካሬውን ለማሳየት በሦስት ሳምንት ውስጥ ዝግጅቱን አጠናቆ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔንን ለመታዘብ ችሏል።
በአጠቃላይ ኅብረቱ የተቋቋመው በምርጫ እና በዲሞክራሲ ዙሪያ የሚሰሩ ማኅበራት በጋራ ተደጋግፎ ለመስራት እንዲያመች ተደርጎ ነው።

ኅብረቱ እስከአሁን የሠራቸው ሥራዎች እና ውጤቶቹ ምን ይመስላሉ?
ከላይ እንደተጠቀሰው ኅብረቱ ከሠራቸው ሥራዎች አንዱ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን መታዘብ ሲሆን፣ ለዚህም 160 ታዛቢዎችን በመላክ ትልቅ ሥራ ተሠርቷል። በዚህ ሥራ መሳተፉ የኅብረቱን ሙያዊ ብቃት ከማሳደግ እና የምርጫ ቦርድን ሥራ በኃላፊነት በመወጣት ትልቅ መንገድ የጀመረበት ነው። በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የሚካሄደው የምርጫ ሂደት ከምርጫ ቦርድ ደንብ ጋር የሚስማማ መሆኑን ለማረጋገጥ የምርጫ ጣቢያ አዘገጃጀትን መገምገም የኅብረቱ ቁልፍ ተግባር ነው።

በመሆኑም የኅብረቱ ታዛቢዎች በተዘጋጀላቸው መጠይቅ መሠረት የምርጫ ጣቢያዎችን አዘገጃጀት ገምግመው ሪፖርት የማድረግ ሥራ ሠርቷል። እነዚህ ጥያቄዎች የምርጫ ጣቢያዎችን ተደራሽነት፣ የምርጫ ቁሳቁሶች አቅርቦትን እንዲሁም በሂደቱ ውስጥ የተሳተፉ ታዛቢዎች፣ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች እና የፓርቲ ወኪሎችን የሚመለከቱ ናቸው።

ከዚህ በመቀጠል ዘንድሮ በተካሄደው ምርጫ የሠራነው ሥራ በብዛት ውጤታማ ነበር። በተለይ ስለዲሞክራሲ እና የመምረጥ መብት መጠቀም ግንዛቤ የሌለባቸውን አካባቢዎች በተለያዩ መንገዶች ተደራሽ ለማድረግ ሲሠራ ቆይቷል። በተጨማሪም አባል ድርጅቶቹ ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን በምን መልኩ መፍታት እንዳለባቸው እና የአመራርነት ክህሎትን የማሳደግ ሥራ ሠርቷል።

ለኅብረቱ ታዛቢዎች ሥልጠና ሲሰጥ የነበረው በምን መልኩ ነበር?
European Centre for Electoral Support (ECES) ከሚባል አጋር ድርጅት ጋር በመተባበር በተለይ በሲቪል ማህረሰብ ውስጥ የሚሳተፉ ከኹሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለተወጣጡ ሰልጣኞች ተከታታይ የአመራርነት ክህሎት ማሳደግ ሥልጠና ተሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ከማስተርስ ዲግሪ ጋር በሚመጣጠን ደረጃ ከ80 በላይ ለሆነ የሲቪል ማኅበረሰብ ውስጥ በአመራር ቦታ ላይ ለሚገኙ አባላት በጣሊያን ከሚገኙ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን የክህሎት ማሳደግ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።

ኅብረቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ባካሄደባቸው ሰባት ክልሎች እና ኹለት የከተማ አስተዳደሮች፤ ከ3000 በላይ የሚሆኑ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን አሰልጥኗል። ቋሚ ታዛቢዎች የታዘቧቸውን መረጃዎች በአዲስ አበባ ወደሚገኘው የኅብረቱ የመረጃ ማዕከል በጽሁፍ መልዕክት የላኩ ሲሆን፣ ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎች ደግሞ በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ ከምርጫ ጋር የተገናኙ ሂደቶችን እንዲሁም የድምፅ አሰጣጥ ሂደትን ከአንድ ምርጫ ጣቢያ ወደሌላ በመዘዋወር ታዝበዋል።

ሰኔ 14 የተካሄደውን ምርጫ እና ቀድሞ በነበረው የምርጫ ዝግጅት ላይ ምን አይነት ሥራዎችን ሠርታችኋል?
በቅድመ የመራጮች ምዝገባ ወቅት የነበረን ትዝብት ስንመለከት ከኅብረቱ የተወጣጡ 140 ያህል ታዛቢዎችን በተለያዩ ምርጫ የሚካሄድባቸው የአገሪቱ ክፍሎች እንዲሰራጩ በማድረግ ታዝበዋል። በዚህም 1200 የሚደርሱ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን መታዘብ ተችሏል።

ኅብረቱ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የመራጮች ምዝገባን ማካሄድ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከባድ የቤት ሥራ እንደነበር ይታወቃል። የመራጮች ምዝገባ ምንም እንኳን ዘግይቶ ቢጀመርም በጸጥታ ችግሮች እንዲሁም ከምርጫ አስፈጻሚዎች በቀረቡ የተለያዩ ቅሬታዎች ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ በአንዳንድ ቦታዎች በጭራሽ አልተካሄደም ነበር።

ነገር ግን የመራጮች ምዝገባ ጣብያዎች ከተከፈቱና ምዝገባው ከተጀመረ በኋላ የኅብረቱ ታዛቢዎች በታዘቧቸው 1,192 ጣብያዎች መረጃ መሰብሰብ ተችሎ ነበር።

የምርጫ ቀንን ለመታዘብ በተዘጋጀው የትዝብት መጠይቅ ላይ በመመስረት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ የተሰጣቸው ታዛቢዎች የምርጫ ጣቢያዎችን ዝግጅት፣ አከፋፈት፣ የድምጽ አሰጣጥ እና ቆጠራ እንዲሁም የድምጽ ቆጠራ ውጤት በሚለጠፍበት ጊዜ የነበሩ ሁኔታዎችን ታዝበዋል።

ኅብረቱ የምርጫ ቀን ትዝብቱን ሥልታዊ በሆነ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ምርጫው በተከናወነባቸው በኹሉም የአገሪቱ ክፍሎች ወጥነት እና ጥራት ያለው መረጃ ለማሰባሰብ የሚያስችል የትዝብት መጠይቆችን ተጠቅሟል። ይህ አሰራር የኅብረቱ ምልከታ፣ መረጃ አሰባሰብ እና ትንተና ሂደት ስልታዊ እንዲሆን ብሎም በመላ አገሪቱ በነበሩ የምርጫ ቀን ክንውን መረጃዎች ለዜጎች እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲደርስ ለማድረግ አስችሎታል።

ከቋሚ ታዛቢዎች በተጨማሪ ከ150 በላይ ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን በማሰማራት በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የተከሰቱ አሳሳቢ ኩነቶችን ለመረጃ ማዕከሉ እንዲልኩ ተደርጓል። የድምጽ መስጫ ቀን ላይ ኅብረቱ አስቦ የነበረው 4000 ያህል ታዛቢዎችን ለማሰማራት የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተወሰኑትን ብቻ በማሰማራት ለመታዘብ ችለናል።

ከእነዚህ 4000 የሰለጠኑ ታዛቢዎች መካከልም 3000 ብቻ ማሰማራት ነው የተቻለው። እነዚህ ታዛቢዎች በቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ታዛቢ በመባል ይታወቃሉ። ከእነዚህ ታዛቢዎች ውስጥ በቋሚነት የተቀመጡት አዲስ አበባ ከሚገኘው የመረጃ ማዕከል በቀን ከ5 ጊዜ ድረስ የጽሁፍ መልክቶችን ያደርስ ነበር።

ካሰለጠናችሁት 4000 ታዛቢ ቀሪዎቹ ያልተሳተፉት በምን ምክንያት ነው?
ለዚህ የተለያዩ አይነት እንከኖች አሉ። ምንም እንኳን 4000 የሚደርሱ ታዛቢዎችን ብናሰለጥንም በዋናነት የመታዘቢያ ፍቃድ ባጅ ከምርጫ ቦርድ በጊዜው ባለመድረሱ ምክንያት የተወሰኑት መታዘብ አልቻሉም ነበር። አንድን ታዛቢ ፍቃድ ለመስጠት ምርጫ ቦርድ የሚወስደው የ15 ቀን የጊዜ ሁኔታ ላለማሳተፍ እንደዋና ምክንያት ይነሳል። ከዚህ በተጨማሪ ባጅ ከተገኘ በኋላ ለታዛቢዎች በወቅቱ ተደራሽ አለማድረግ ነው። ይህ ሲባል ኅብረቱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ለታዛቢዎች ተደራሽ ማድረግ አለመቻል ነው። ተደጋጋሚ የባጆች መታተም አንዱ ምክንያት ነው።

ተሰማሩ ከተባሉ ታዛቢዎች መረጃዎች በወቅቱ አይደርሱም ነበር። በምን ምክንያት የተፈጠረ ነው?
መረጃዎችን የምንቀበለው በተለያየ መንገድ ነው። በተለይ ተቀማጭ ታዛቢዎች በመልዕክት ጽሁፍ እና በስልክ የሚያደርሱ ናቸው። እነዚህ ታዛቢዎች ይህን መንገድ ተጠቅመው የሚልኩት ከተለያዩ ክልል ከሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ነው። እነዚህን መልዕክቶች በቀን ከ5 ጊዜ በላይ በተለያዩ ሁኔታ ውስጥ በመሆን የሚልኩበት ነው። ይህንን በቀን 5 ጊዜ መረጃ የመለዋወጥ ተግባር የሚከናወነው በስልክ በመሆኑ አገሪቷ ካለችበት የተሟላ የመሰረተ ልማት ችግር ምክንያት የተፈጠረ ነው። ለመታዘብ የተመደቡት ሰዎች የሚገኙበት አካባቢ ዕለቱ ምርጫ አይካሄድባቸውም በመባሉ ወደ ስራ ያልገቡ ነበሩ። ታዛቢዎቹ የተመረጡት በየአገሪቱ ካሉ ወረዳ እና ቀበሌ ላይ በመሆኑ በቦታው ቢገኙም ባጅ ባለመያዛቸው በሚፈለገው ያህል መቃኘት አልቻሉም።

ተንቀሳቃሽ የሚባሉት የኅብረቱ ታዛቢዎች የምርጫው ውጤት እስኪጠናቀቅ የሚያገኙትን መረጃ ወደ ዋናው እንደሚያደርሱ ሊታወቅ ይገባል።ስለዚህ መረጃ ካደረሱ 2200 ታዛቢዎች የተቀሩት ቀስ በቀስ መረጃ የማድረስ ሥራቸውን ይቀጥላሉ።

ኮቪድ 19 እና የተካሄደው የድምጽ አሰጣጥ እንዴት ታዘባችሁ?
ኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑ ይታወቃል። የአገሪቱ 6ኛው ምርጫ የተራዘመበት አንደኛው ምክንያት ነው። ስለዚህ በድምጽ አሰጣጥ ቀን ብቻ ሳይሆን በመራጮች ምዝገባ ወቅት ጭምር ኮቪድ 19ን ለመከላከል ሲወሰዱ የነበሩ ጥንቃቄዎች በቦርዱ የነበረውን አፈጻጸም ለመቃኘት ሞክረናል።

6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚካሄደው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተስፋፋ በሚገኝበት ወቅት ላይ እንደመሆኑ ኅብረቱ አተኩሮ ከታዘባቸው ጉዳዮች መካከል ከድምጽ አሰጣጡ ቀድሞ የነበረው የምዝገባ ሂደት ላይ ቫይረሱን ለመከላከል የተደረጉ ጥረቶች እና አፈጻጸማቸው አንዱ ነው። ከእነዚህም መካከል የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች (face masks) እና የእጅ ማጽጃዎች (sanitizers) በአብዛኞቹ ጣቢያዎች አቅርቦት መሟላቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ 52 በመቶ ያህል በሚሆኑ ጣቢያዎች የእጅ መታጠቢያ ቦታዎች አልነበሯቸውም። ከዚህ በተጨማሪም 60 በመቶ የሚሆኑ ኅብረቱ የታዘባቸው አስፈጻሚዎች የእጅ ጓንቶች (Gloves) አልነበሯቸውም።

ኅብረቱ ከጎበኛቸው 13 በመቶ ከሚሆኑት ጣቢያዎች መካከል የምርጫ አስፈጻሚዎች የፊት ጭምብሎችን ያላደረጉ ሲሆን፤ 28 በመቶ የሚሆኑ የምርጫ አስፈጻሚዎች በአንጻሩ በወቅቱ የፊት ጭምብሎችን ያደረጉ ነበሩ። በተጨማሪም 23 በመቶ በሚሆኑት ጣቢያዎች ዜጎች የፊት ጭምብሎችን ያላደረጉ ሲሆኑ፣ 48 በመቶ በሚሆኑት ጣቢያዎች መራጮች የፊት ጭምብሎችን ያደረጉት በከፊል ብቻ መሆኑ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ከላይ እንደሚታየው በምዝገባው ወቅት ከቫይረሱ ጋር የተያያዙ የተለያዩ የጥንቃቄ ክፍተቶች ያሉ ሲሆን፣ 89 በመቶ ያህል በሚሆኑት የምርጫ ጣብያዎች የኮቪድ19 ባለሙያዎች አለመገኘታቸው ለሚታዩት ክፍተቶች ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደነበረው ታይቷል።

በዚህ ጊዜ ያገኘነው በመራጮች በኩል የነበረው አለመጠንቀቅ አሳሳቢ እንደነበር ታዝበናል። በዚህም መራጮች የምርጫ ካርድ በሚወስዱበት ጊዜ ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ስለነበር የድምጽ አሰጣጥ ቀን ላይ ይህ መዘናጋት እንዳይደገም ከጤና ሚኒስቴር ጋር ሰፊ ውይይት አድርገን ነበር። ይህ ደግሞ ኅብረታችን ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ከማድረግ አንጻር የሠራው ቀዳሚ ሥራ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የድምጽ አሰጣጡ ቀን ላይ ግን በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ውስጥ የነበረው ሂደት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ጥንቃቄ መተግበር ሲገባው ይህ ሳይሆን ቀርቷል።

ከኅብረቱ ምን እንጠብቅ?
ኅብረታችን በአሁኑ ወቅት ካለው አቅም በተጨማሪ ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ተደጋግፎ መሥራት ይጠበቅበታል። እንደ ታዛቢ ኅብረት በየጊዜው ህጸጾችና ችግሮችን መፈለግ ብቻ ሳይሆን የምርጫ ሂደት ማጭበርበሮችንም እንዲጋለጥ የሚያደርግ ነው። የኛም ዓላማ ድምጽ የሚሰጥባቸውና ምርጫ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ላይ በመሰማራት ሂደቱን የመከታተል እና ምርጫ ቦርድን የመደገፍ ሥራ የመሥራት ዓላማ ያለው ነው። ምርጫ ቦርድ ያልደረሰባቸውን መረጃዎችን በፍጥነት የማድረስ ሥራ እና ሕብረተሰቡም ስለምርጫው ግልጽነትና አሳታፊነት እንዲያውቅ ለመሥራት የቆመ ነው።

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (CECOE) ከ176 በምርጫ ዙርያ የተለያዩ ሥራዎችን የሚሠሩ አገር በቀል የሲቪል ማኅበራት ስብስብ በመሆኑ በቀጣይም ትልልቅ ተግባራትን ለማከናወን ቆርጦ የተነሳ ድርጅት ነው። ኅብረቱ መጪውን አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በተመለከተ የዜጎች ተሳትፎ ከቅድመ ምርጫ አንስቶ እስከ ድህረ-ምርጫ ድረስ የተረጋገጠ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here