ንግድ ባንክ ሠራተኞቹ በሥራ ሰዓት ስልክ እንዳይጠቀሙ ከለከለ

Views: 693

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥቅምት 03/2012 ከ30ሺህ ለሚልቁ ሰራተኞቹ በላከው የውስጥ ማስታወሻ የደንበኛ አገልግሎት የሚሰጡ የድርጅቱ ሠራተኞች በሥራ ሰዓት የስልክ ጥሪን ጨምሮ የማህበራዊ ሚድያ እና ሌሎች የሞባይል ስልክ አገልግሎቶችን እንዳይጠቀሙ ከልክሏል።

በሲስተም መጨናነቅ ምክንያትና የኤቲኤም ማሽኖች በአግባቡ ባለመሥራታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የደንበኞቹ ቅሬታ እየጠነከረ የመጣበት ባንኩ፣ በስትራቴጂክ እና ኢኖቬሽን ክፍሉ አማካኝነት አጠናሁ ባለው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፤ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቶ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። ለዚህም አንኳር ተብለው ከተቀመጡ ምክንያቶች መካከል የደንበኞች አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች የሞባይል ስልክ አጠቃቀም ሆኖ በመገኘቱ በውስጥ እርምጃው እንዳስፈለገ የውስጥ ማስታወሻው ላይ መጠቀሱን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

ባንኩ በዚሁ ጥናት ላይ ተመርኩዞ ‹‹አጠቃላይ ስር ነቀል የአገልግሎት አሰጣጥ ለውጥ እስኪደረግ ድረስ አገልግሎት ሰጪዎች የሞባይል ስልኮቻችሁን በሥራ ሰዓት ከመጠቀም ተቆጠቡ›› ሲል ቀጣይ እርምጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም አመላክቷል። መመሪያውን ተላልፎ የተገኘ ሠራተኛም በቅርብ ኃላፊዎች አማካኝነት አስፈላጊው አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት የውጥ ማስታወሻው ቢጠቅስም በቀጥታ የቅጣቱ ምንነት ግን አልተገለፀም።

የደንበኞች አገልግሎት ሰጪ በመሆን ለዓመታት ያገለገለ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የባንኩ ሠራተኛ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው፣ ከዚህ ቀደም ከሞባይል ጋር የተገናኘ መመሪያም ሆነ ሕግ ያልነበረ ሲሆን የአሁኑም በተለይ ፊት ለፊት ከደንበኞች ጋር የሚገናኙና የመስኮት አገልግሎት ለሚሰጡ ሠራተኞች የወጣ ነው። በሥራ ሰዓት የሞባይል ስልክ ከመጠቀም አንጻር ያን ያህል የተጋነነ ተጠቃሚ እንደሌለና መመሪያው በ ‹‹ሩቅ እንደማጠር›› ሠራተኞች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሲባል በውስጥ መመሪያነት ሠራተኛውን ለማስታወስ የተላለፈ ነው ብሏል።

የንግድ ባንክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የአብሥራ ከበደ በበኩላቸው፣ ባንኩ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን (ሰርቪስ ኤክሰለን) ዋና ርዕዮ እንደሆነ አንስተዋል። ለዚህም የሠራተኞች የባህሪ ለውጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም መሠረት ባንኩ ደንበኛ ሳይጉላላና ሳይንገላታ የሚፈልገውን አገልግሎት በአጭር ጊዜ እንዲያገኝ የማድረግ አሠራር ለመመለስና ለማስቀጠል ነው ይህ የውስጥ መመሪያ የወጣው ብለዋል።

‹‹በፊት ሠራተኛው አራትና አምስት ሺሕ ነበር፣ አሁን አርባ ሺሕ ደርሷል›› ያሉት የአብሥራ ‹‹የሰው ኃይል እየበዛ ሲሔድ ለአመራር ፈታኝ ሆነው የሚያጋጥሙ ጉዳዮች አሉ›› ብለዋል። ይህም መመሪያ አገልግሎት ፈልጎ የመጣን ደንበኛ አቁሞ ስልክ ማውራት ክልክል ነው የሚለውን ለመግለጽ፤ ደንበኛን ከማክበር የመጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም ሠራተኞች የተለያየ የግል ጉዳይ ሊገጥማቸው እንደሚችል የታወቀ ሆኖ፣ ቅድሚያውን ግን ለደንበኛና ለመስተንግዶ እንዲሰጡ ለማድረግ ያሰበ ነውም ብለዋል።

የባንኩ ስትራቴጂክ እና ኢኖቬሽን ክፍል ለወራት በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ባደረገው ሰፋ ያለ የዳሰሳ ጥናት፣ እነዚህ ምልክቶች መታየታቸውንና ይህም ከሞባይል ስልክ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የውስጥ መመሪያው እንዲወጣ ምክንያት እንደሆነም ነው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው የጠቀሱት።
ከ22 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ 1 ሺሕ 450 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎቹ 40 ሺሕ የሚጠጉ ሠራተኞች የሚያስተዳድር ባንክ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com