ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ በኢትዮ ምኅዳር ጋዜጣ ላይ በሠራው ዜና ምክንያት “ሥም አጥፍተሃል” ተብሎ ለአንድ ዓመት እስር ተዳርጎ ነበር። እነሆ ከእስር ቤት ትዝታዎቹ መካከል በ2008 የጥምቀት በዓል በሸዋ ሮቢት እስር ቤት ዞን ሦስት የተፈፀመውን አሳዛኝ ድርጊት በትዝታ ያስነብበናል።
እንደ እውነቱ ከሆነ የታሰርኩት ልሸለምበት በሚገባ ጉዳይ (የምርመራ ዜና) ነበር። በጋዜጠኝነት “ለድምፅ የለሾች ድምፅ መሆን” የሙያው ግዴታም ጸጋም ነው። እናም የታሰርኩት ለዚህ የሙያው መርሕ ነው፤ በመሆኑም በእስር ቤቱ (በረት) ውስጥ በዓይኔ በብሌኑ ያየሁትን የሌሎች ዜጎች በደሎችን፣ አብሬ የቀመስኩትን አሳዛኝ የቅጣት ሕመም፣ የእስረኞች መድልዎ እና የጥቂት ደልቃቃ እስረኞች ክብር፣ ከእስር መልስ አጣርቼ ያረጋገጥኩትን ኹነቶች እና የበረቱ (የእስር ቤቱ) አለቃ የነበረው የማነ አሰፋ “ገድለ- ዲያቢሎስ” ሥራዎችን፣ እንዲሁም ሌሎች ተጨባጭ ኹነቶችን በዚህ መጣጥፍ ላይ አካትቼ በአጭሩ እተርካለሁ።
ቅድመ ታሪክ
እስር ቤቶችን (ጣቢያዎች፣ ቂሊንጦ፣ ቃሊቲ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ዝዋይ ወዘተ) በቅጡ ላስተዋለ ሰው፣ የከብቶች በረት እንጂ፣ ማረሚያ ቤት አይመስሉም። አይደለም የሕሊና እሥረኞች (ጋዜጠኞች፣ ጦማርያን የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ መብቴን አላስነካም የሚሉ ዜጎች) ይቅርና፣ ደረቅ ወንጀል የሠሩ አፈንጋጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንኳ ሊታረሙበት አይችሉም፤ ይልቁንም የበለጠ አፈንጋጭ ወንጀለኛ ሆነው የሚወጡበት ዕድል ከፍተኛ ነው። በበረቱ ውስጥ ያለው ድርጊት ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይህን ነው የሚያስተምረው።
በዚህ ላይ እኔ በነበርኩበት ወቅት ቂሊንጦ ጊዜያዊ “ማረፊያ” ዞን ሦስት አንደኛ ቤት ውስጥ ብቻ ወደ ሦስት መቶ ስልሳ ሰባት ሰዎች ደርሰን ነበር። ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ዞን ሦስት በአጠቃላይ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሃያ ስምንት የነበርን ሲሆን፣ ዐሥረኛ ቤት ውስጥ ብቻ እንኳ ወደ አራት መቶ ከምናምን ደርሰን ነበር። ይህ የበረቱ አንዱ ማመላከቻ ነው። ሰው በሰው ላይ አስመራ ድርድር ተደርቦ ይዘረራል። ይተኛል ማለት ይከብዳል።
የበረቱ አለቆች (እረኞች) ደግሞ ጉምቱ የሕወሓት ታጋዮች ነበሩ። እነዚህ “ጨዋ” የገበሬ ልጆች፣ “ውድብ” (ድርጅታቸው ሕወሓትን የሚጠሩበት ቃል) አድርጉ ብላ ያዘዘቻቸውን ሁሉ እንደ ፈጣሪ ቃል ከላይ ወደ ታች አክብረው፣ በፍፁም ታዛዥነት ያለምንም የልቦና (ሕሊና) ጥያቄና ማመንታት የሚተገብሩ “ትጉህ ተጋዳላይ” መሆናቸውን በቆይታዬ ታዝቤያለሁ። ሕይወታቸው በዚህ የተጋዳላይ “የአድርግ-አታድርግ” መርሕ ብቻ የሚመራ መሆኑን ከድርጊታቸው መረዳት ይቻላል።
የሸዋ ሮቢት “ማረሚያ ቤት” ዋና ሰው የነበሩት “ተጋዳላይ” የማነ አሰፋ፣ ባልደረቦቻቸው እንደነገሩኝ የትውልድ ሥፍራቸው አላማጣ ሲሆን፣ በ1970 ወደ ሕወሓት የትግል ዓለም ተቀላቅለዋል። የደርግ መንግሥት በሕወሓት/ኢሕአዴግ መራሽ መንግሥት መተካትን ተከትሎ እሳቸውም ልክ እንደ ትግል አጋሮቻቸው ወደ መካከለኛ አመራርነት ተመድበው በመጀመሪያ በዓለም በቃኝ ወሕኒ ቤት፣ ቀጥሎ ድሬዳዋ “ማረሚያ ቤት”፣ ከዚያ ቂሊንጦ ቀጠሮ “ማረፊያ ቤት” እና በመጨረሻ ሸዋ ሮቢት “ማረሚያ ቤት” በኃላፊነት ሠርተዋል።
ያልተከበረው ጥምቀት የአከባበር ዝግጅት
ረቡዕ ጥር 10 ቀን 2008 የዋለውን የጥምቀት (ከተራ) በዓል ለማክበር የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት እስረኞች ዝግጅት የጀመሩት ሦስት ወራት ቀደም ብለው ነው። በእስር ቤቱ ውስጥ በሚገኘው “እስረኛው መድኃኔዓለም” ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ እስረኞች በዋናነት ኮሚቴ አዋቅረው ዝግጅት ያደረጉ ሲሆን፣ ጸሎት፣ መዝሙራት እና መወድስም አዘጋጅተው ነበር። ሌሎች እስረኞችም ተጓዳኝ የሆኑ ዝግጅቶችን አድርገው በርከት ያሉ የጥምቀት ቲሸርቶችን፣ ነጠላዎችን ለማስገባት ችለው ነበር።
ማረሚያ ቤቱ በበኩሉ፣ በዐሥራ አምስት ቀን የሚደረገውን የበሬ እርድ ለበዓሉ ድምቀት ሲባል አሳልፎ (በጀቱን አሻግሮ)፤ የበዓሉ ዕለት ጥር 11 ቀን 2008 እና በማግስቱ የሚካኤል ቀን በተከታታይ ለኹለት ቀናት እርድ ተካሒዶ የፍስክ ምሳ ይኖራል ተብሎ፣ የበሬ ግዢ ተካሒዶ፤ በሬ አራጅ ከእስረኛው ተመልምሎ ነበር።
ሆኖም፣ ረቡዕ ጥር 10 ቀን 2008 የእስር ጊቢው በእንዲህ ዓይነት የመነቃቃት መንፈስ ውስጥ ባለበት ጊዜ፣ እኩለ ቀን ላይ ምሳ እደላ መዘገጃጀት በጀመረበት ጊዜ “ሙጋቤ” በተባለ ወጠምሻ እስረኛ እና በሦስት (የኮልፌ እና የጨው በረንዳ ታዳጊ ወጣቶች) መካከል ፀብ ተፈጠረ።
የፀቡ መነሾ “ሙጋቤ” የሚባለው “ደጋጋሚ” ወንጀኛ ነው የሚባለው እስረኛ (አብዛኛው የደረቅ ወንጀል ደጋጋሚ እስረኛ “ቆሻሻ” (ቆሼ) ብሎ ፈርጆት አግልሎታል፤ ይህ ሥም በብዛት የሚሰጠው የሚሆነው የተከሰሰበት ክስ ከተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ከሆነ ነው።)
በአፀፋው እርሱ ደግሞ፣ ግንኙነቱን በሙሉ ከፖሊሶች ጋር አድርጎ፣ እርሱ ያለበት 10ኛ ቤት በእያንዳንዱ ሌሊት ምን እንደተደረገ፣ ምን እንደታሰበ በመሰለል ከቤት አስተዳደሩ ማልዶ ለፖሊሶች ዘገባ ያቀርባል። ከፖሊሶች ባገኘው ግብዣም በእያንዳንዱ ቀን በዞን ተጠሪ ቢሮ ውስጥ በሚደረገው አመክሮ የማግኘትና የማጣት የእያንዳንዱ እስረኛ ግምገማ ላይ ከፖሊሶች ጎን ተቀምጦ ፖሊሶች የዘነጉትንና መለየት የተሳናቸውን ሥም ለዋጭ ደጋጋሚ እስረኛ በመገምገም እየመነጠረ ያጋልጣል። (እንዲህ የሚያደርጉ እስረኞች በእስረኞቹ አጠራር “አስጠጪ” ነው የሚባሉት።)
በዚህ ሥራው የዞን ተጠሪው ዋና ኢንተንዴንት ቅርብ ሰው ሆኗል። በማረሚያ ቤቱ ውስጥ እንደ ፈለገ የሚንቀሳቀስ እስረኛ ሆኗል። ለሌሎች እስረኞች በደንብና በመመሪያ የተገደቡ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ለእርሱ የተፈቀዱ ሆነዋል። ከማረሚያ ቤቱ ወታደሮች ጋር ይበላል፤ ያመሻል። ለሌላው እስረኛ 10፡30 ሰዓት ላይ የሚዘጋው የበረቱ በር፣ ለእርሱ እንደ ቤቱ አባወራ አምሽቶ ሰዓት እላፊ ተከፍቶለት በአባላት ታጅቦ የሚገባበት የግል ጎጆው ሆኗል።
እነዚህ ሦስት (የኮልፌ እና የጨው በረንዳ) ሰፈር ልጆች፣ ቀናቸው ደርሶ ዞን ተጠሪ ለአመክሮ ግምገማ ይቀመጣሉ፤ ፖሊሶቹም የልጆቹን የቀድሞ እስረኝነታቸውን ዘንግተው የአመክሮ መብታቸው ተከብሮላቸው ሊወጡ ሲሰናዱ፣ ሙጋቤ ደርሶ ያጋልጣቸዋል፤ ማጋለጥ ብቻም ሳይሆን ከዚህ ቀደም አብሯቸው በታሰረበት ጊዜና ዞን ውስጥ ያለውን ፋይላቸውን በርብሮ አመክሯቸውን “ያስበላቸዋል” (ያሳግድባቸዋል)።
በዚህ ብስጭት ከንፈራቸውን ነክሰውበት፤ ለአመክሮ ከሚቀመጡ ደጋጋሚ ታሳሪዎች ገንዘብ እየተቀበለ እንዳላወቀ እንደሚያሳልፍ ምስክር ይዘው ለዞን ተጠሪ ቢያመለክቱም ሰሚ ፖሊስ ያጣሉ።
እናም፣ በዚህ ንዴት ከንፈራቸውን እንደነከሱ አልቀሩም፤ ለድብደባ አሳቻ ሰዓት (አብዛኛው የማረሚያ ፖሊስ) ለምሳ በሚወጡበት እኩለ ቀን ላይ ይጠብቁና፣ ምሳውን ሊቀበል ወደ ዳሱ ጎንበስ ሲል፣ እዛው አካባቢ የደበቁትን የባሕር ዛፍ ግንጣይ ዱላ አንስተው ጀርባውን ሲደበድቡት ሌሎች አጋዥ አጋሮቻቸው ደግሞ ድንጋይ በመወርወር ገላጋይ እንዳይገባ ከለላ ሰጧቸውና ደበደቡት።
ከምሳ በኋላ አብዛኛው የማረሚያ ቤቱ ወታደሮች በብዛት ወደ ጥምቀተ ባሕር ዝግጅት አምርተው የነበረ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ ግን ዘገባው ወደ ላይ አስተዳደር ደርሶ “ታጋይ” የማነ ወታደሮቹን አስከትሎ ከች አለ።
መጀመሪያ ሁሉም እስረኛ ወደ ማደሪያ ቤቱ (በረት) እንዲገባ ‘በሚኒ ሚዲያ’ አስነገረ። ልንበላ የነበረው “ደያስ”ም (እንደ ነገሩ ሽሮ) በቤታችሁ ይመጣል ተባለ። ከዚያ ሁላችንም ወደ ቤታችን ከተትን። በሩ በላያችን ላይ ተቆለፈ። ከጥቂት ቆይታ በኋላ በመጀመሪያ የሰባተኛ ቤት ቁልፍ ተከፍቶ ወደ ውጭ መንጋጋት፣ መጮህ፣ ማቃሰት፣ ማልቀስ ጀመሩ። በራችን ስለተቆለፈ የጣር ድምፃቸው ብቻ ይሰማናል። ቀጥሎም ፀሐይ ላይ እንዲሰጡ ተደረገ። ለአፍታ ፀጥ አሉ። አልፎ አልፎ የሚያቃስቱና የሚጮሁ ነበሩ። ቀጥሎ ስምንተኛ ቤት፣ ከዚያ የዘጠነኛ ቤት እስረኞች እንዲሁ ተደረጉ።
በመቀጠል የእኛው ዐሥረኛ ቤት ተራ ደርሶ በተርታ ሰልፍ መውጣት ስንጀምር “አኮብኩብ” የሚል ቀጭን የወታደር ትዕዛዝ ተሰማ። (አኮብኩብ ማለት እጅህን ወደፊት ዘርግተህ በርከክ ብለህ ጭንህ ላይ ብቻ በመቀመጥ /ከተረከዝህ ከፍ ማለት አለብህ/ እንደ እንቁራሪት የእንቁጢጥ እየዘለልክ መጓዝ ማለት ነው።) የማነ ነበር ፊት አውራሪው። በዚህ ላይ ከበር ጀምሮ ወታደሮቹ ሁሉ ባገኙት ነገር፡- በልምጭ፣ በጎማ፣ በከስክስ፣ በጥፊ፣ በቦክስ ያጋጠማቸውን እስረኛ ሁሉ ሳይለዩ ይማታሉ። ሜዳው ሁሉ በአቧራ ጢስ ተወረረ። ግርግር፣ ኹካታ ከዱላ ለመሸሽ፣ ከከስክስ ጫማ ካልቾ ለማምለጥ።
አቶ የማነም ያገኘውን ሰው በጎማ ይዠልጣል፣ ያስዠልጣል። እየተደነቃቀፍን መሐል ሜዳው ላይ ፀሐይ ላይ በሸዋ ሮቢት ሙቀት የእንቁጢጥ እንድንቀመጥ አዘዙን፣ ነቅነቅ ካልክ በልምጭ ጀርባህንና ወገብህን ትለመጣለህ። መነቃነቅህ ደግሞ በተርታው ውስጥ በቀላሉ ይታያል፤ ይለያል። ከኛ ቀጥሎም ዐሥራ አንደኛ ቤት፤ በመጨረሻም ዐሥራ ኹለተኛ ቤት እየተደበደቡ ወጥተው ፀሐይ ላይ ተዘረጉ።
ሙጋቤ እንደ ታጋዮቹ ሽርጡን አንገቱ ላይ አገልድሞ ጎንና ጎኑ ከሚንቀሳቀሱ የማረሚያ ቤቱ ወታደሮች ጋር ሆኖ፣ በ“ሥርዓት አስከባሪ” ተብዬ አድር ባይ እስረኞች በመታገዝ የጠሉትን፣ የተቀየሙትን ሁሉ “እርሱም አለበት!” እያሉ ሕዝበ አዳምን ተበቀሉት።
በታጋይ የማነ መርሕ መሰረት፣ ሙጋቤን ከደበደቡት ልጆች ባሻገር፣ አጋዥ ግብረ ኃይል የነበሩትን እስረኞች፣ የእነርሱ ጓደኞችን፣ ከእነርሱ ጋር አብረው የሚመገቡ “መቅዱሶችን”፣ አብረዋቸው የሚታዩ ልጆችን፣ በእነርሱ መኝታ አቅራቢያ ያሉ እስረኞችን ሁሉ ተለይተው እንዲወጡ ተደረገ።
እነዚህ ባየ፣ በነካ፣ በሰማ፣ በተጠጋጋ በደቦ የተለዩ እስረኞች በእኩለ ቀን የሸዋ ሮቢት ፀሐይ (ሙቀቱ አርባ እና አርባ ኹለት ሴንቲ ግሬድ የሚደርስበት ጊዜ አለ)፣ በወታደሮች በጎማ፣ በዱላ እየተዠለጡ፣ በከስክስ ካልቾ፣ በቦክስ እየተነረቱ፤ ወታደራዊ የስፖርት ቅጣት ማኮብኮብ፣ በጣታቸው አሸዋ ላይ በእስር ቤቱ ውስጥ የተከለከለውን “ፑሽ አፕ” ስፖርት እንዲሠሩ፤ አንዱ አንዱን አዝሎ ኮረት ድንጋይ ላይ በባዶ እግሩ እንዲዘል ካደረጓቸው በኋላ፣ ለማረሚያ ቡቱ እርሻ ፀረ አረም የሚረጨው ትንሽ አውሮፕላን የሚያርፍበት አስፋልት ላይ በጀርባቸው አንጋለዋቸው በፀሐይ እንዲመቱና አፍንጫቸው በደም ተጨማልቆ ነስር በነስር እንዲሆኑ አደረጓቸው። ጅማታቸው ግትርትር ብሎ፣ ራሳቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ተዘረሩ (ፌንት ሠሩ)። ቀሪዎቻችንን ይህንን ትዕይንት አይተን “ና ውጣ አንተ!” የሚባል እስረኛ በላዩ ላይ እስኪሸና ድረስ ፍርሐት ለቀቁብን። አንዳንድ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የኤች አይቪ ኤድስ ታማሚዎች እና አቅመ ደካማ ሽማግሌዎች በየቦታው ራሳቸውን ይስቱ ጀመር።
በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ አቶ የማነ እና መሰሎቹ የእነርሱ የሚመስሏቸውን ሰዎች በመልክ፣ በልዩ ምልክት፣ በቋንቋ ዘዬ እየለዩ ወደ ጥላ እና በረንዳ እየወሰዱ ከዱላው መዓት አራቋቸው። ከእኔ ወደ ሸዋ ሮቢት መጫን አንድ ሳምንት በኋላ ከቃሊቲ ወደ ሸዋ ሮቢት የተጫነው “በቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ ወንጀል” የታሰረው የከባድ መኪና ሾፌር የሰፈሬ ልጅ፣ በፊት መልክና በቋንቋ ዘዬ አጭር ምልልስ ከጎኔ የማነ ወደ ጥላ ቦታ ሲወስደው ፀሐይ ላይ ተሰጥቼ የተመለከትኩ የባዳ ምስክር ነኝ።
ከዚህ ሁሉ ባሻገር ግን አንድ ግለሰብ በሦስት ልጆች ስለተደበደበ፣ አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ሃያ ስምንት (በመሐል የተፈቱ እስረኞች ይኖራሉ) የዞን ሦስት እስረኛ የጅምላ ቅጣት ውስጥ ወደቀ። ይሄን በየትኛው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ ሕግና መርሕ እንዳደረገው የማነ እና መሰሎቹ ብቻ ናቸው የሚያውቁት።
ከረቡዕ ጥር 10 ቀን 2008 እኩለ ቀን ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2008 እኩለ ቀን ድረስ ቤታችን እንደተቆለፈብን አድረን ተቆልፎብን የምንውል ቅጣተኞች ሆንን፤ ቤተሰብ ጋር መገናኘት ተገደበ። ለሌሎችም ተከለከለ። የአንድ ቀን እርድ በጀቱ ታጠፈ፤ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ መፀዳዳት የምንችለው ረፋዱ ላይና ተሲያት በኋላ ብቻ በከፍተኛ ጥበቃ ሥር ሆነን ለሦስት ደቂቃወች ብቻ ሆነ፤ (ያውም በመሐሉ “ሰዓት አልቋል” መባል አለ)። ለዚያውም ሽንት ቤት ድረስ የምንሔደው በእንቁጢጥ “እያኮበኮብን” የነበር ሲሆን፣ በጎማ ወይም በዱላ ዥለጣ እና በካልቾ ንረታም እንታጀባለን። በነገራችን ላይ ሽንቴ አልመጣም ብሎ በመቅረት፣ የእንቁጢጥ ኩብኮባውንና በጎማ ወገብ ዥለጣውን ለማምለጥ ነው በሚል አይቻልም። ባትሸናም አኮብኩበህ ተዠልጠህ መምጣት ግዴታህ ነው። በአራት ቀን ውስጥ እስረኛው ሁሉ “ስትራፖ በስትራፖ” ሆነ። እኔም የእግሮቼ ጭንና ጭን ተሳሰረ።
እነዚያ ምንም የድርጊት ጥፋት ሳይኖርባቸው ባየ፣ በነካ፣ በሰማ፣ በአቅራቢያ የተለዩ እስረኞች ከዐሥራ አምስት ቀናት እስከ ኹለት ወር ድረስ ዞን አንድ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በስተጀርባ ወዳለው ጨለማ ቤት ተወስደው ተሰወሩ።
ድኅረ ታሪክ
በዚህ መንገድ የጥምቀት ዝግጅታችን ሁሉ ከሸፈ፤ እኔም የእስር ዘመኔን ጨርሼ ተፈታሁ። ኢትዮጵያም የፖለቲካ ለውጥ ማስተናገድ ጀመረች። የሸዋ ሮቢቱ ወሕኒ ቤት አምባገነን የማነም ከጥቅምት 2011 በኋላ አብዛኛው የሕወሓት ሰዎች ወደ ትግራይ በማፈግፈጋቸው፤ እሳቸውም የዚህ መዋቅራዊ ሒደት ተቋዳሽ በመሆን፣ ወደ ትግራይ ክልል በመዘዋወር የአላማጣ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሆነው ተሾመው ትግራይ ሔደው “መሽገዋል”።
ጌታቸው ወርቁ የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው ጋዜጠኛ ነው።
በኢሜይል አድራሻው getacheww7@gmail.com ሊገኝ ይችላል።
ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011