“ከመንግሥት ውጪ ታጥቆ መንቀሳቀስ የሚችል ኃይል መኖር የለበትም”

0
623

አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር) በዩናይትድ ኪንግደም ኪል ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በመምህርነት እንዲሁም በጥናትና ምርምርም ላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ጥናታቸው በአብዛኛው ሰብኣዊ መብት እና ዓለም ዐቀፍ ሕግ ላይ ያጠነጥናል። በተጨማሪም ከሕገ መንግሥት ጋር በተያያዘ ጥናት ያደርጋሉ። በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ባሉ ፖለቲካዊ፣ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቀት ያላቸው ጽሑፎች እንዲሁም ትንታኔዎች በመስጠትም ይታወቃሉ። አል ጄዚራን ጨምሮ ሌሎች ዓለም ዐቀፍ የመገናኛ ብዙኀን ላይ በመጻፍም ሆነ በቃል በመተንተን በይበልጥ ይታወቃሉ። ዕድገትና ውልደታቸው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በባሌ ዞን የሆኑት አወል፥ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የሕግ ትምህርት አጥንተዋል። ከግላስኮ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም አግኝተዋል። አወል በወቅታዊና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አዲስ ማለዳ፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደውን የሥልጣን ሽግግር ሂደት በአጠቃላይ እንዴት ያዩታል?
አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር)፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው የሥልጣን ሽግግር ሒደት በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ተከሰቱ ብዬ ከማስባቸው ፖለቲካዊ ለውጦች ወይም የሽግግር ሒደቶች ከነበረው ችግር አንጻር ሲታይ የተሻለ ለውጥ ነው። የነበርንበትን ሁኔታ ስታየውና አሁን ያለንበትን ስትመለከት እንደ ትልቅ ክስተት የሚቆጠር ለውጥ ነው ።
ባለፉት 27 ዓመታት ሥልጣን ላይ የነበረው ፓርቲ በምን ዓይነት ሁኔታ ሲመራ እንደነበር ይታወቃል። በሕዝባችን መካከል በጣም ሥር የሰደዱ ልዩነቶች፣ አለመግባባቶችና ጥላቻ ነበሩ። እነዚህ ነገሮች ሁላችንንም ወደ ጦርነት ሊያስገቡን ይችሉ ነበር፤ ወደ ጦርነት ሳንገባ አሁን ያለንበት ቦታ ላይ መገኘታችን በጣም ዕድኞች እንደሆንን ነው የማስበው። ለውጡ በጣም ሊበረታታ የሚገባ፣ ሊታገዝ የሚገባ ለሁላችንም ተስፋ የሚሠጥ ለውጥ አድርጌ ነው ያየሁት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብሔር ተኮር ግጭቶች መበራከት መፈናቀልንና የሰው ሕይወት መጥፋትን እያስከተሉ ሲሆን የአገር ደኅንነትና ሰላም አደጋ ላይ መውደቁን ማስተዋል ይቻላል። ተስፋ ያለውን ያህል የሰላም ማጣት ሥጋት ሆኗል። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አንድ ሥርዓት ከአንባገነን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚካሔድ የሽግግር ሒደት ተስፋና ሥጋት ሁል ጊዜ የማይነጣጠሉና አብረው የሚኖሩ ናቸው። ከዚህ በፊት በሽግግር ውስጥ ያለፉ አገራት ሁሉ በተወሰነ ደረጃ እነዚህን ኹለት ተቃራኒ የሆኑ ክስተቶችን አስተናግደዋል።
አንድ ምሳሌ ብንወስድ በርማ የምትባል አገር በሚገርም ሁኔታ በጣም ጠንካራ ከሆነ ወታደራዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተሸጋገረችበት ሁኔታ አይተናል። ይሁንና በዛው ሽግግር ሒደት ውስጥ ግን ሕዳጣን በሆኑት ሮሂንጋ ላይ ምን ዓይነት እልቂትና ጭፍጨፋ የተደረገበት ሁኔታ ነበር። መካከለኛው አፍሪካን ብንወስድ ወደ ሽግግር ለመሄድ ሞክረው ወደ ኋላ የተመለሱበት ሁኔታ እናገኛለን። ግብጽን ብንወስድ ምርጫ ተደርጎ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በሕዝብ ከተመረጠ በኋላ እንዴት ወደ ኋላ እንደተመለሱ አይተናል። ሊቢያም ላይ የተሞከረው ለውጥ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተጠናቀቀ አይተናል።
የሽግግር ሒደት በእነዚህ ኹለት ተስፋና ሥጋት መካከል የተተከለ ነው፥ እነዚህን ኹለት ክስተቶችም በእኩልነት ያስተናግዳል። ይህም የሚሆንበት ምክንያት በጨቋኝ ወይም አንባገነን ሥርዓት ስር ታፍነው(ታምቀው) የቆዩ የሕዝብ አስተያየቶች በዚህ ወቅት ይፈነዳሉ። ሁሉም ሰው የፈለገውን ነገር ያወራል፣ የፈለገውን ይናገራል፥ በእውነትም በውሸትም ያመነባቸውን ነገሮች እውነት አድርጎ ይነሳል። የለውጥ ጊዜ ስለሆነ የተደራጀውም ቡድን ራሱን የተሻለ ሥልጣን ለማግኘት፣ በተሻለ ለመጥቀም የሚያደርገው ስትራቴጂያዊ እንቅስቃሴዎችም አሉ።
አገሪቷ ደግሞ እነዚህ ለውጦች ሲፈጠሩ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ የሕዝብን አስተያየቶች ሲናኙ በፊት የነበረው ቁጥጥር እየላላ፣ እየሳሳ ይሄዳል። እየሳሳ መሄድ ብቻ አይደለም እነዚህን ሁሉም የራሱን አመለካከት፣ ጥቅም ለማስከበር የሚገፋውን የፖለቲካ አመለካከት አዎንታዊ በሆነ መልኩ አዋህዶ ገንቢ ወደሆነ አቅጣጫ የመምራት አቅም አይኖረውም ምክንያቱም የመንግሥት ተቋማት ዴሞክራሲያዊ በሆኑ መልኩ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ስላልተገነቡ ነው። ስለዚህ ነው ትክክለኛ የሆነ ችግር አለ። አብዛኛው እኔ አሁን በሕዝባችን ላይ የማየው ሥጋት መኖሩን ልክ ነው ይሁንና በጣም የተጋጋነነ ነው። ያለንበትን ወቅት ክስተት ካለመረዳት የሚመነጭ ይመስለኛል። የሽግግር ጊዜ ሁል ጊዜ ፈታኝ፣ ሊፈነዳ የደረሰ የሚመስል ሁኔታ የሚስተዋልበት ነው። ስለዚህ ያለንበትን ወቅት መረዳት ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ ሲታይ የመሻገር ዕድላችን ትልቅ ነው፤ ይሁንና ሥጋቱም እንደዚሁ ትልቅ መሆኑን ማሰብ ይገባናል።
ከሥጋቱ ጋር በተያያዘ በኦነግና በመንግሥት መካከል ያለው ፍጥጫና ግጭት እየጋመ ያለበት ሁኔታ አለ። የግጭቱን መንስዔ እርስዎ እንዴት ተረዱት?
ይሔ ነገር በአብዛኛው የሚመለሰው በኹለቱ መካከል ወደ ነበረው ስምምነት ነው። ‘ምን ነበር የተስማሙት?’ የሚለው ነው። ከመንግሥት የሰማነው ማንኛውም ወደ አገር ቤት የተመለሰ ድርጅት መሣሪያ ታጥቆ ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ሕገ መንግሥታዊ ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ተስማምቶ ነው የሚል ነው። ስለ ስምምነቱ ማስረጃ እንኳን ባናይ እንደዛ ዓይነት ተግባቦት ላይ እንደደረሱ ታሳቢ መደረግ አለበት የሚለውን እወስዳለሁ። ምክንያቱም ማንም መንግሥት ማናኛውም ኃይል ታጥቆ አገር ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ይፈቅዳል ብዬ ስለማላስብ ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ ስምምነቱ ምን እንደሚል ያየሁት ነገር የለም። ለሕዝብም የተገለጸ ነገር የለም። ከስምምነቱ አንጻር መንግሥት የሰጠው ምንድን ነው? ያልሰጠውስ? የሚለውን አላውቅም። ነገር ግን ዋናው የመርሕ ጉዳይ ነው የሚመስለኝ። አንድ ቅቡልነት ያለው ወይም የሌለው(‹ዲ ፍክቶ›) መንግሥት ያለበት አገር ላይ ኃይል የመጠቀም ሥልጣን ያለው ብቸኛ አካል መንግሥት ነው። ከመንግሥት ውጪ ሌላ ኃይል ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ግጭት የማይቀር ነው።
ስለዚህ ትልቁ ችግር የሚመስለኝ ከመንግሥት ውጪ ያለ የፖለቲካ ፓርቲ ታጥቆ መንቀሳቀስ ችግር አድርጌ ነው የምወስደው።
ግጭቱን ለዘለቄታው ለመፍታት በተግባር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
እነዚህ ኹለት አካላት በአስቸኳይ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ አለባቸው፤ ከመንግሥት ውጪ ታጥቆ መንቀሳቀስ የሚችል ኃይል መኖር የለበትም። ያ ካልሆነ ግን ከመንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋርም ወደ ጥል የሚገባበት፣ የሰው ልጅ ሕይወትና ንብረት አደጋ ላይ የሚወድቅበት ዕድል በጣም ሰፊ ነው። ይሄ ደግሞ በጭራሽ አስፈላጊ ነገር አይደለም። አሁን የምናየው ነገር ከዛ ጋር የተያያዘ ነው። ወደ ጦርነት መግባት በፍፁም አስፈላጊ አልነበረም።
እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በፖለቲካዊ መፍትሔ ጭምር እንጂ በጦርነት ብቻ የሚፈቱ አይደሉም። ነገር ግን ግጭት ካለና መንግሥት እንደመንግሥት አንድ ቦታ ላይ መንቀሳቀስ ካልቻለ ኃይል መጠቀሙ የማይቀር ነገር ነው። ሰዎች የሚገደሉ፣ ንብረት የሚጠፋ ከሆነ ወደ ግጭት መሄዱ አይቀሬ ነው።
ትልቁ መፈታት አለበት ብዬ የማስበው የኦነግ ሸኔ ቡድን በሕገ መንግሥቱ ዓውድ የሚፈልጉት ነገር እና ዴሞክራሲያዊ ለሆነ ምርጫ የሚዘጋጁበት ሁኔታ ተፈጥሮ ኹለቱም ስምምነት ላይ ደርሰው ምርጫና ምርጫ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ የሚገባበት ሁኔታ መፈጠር መቻል አለበት። የፖለቲካ ፓርቲ ሥራ መንግሥትን መቃወም ነው። ውጤታማ የሚሆነው ግን ፓርላማ ሲገባ ነው።
መንግሥት የኦነግ ሸኔ ቡድን የሚጠይቀውን ጥያቄ በተቻለ መልኩ ማስተናገድ መቻል አለበት። ነገር ግን ኦነግም በዛው መጠን የትጥቅ ትግል አካሂዳለሁ የሚለውን አላስፈላጊ ዋጋ የሚያስከፍል፣ ሕዝቡን የሚጎዳ እንቅስቃሴ ትቶ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ራሱን ማደራጀትና ወደ ምርጫ ዝግጅት መግባት አለበት። ይህ ካልሆነ አሁን ከመንግሥት ጋር በጦር ሜዳ አሸነፎ ሥልጣን ሊያዝ የሚቻልበት ሁኔታ እኔ አይታየኝም። መሆንም አይችልም፤ መሆንም የለበትም።
ዞሮ ዞሮ ትልቅ ዋጋ የሚከፍለው ሕዝብ ነው። ለሕዝብ እታገላለሁ የሚል ማንኛውም ቡድን በዚህ ሰዓት ይህቺን አገር ወደ ጦርነት ማምራት በጣም ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው እላለሁ።
የኦሮሞ የፖለቲካ ታሪክ ትርክት በተለምዶ ኢትዮጵያዊነት ከሚሉት የፖለቲካ ታሪክ ትርክቶች ጋር ይጋጫሉ። የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?
ታሪክ ከኃይል ጋር፣ ታሪክ ከሥልጣን ጋር የሚለያይ አይደለም። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የታሪክ ጸሐፍት ከመንግሥታዊ ሥርዓት ጋር ቁርኝነት አላቸው። በአብዛኛው እውነተኛ የሆነን ታሪክ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ታሪክን ለሥርዓቱ በሚመች መልኩ መፃፍ ነው። ይሔ እንግዲህ የቆየውን የአገራችንን ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዚህ አሁን በነበርንበት መንግሥት ሥርዓት ውስጥም የነበረውን ሁኔታ በግልጽ ያሳያል። አብዛኞቹ ጸሐፍት በመንግሥት የሚደረግባቸው ጫና አለ። ለመንግሥት የሚሰሩም ጸሐፍት አሉ። ለመንግሥት የሚሰሩ ባይሆኑም ገለልተኛ የምትላቸው አንዳንድ የታሪክ ሁነቶችን በትክክል የማያሰፍሩበት ሁኔታ አለ። እነዚህ ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የታሪክና ሥልጣን ቁርኝት የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የተጻፈው የኢትዮጵያን ብዙኀን የሆኑ ሕዝቦች ማንነት፣ የደረሰባቸውን ችግር፣ የሚያስቀምጥ አይደለም። በጣም በተመረጠ መልኩ ነው የተጻፈው።
በሌላ በኩል በኦሮሞ ጸሐፍትና ታሪክ አጥኚዎች በኩልም የተጻፉት ጽሑፎች የኢትዮጵያን ታሪክ፣ መንግሥት የሚያዩበት ዓይን (መነጽር) አለ። ይህ መነጽር ከራሳቸው ልምድ አንጻር ነው። በራስ ዕይታ የሚጻፍ ነገር ደግሞ ሁል ጊዜ የተሳሳተ ነው ማለት ባይችልም አንዳንዴ ለፖለቲካ ጉዳዮች የሚሰጡት ትንታኔዎች ከዛ ሕዝብ ችግር፣ ሥቃይ፣ ተመክሮ፣ መረዳት ተነስቶ ነው።
ታሪክ ትርክቶች ከሥልጣን እና ከኃይል ጋር በጣም ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። ከዚሀ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሥልጣን ጋር በተያያዘ በተቃራኒ መልኩ ሲታገሉ የቆዩ ሕዝቦች በተለይም ኦሮሞና አማራን መውሰድ ይቻላል። በአብዛኛው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት በአማራና በአማራኛ ቋንቋ ቅርጽ እንድትይዝ ተደርጓል። የዚህ ትርክት መሠረቱ ከሥልጣን ጋር ተያያዥ መሆኑ ነው።
ትርክት በምልበት ጊዜ ውሸት ነው ማለቴ አይደልም። በተመሳሳይም እውነት ነው ማለትም አይደለም። ግለሰቦች አንድ የሆነ አመለካከትን አንድ ቀን ስለሰሙ ብቻ አይደለም የሚያምኑት፣ ራሳቸው የሚያጋጥማቸውን ነገር ከሚፈልጉት ሥልጣን ጋር፣ ሊደርሱበት ከሚፈልጉት ቦታ ጋር እያዋዙ ሲያስቀምጡ እነዚህ ትርክቶች የሆነ ዕውነታን ለማግኘት እያደጉ ይመጣሉ። አብዛኛው ልዩነት ከዚህ የሚመነጭ ይመስለኛል።
እነዚህ ልዩነቶች ጫፍ ደርሰው ለአገር ኅልውና አደጋ ሊሆኑ አይችሉም?
በርግጥም ለአገር ኅልውና አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የማንነት ፖለቲካ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ባገኘበት አገር እነዚህ የማንነት ፖለቲካ አንተ እንዳልከው በጣም ጫፍ ደርሰው የጋራ ራዕይ በሌለበት ሁሉም ለራሱ ብቻ ሥልጣን ይገባኛል ወይም ደግሞ ወደ ሥልጣን ሊያደርሰኝ የሚችለው ይሄ ነው ብሎ የረጅም ጊዜ ግብ ሳይያዝ የሚደረግ ከሆነ ትልቅ ሥጋት ሊሆን ይችላል።
አንድ ዓይነት የትግል ዘዴን የተወሰነ የትግል ምዕራፍን ለማለፍ ከተጠቀምክ ያንን ምዕራፍ ደግሞ አገር ለመገንባት የሚያስፈልገው ስትራቴጂ እንድንጠቀም ማተኮር ይኖርብናል። ከዛሬ 10 ወራት በፊት የመታገያ ዘዴዎች ዛሬም የምንጠቀምባቸው ከሆነ ትግል ላይ አይደለንም፤ በግብታዊነት እየተንቀሳቀስን ነው ማለት ነው።
ኅብረተሰባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲመጣ የምንፈልግ ከሆነ የተለያዩ የትግል ደረጃዎችና ስልቶችን መጠቀም ያስፈልጋል።
አምባገነን ሥርዓትን ለማፍረስ የተጠቀምክበትን ሥልት ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመገንባት ልትጠቀምበት አትችልም። አሁን ትርክቶች ገንቢ መሆን መቻል አለባቸው። ተዋስኦው መልሶ ገንቢ መሆን መቻል አለበት። ዝም ብሎ አፍራሽ መሆን አይደለም። እንደ ግለሰብም እንደተቋምም መለወጥ ያስፈልጋል። አተያያችን ከድሮው አቅጣጫ ትንሽ ዞር ማለትና ገንቢ ወደሆነ አቅጣጫ ማየት መቻል አለበት።
አሁን ትልቁ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ከዚህ በፊት ተጎዳሁ የሚለው አካል ያስብ የነበረው ስለጉዳቱ ስለነበረ ከዛ አመለካከት መውጣት አልቻለም፤ አሁን ቅርብ ጊዜም ሥልጣን አጣሁ የሚለው አካል ደግሞ ተመልሶ እዛው ተጎዳሁ የሚለው አመለካከት ውስጥ ገብቷል።
በሄድክበት አቅጣጫ ሁሉ የምታገኘው የተጎዳ ሕዝብን ነው። ሁሉም ተጎጂ ነኝ በሚልበት ወቅት አጓጊ፣ ቆራጥ የሆነ መጪውን አመልካች የሆነ ርዕይ ለማየት ያስቸግራል። ርዕዩ በሕዝቡ ተቀባይነት የማኖረው ከሆነ ብዙ ርቀት ላይሄድ ይችላል።
ስለዚህ እንዴት ነው ከለመድነው አዙሪት ወጥተን ገንቢ በሆነ መልኩ ልናስኬደው የምንችለው የሚለው ነው ዋና ነገር።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በተካሄደው ‘የወጣቶች ሚና በኢትየጵያ’ በሚል የውይይት መድረክ ላይ ባቀረቡት ንግግር ከዚህ ቀደም “አፍራሽ” የሆኑ (ዲኮንስትራክቲንግ) ሥራዎች ስንሠራ ነበር፤ አሁን ደግሞ አስፈላጊው ለውጥ ስለመጣ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ የሚገነባልንን መልሶ ገንቢ (ሪኮንስርታክቲቭ) ትርክት እና ሥራዎችን መሥራት አለብን ብለዋል። ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
በዝግጅቱ ላይ ስለኹለት ነገሮች ነው ያወራሁት። አንደኛ በትርክት ደረጃ ከዚህ በፊት ታሪክ ስናወራበት የነበረው ሁኔታ ቅርጽ እንዲይዝ የተደረገው ሕዝብን ለመቀስቀስና ለማሰባብብ በሚመች መልኩ ነው። አንባገነን ሥርዓቱን ለማፍረስ ሕዝቡን የምታንቀሳቅስበት መንገድና በሽግግር ውስጥ ሆነህ ሕዝብን ለገንቢ ሥራ የምትቀሰቅስበት ሁኔታ አንድ ሊሆን አይችልም።
ከተጎድቻለሁ መንፈስ ወጥተን ተስፋን በሚሰንቅና ድፍረት በተሞላበት አመለካከት አገርን መገንባት እንችላለን። የድሮው ነገር አይመለስም በሚል በራስ መተማመን መሥራት የሚያስችል መልሶ ገንቢ ተዋስኦ ያስፈልገናል። ይሄ ተዋስኦም የግለሰቦችን አመለካከት እንደገና የሚያድስ መሆን መቻል አለበት።
ስለዚህ ቀደም ብዬ ከተናከርኩት ጋር በመሠረቱ የሚጋጭ አይደለም። እርስ በርሱ የሚደጋገፍ ነው።
ስለወጣቱ ብዙ ተብሏል፥ አመጽን ዒላማ አድርጎ መጣቶችን እያደራጀና እየቀሰቀሰ የነበረው ልኂቅ ተሳትፎ ምን መሆን ይገባዋል?
‘ልኂቅ ማነው? ወጣት ማነው?’ የሚለው ብዙ አከራካሪ ናቸው። ሕዝብን ከማደራጀት፣ ከማንቀሳቀስ፣ ሐሳብን ከማፍለቅ፣ ትንታኔዎችን ከመስጠት አንጻር ልኂቃን፣ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት፣ ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል።
በጣም ተስፋ የሚሰጥ ለውጥ ከተገኘ በኋላ በማይሆኑ ነገሮች ወዳልሆነ አቅጣጫ መሄድ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። ‘ሁላችንም ኃላፊነታችን ምንድን ነው?’ የሚለውን ማየት አለብን። ለእኔ ከሁሉም የሚበልጠው ትልቁ ኃላፊነት ይህንን ሽግግር ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ ደግፈን ማሸጋገር መቻል ነው።
ሽግግር ብዙ ደረጃዎች አሉት። ሥርዓቱንም በተወሰነ ደረጃ በመክፈት ይህንን ደረጃ ማለፍ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ይህንን አልፈን ተቋማትን ወደ መገንባት ስንሄድ አሁን የምናየውን ሥርዓት አልበኝነትና ግጭቶች ተወግደው የፖለቲካ ሥርዓቱን በመቀበል መጠቀም መቻል ይገባል፤ ተቋማትን ለመገንባት እንቅስቃሴ ማድረግ አለብን። ተቋማትን መገንባት መንግሥት ብቻ የሚሠራው ነገር አይደለም። ሕዝቡም መረዳትና ማገዝ ያለበት ጉዳይ ነው። እነዚህ ሒደቶች ላይ ልኂቁ ሐሳብ በማፍለቅ፣ የሚነሱ ሐሳቦችንና የሚወሰዱ እርምጃዎችን በፖሊሲ ደረጃ ማገዝ ይገባዋል። ለምሳሌ መንግሥት በበቂ ጥናት ያልተደገፉ ትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ይዞ በሚንቀሳቃስበት ጊዜ ጉድለቱን መጠቆም መቻል አለበት። ስለዚህ ከልኂቁ የሚጠበቀው ኃላፊነት በጣም ትልቅ ነው። ዝርዝሩ ግን ብዙ ነገር ሊሆን ይችላል።
የኢትዮጵያን የውጪ ግንኙነት ፖሊሲስ እንዴት ይገመግሙታል?
ኢትዮጵያ ግልጽና ወጥ የሆነ የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ያላት አይመስለኝም። በተግባር ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተደረጉትን አንዳንድ ነገሮች ስመለከት ግን አገሪቷ ጠቃሚ የሆኑ እርምጃዎችን ወስዳለች።
አንዳንድ ጊዜ ቆም ብለህ ‘ይሔ ነገር ወዴት ነው የሚያመራው ? ምን ማለት ነው?’ ብለህ ብዙ ሐሳብ ልታነሳ የምትችልበት ጉዳዮች አሉ። የውጪ ግንኙነት ፖሊሲን በተመለከተ ግልጽ የሆነ የተጻፈ ነገር ስለሌለ ትንሽ ግልጽነት የሚጎድልበት ሁኔታ አለ።
ለእኔ አሁንም ሽግግር ላይ ስለሆንን ፖሊሲ ለማውጣት ጊዜ አልነበረም፤ የተወሰዱ እርምጃዎችን ግን አዎንታዊ አድርጌ ነው የምወስደው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እስቲ የኢትዮጵያና አፍሪካ ቀንድ አገራት ግንኙነት ምን ይመስላል?
በአፍሪካ ቀንድ ላይ ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለችው በጣም የሚያበረታታ ነው። ይህንን ቀጣና በምጣኔ ሀብት ማስተሳሰር ከማንም በላይ ኢትዮጵያን ይጠቅማል። ኢትዮጵያ የባሕር ወደብ የሌላት አገር ነች። ባለፉት 18 ዓመታት ከ97 በመቶ በላይ የሚሆነውን ከውጪ የምናስገባው ዕቃ መድኃኒትን እና ከአገር ደኅንነት ጋር የተያያዙትን ጨምሮ በጅቡቲ ነው የምናስገባው። ይህም ትልቅ የሆነ የደኅንነት ሥጋት ምንጭ ነው።
በቀጣናው ብዙ ኃያላን የወታደራዊ ሠፈር አላቸው። እዛ አገር [ጅቡቲ] ላይ አንድ ችግር ቢፈጠር ለኢትዮጵያ የሥጋት ምንጭ ነው።
ኢትዮጵያ የወደብ ተደራሽን ማስፋት ከቻለች ይሄ ትልቅ ስትራቴጂያዊ ድል ነው ብዬ እወስደዋለሁ። ከዛም ባለፈ አገራቱ በኢኮኖሚ ቢተሳሰሩ ጥሩ ውጤት ያመጣል። ሁሉም አገሮች ምጣኔ ሀብታዊ ድርሻ ካላቸው አንዱ አገር ከሌላው አገር ጋር ያለው ግንኙነት በራሱ ግጭቶችን የመቀነስ ትልቅ ዕድል አለው። በኢትዮጵያ በኩል እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎችን በአዎንታዊነት ነው የምወስዳቸው።
ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ያሉ ግንኙነቶችን በተመለከተ ኢትዮጵያ ብልሃት የተሞላበት ግንኙነት ነው እያደረገች ያለችው፤ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ሁኔታ ከግምት ያስገባና ለራሷ በሚመች ሁኔታ ዕድሉ ለመጠቀም እየሞከረች ይመስለኛል።
በአጠቃላይ በእኔ ምልከታ እስካሁን ኢትዮጵያ የወሰደቻቸው አዎንታዊ የሆኑ ተግባራዊ እርምጃዎች እንደሆኑ ነው የማስበው። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ቦታ ላይ ያለ አገር የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ሊኖረው ይገባል። ከፖሊሲ አንጻር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መኖራቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን በዝርዝር ምን እንደሆኑ አላውቅም።
በቅርቡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ሰላም አውርዳለች። የኹለቱ አገራት ግንኙነት እስከምን ደረጃ የሚደርስ ይመስሎታል?
የኹለቱ አገራት ግንኙነት አሁን ባለው መልኩ መሻሻሉን ከነበሩበት የጠላትነት ስሜት፣ ካስከተለው የሰብዓዊ ጥፋት እንዲሁም አለመግባባቱን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ያገለግል እንደነበረ ስታውቀው የነበረው ልዩነት በዚህ መልኩ መፈታቱ ለኹለትም አገራት ትልቅ ድል ነው ብዬ ነው የማስበው። መጀመሪያም መፈጠር አልነበረበትም።
ወደፊት ምን ሊፈጠር ይችላል?
ከጦርነት ማንም የሚጠቀም እንደሌለ አይተናል። በኹለቱ አገራት መካከል አሁን ለጦርነት የሚያመች ሁኔታ የለም። ይህንን ቋሚ በሆነ መልኩ መቀየር እንኳን ባንችል ቢያንስ በቅርቡ ወደ ጦርነት የሚወስድ ሁኔታ ያለ አይመስለኝም።
ከሕዳሴው ግድብ መጓተት፣ የአገር ውስጥ ሰላም መታጣት ለግብጽ ‘ሰርግና ምለሽ’ እንደሆነላት አንዳንዶች ይናገራሉ። በኢትዮጵያ የውስጥ ሰላም ማጣትስ የግብጽ እጅ ይኖርበታል ብለው ያምናሉ?
አያስቡም ብሎ [ግብጾች] መገመት ጥሩ አይሆንም። ከግብጽ ጋር የመልከዓ ምድራዊ ፖለቲካ ተቀናቃኞች ነን። ስለዚህ ሁል ጊዜ መጠራጠር አስፈላጊ ነው። እንደ አገር ደግሞ መውሰድ የሚገባንን ጥንቃቄ መውሰድ ይኖርበናል። ሁል ጊዜ በተጠንቀቅ ላይ መሆን አለብን። በተለይ ትልልቅ የሆኑ የመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የመልከዓ ምድራዊ ፖለቲካ ልዩነት ካለ ማለት ነው። ይህንን ፕሮጀክት አሻጥር አይሞከርበትም ብሎ ማሰብ ተገቢ አይሆንም። ኢትዮጵያ በተቻላት አቅም የግብጽን ውሃ ላለመጉዳት ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ ሁኔታ ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ሁኔታ መፈጠር ያስፈልጋታል። ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን የራሷን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ድርድር ውስጥ መግባት የለባትም፥ ሉዓላዊ መብታችን ስለሆነ። ከዛ ባለፈ አገሪቷ እንድትበጣበጥና ፕሮጀክቱም እንዲቋጥ ምን ያህል እየሰሩ ነው ለሚባለው ምንም ማስረጃ የለኝም። እንደ አንድ ተራማጅ አገር ግን ሁልጊዜ ነቅተን መጠበቅ ይገባናል፤ ይሄ የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ጉዳይ ስለሆነ ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል።
የውጪ አገር ዜግነት ያለቸው ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ስለእኔ ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነው የውጪ ፓስፖርት የያዙ ሰዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ወይም አለመሳተፍ አለባቸው ለሚለው አሁን ያለው ሕግ መሳተፍ እንደማይችሉ ነው የሚያስቀምጠው። የሽግግር ጊዜ ላይ ስለሆንን መንግሥት በሆደ ሰፊነት እንዲሁም አብዛኞቹ ተገደው፣ ተገፍተው ወይም በማኅበራዊ ችግር ፓስርታቸውን የቀየሩ በመሆናቸው አሁን ባለንበት ሁኔታ በፖለቲካው እንዲሳተፉ መፍቀድ ለምንፈገው ሽግግር አስፈላጊ ይመስለኛል። አዎንታዊም አበርክቶ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ።
ይሁንና የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጥምር ዜግነትን አይፈቅድም። ስለዚህ የሌላ አገር ዜግነት ስትይዝ ወዲያውኑ የኢትዮጵያዊ ዜግነትህን ታጣለህ።
አሁን ባለበት ሁኔታ ሕግ መቀየሩና እነሱን በፖለቲካ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ ማስቻል ምን ዓይነት አዎንታዊ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል እርግጠኛ አይደለሁም። አንዳንድ አሉታዊ የሆኑ ነገሮች ግን ይታየኛል። አፋኝ መንግሥት ባለበት አገር የውጪ ዜጋ ስትሆንና ኹለተኛ አገር ሲኖርህ አደጋውን ተቋቁሞ ከመታገል ቲኬት ቆርጦ ወደ ሌላኛው አገሩ የሚመለስ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ ጥምር ዜግነት ማሰቡ ጠቀሜታ ያለው ይመስለኛል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ጉዳዩ ቢያድር ይሻላል።
በስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ አዋጅ በውይይት ላይ ይገኛል። ረቂቁ ለስደተኞች እስከ ዜግነት መስጠት መብት አካቷል። የረቂቁ አዋጅ መጽደቅ ያለው አንድምታ ምንድን ነው? (አዋጁ ሐሙስ፣ ጥር 9 ጸድቋል)
ረቂቅ ሕጉን አላየሁትም። ምናልባት አንተ እንደምትለው ረቂቅ ሕጉ ስደስተኞች እዚህ አገር በስደተኝነት መጥተው፣ የስደተኝነት ዕውቅና ተሰጥቷቸው፣ እዚህ አገር የተወሰነ ጊዜ ኖረው፣ ለዚህ አገር ምጣኔ ሀብታዊና ለባሕላችን አስተዋጽኦ አድርገው በሒደት ወደ ዜግነት የሚቀየሩበት ሁኔታ የሚያመቻች ሕግ ከሆነ ይሄ በጣም ጥሩ ነገር ነው፥ የሚያሳየውም ተራማጅ አገር መሆናችንን ነው።
እኛ እንደስደተኛ ሰው አገር ኖረን፣ ስደተኝነት መብት ተሰጥቶን፣ ከለላ ተሰጥቶን አገራችን መርዳት ችለናል። ለምሳሌ ኢትየጵያ ትልቅ የውጪ ምንዛሬ የምታገኝበት አንዱ ምንጭ ሐዋላ ነው፥ በሕጋዊ መንገድ በባንክ በሚተላለፍ በዓመት እስከ 4 ቢሊዮን ዶላር ድረስ እንደምታገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ስለሆነም ከዚህ ሒደት እንደተጠቀመ ሕዝብ ልክ እንደኛ የተቸገረና በፖለቲካ ወይም ማኅበራዊ ጉዳይ አገሩ መኖር ያልቻለ ግለሰብ እኛ አገር መጥቶ መኖር የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር በጣም አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የሞራልም ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here