በዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ውስጥ ባርነትም ይሁን “ዘመናዊ ባርነት” ተቀባይነት የላቸውም። “ዘመናዊ ባርነት” በጥቅሉ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ በተለይ ደግሞ ሕገ ወጥ የሕፃናት ዝውውር እና የወሲብ ዝውውር (‘ሴክስ ትራፊኪንግ’) ይመለከታል።
በኢትዮጵያ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። ዩኤንኤድስ እ.አ.አ. በ2016 ባወጣው መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ 19,305 የሚገመቱ በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች አሉ። ‘የግሎባል ስሌቨሪ ኢንዴክስ’ እ.አ.አ. በ2018 ባወጣው ሪፖርቱ ኢትዮጵያ “በዘመናዊ ባርነት” ከ167 የዓለማችን አገራት 52ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በወሲብ ባርነት ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በጥቅሉ 614 ሺሕ ዜጎች ገደማ “ዘመናዊ ባርነት” በሚባል ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ሪፖርቱ ይናገራል። ይህም ማለት ከአንድ ሺሕ ሰዎች 6.5ቱ ገደማ “ዘመናዊ ባሮች” ሆነዋል ማለት ነው።
ሴት የወሲብ ንግድ ሠራተኞችን ቀጥረው ደንበኞችን ለመሳብ የሚሞክሩ ቡና ቤቶች እና የዕርቃን ዳንስ ቤቶች በአገሪቱ፣ በተለይም ደግሞ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እየተበራከቱ ነው። እነዚህ በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶች ከደላላ ጀምሮ የቡና ቤት ባለቤቶች ድረስ በተለያየ መንገድ “ዘመናዊ ባርነት” ይጭኑባቸዋል። በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩት ሴቶች ከቀጣሪያቸው ቡና ቤት ውጪ ሌላ ቦታ ለመሔድ ሲፈልጉ ለቡና ቤቱ “ቀረጥ” ከመክፈል ጀምሮ የተለያዩ እርከኖች ያሏቸውን የወሲብ ንግድ አገልግሎቶችን እየሰጡ ያንን ለዕርቃን ዳንስ ቤቱ ወይም ደግሞ ቡና ቤቱ እንዲያካፍሉ እስከ መገደድ ድረስ የዘለቀ “ዘመናዊ ባርነት” ውስጥ ተዘፍቀዋል።
በኢትዮጵያ፣ ምንም እንኳን የወሲብ ንግድ በሕገ ወጥነት ባይፈረጅም፣ የወሲብ ንግድ ሠራተኞችን መቅጠር ግን ተከልክሏል። በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 634 ላይ እንደተመለከተው “የሌላን ሰው የዝሙት ድርጊት የዘወትር መጠቀሚያ ማድረግ” የተከለከለ ነው፤ በወንጀልም ያስቀጣል። በተለይም ደግሞ በአንቀፅ 636/ሐ እንደተደነገገው፣ “ወንጀለኛው ድርጊቱን የፈፀመው የተበዳዩን የገንዘብ ችግር ወይም የኅሊና ሐዘን ወይም በዚህ ሰው ላይ ያለውን የጠባቂነት፣ የአሠሪነት፣ የአስተማሪነት፣ የአከራይነት ወይም የአበዳሪነት ወይም ይህን የመሰለውን ሌላ ሥልጣኑን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ፤ (…) ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ ዐሥር ዓመት ለመድረስ የሚችል ፅኑ እስራትና ከሃያ ሺሕ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል።”
በኢትዮጵያ በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሰዎች (በተለይም ሴቶች) ለዚህ ሥራ የሚዳረጉት በገንዘብ እጦት ወይም ችግር እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያስገነዝባሉ። ስለሆነም ቡና ቤቶቹ እና የዕርቃን ዳንስ ቤቶቹ እነዚህን ችግረኛ ሴቶች መጠቀሚያ እያደረጓቸው መሆኑ በኢትዮጵያ የሕግ ዓይንም ቢሆን ድርጊቱ “ዘመናዊ ባርነት” ሊባል ይችላል።
ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011