አዲስ አበባ አውጥታ ልትተፋቸው የማትችላቸውን የጎዳና አዳሪዎች መንገድ ላይ እንዳይታዩባት ከምትሸሽግባቸው ጊዜያት አንዱ የአፍሪክ ኅብረት የመሪዎቸ ጉባኤ ነው። ይህ ተግባሯ በነዋሪው ዘንድ ብዙ ትችት ቢያሰነዝርባትም የአዲስ አበባ አስተዳደር ግን ‹‹ገጽታዬ ይበላሽብኛል›› በሚል የኅብረቱ አባል አገራት መሪዎቸ ከቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ኅብረቱ አዳራሽ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የጎዳና አዳሪን እንዳያዩ ማረፊያ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን በፖሊስ ኃይል በግድ ወደ ሌላ ስፍራ እንዲርቁ ሲያደርግ ይስተዋላል። ዳሩ ግን ስብሰባው አልቆ መሪዎቹ ወደ የመጡበት ሲመለሱ በግድ እንዲደበቁ የተደረጉት ጎዳና አዳሪዎችም ወደለመዱት መስመር ይመለሳሉ።
አፍሪካ ኅብረት ለምን?
ቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይባል የነበረውና በግንቦት 1955 የተመሰረተው የአፍሪካ አገራት ጥምረት በምዕራባውያኑ ግዞት ስር የነበሩ አፍሪካውያን የቅኝ ግዛት ቀንበርን ፈልቅቀው እንዲወጡ ብርታት በመሆን ረገድ ብዙ ስለማበርከቱ ይወሳለታል።
‹‹Understanding Eritrea: Inside Africa’s Most Repressive State›› በሚለው መጽሐፋቸው የሚታወቁትና የአፍሪካን ቀንድ ፖለቲካ የተመራመሩበት ማርቲን ፕላውት ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት ከሆነ ድርጅት በነበረ ጊዜ በቅኝ ግዛትና በአፓርታይድ ትግል ያመጣውን ያክል ለውጥ ኅብረቱ ማምጣት አልቻለም። ኅብረቱ መለካት ያለበት ለአፍሪካውያን ዋስትና ሆኗል ወይ፣ በምጣኔ ሀብትና ባሕልም ሕይወታቸውን አበልጽጎታል ወይ እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ መድረክስ ወክሏቸዋል ወይ በሚሉት መመዘኛዎቸ ሊሆን እንደሚገባ ያነሱት ማርቲን ‹‹ሁሉም የራሱ አስተያየት ሊኖረው ይችላል፤ እንደኔ ግን ኅብረቱ ውድቀት ገጥሞታል›› ይላሉ።
በድርጅት የጀመረው የአፍሪካውያን ቅርርብ በመስከረም 1992 ወደ አፍሪካ ኅብረትነት እንዲያድግ ተወስኖ ይህም በሐምሌ 1994ቱ የደርባን ጉባኤ አንድ ብሎ መጀመሩ ይታወሳል። አጀንዳ ያደረገውም የአፍሪካውያንን የመቀናጀትና መተባባር ሒደት በማጠንከር አህጉሩ በዓለም ዐቀፍ የምጣኔ ሀብት መድረክ ቁልፍ ሚና እንዲኖረው ማስቻልን ነው። የአህጉሩን ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እልባት መቸርም የኅብረቱ ዋነኛ የመመስረቻ ግብ ከሚባሉት ማከከል ይጠቀሳል። የኅብረቱ ራዕይም ‹‹በራሱ ዜጎች የመጣና በዐለም ዐቀፍ ደረጃ ብርቱ ኃይል የሚኖረው የተዋሐደና የበለጸገ ሰላማዊ አፍሪካን ማየት›› እንደሆነ ያትታል።
ኅብረቱ መሠረታዊ ዓላማዎቼ ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል በአህጉሩ ፖለቲካዊ እና ማኅበረ ምጣኔ ሀብታዊ ውኅደትን ማላቅ፣ የተባበሩት መንግሥታትና ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዓለም ዐቀፍ ትብብርን ማሳደግ፣ በአህጉሩ ሰላም፣ ፀጥታና መረጋጋትን ማረጋገጥ፣ የዴሞክራሲ መርሆዎችንና ተቋማትን ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም ሕዝባዊ ተሳትፎንና መልካም አስተዳደርን ማበልጸግ የሚሉት ይገኙበታል። ኅብረቱን በእነዚህ የተመረጡ ዓላዎቹ ለክተው ትንተና የሚሰጡ ወገኖች አፍሪካ ኅብረት የዓላማውን ያህል ስላለመጓዙ ብዙ አብነቶችን ያነሳሉ።
ኅብረቱና ዴሞክራሲ
ማርቲን፣ የኡጋንዳው ፕሬዘዳንት ዮሪ ሙሰቨኒ በ1968 (እ.ኤ.አ) ወደ ሥልጣን ሲመጡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአንባገነኖች ስብስብ ነው ብለው የነበረ ሲሆን የሚሳዝነው ግን ዛሬም የኅብረቱ አባል አገራት አብዛኞቹ መሪዎች አንባገነን እንደሆኑ መገኘታቸው ነው ሲሉ ትዝብታቸውን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል። ኅብረቱ የቅርቡን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኢፍትሓዊና ፀረ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ አካሄድ ጨምሮ ባላየ ማለፉን በመጥቀስም ኅብረቱ ዴሞክራሲን እያስመሰለ (እያሾፈበት) ነው ሲሉም ይተቻሉ።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማም ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባው የኅብረቱ አዳራሽ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ‹‹ዛሬ ላይ የአፍሪካ የዴሞክራሲ ሒደት የሥልጣን ጊዜያቸው ካበቃ በኋላም ሥልጣን መልቀቅን በሚቃወሙ መሪዎች ችግር ውስጥ ወድቋል›› ማለታቸው አይዘነጋም። ፕሬዘዳንቱ ማንም ሰው እድሜ ልኩን ፕሬዘዳንት ሊሆን እንደማችል በመጥቀስ ኅብረቱ ለአፍሪካውያን ዴሞክራሲ እድገት ሊታትር እንደሚገባ ነበር የመከሩት።
ኅብረቱ ስለዴሞክራሲ፣ ምርጫና መንግሥታዊ ሥልጣንን መለማመድ ሕገ መንግሥት (African charter on democracy, election and governance) በሚያትተው ሰነዱ አንቀጽ 14 እና 15 ዴሞክራሲን ለማበርታት የሚስችሉ ተቋማት ግንባታና ነፃ አድርጎ ማንቀሳቀስን በተመለከተ አባል አገራቱ ሊሰሩ እንደሚገባ ያሳስባል። ቀጣዮቹ አንቀጾችም ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የግድነት የሚያስገነዝቡ ሲሆን አንቀጽ 23 እና 25 ደግሞ ሕገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ መንግሥት ለመመስረትም ሆነ ሥልጣን ለመያዝ ጥረት ማድረግና ማገዝ ለኅብረቱ ምጣኔ ሃብታዊና ሌሎችም ማዕቀቦች እንደሚዳርግ በግልጽ አስፍሯል።
የአፍሪካ ኅብረት ከአፍሪካ አንድት ድርጅት ወደ ኅብረትነት ሲያድግ ተቋማዊ መዋቅሩን ከአውሮፓ ኅብረት ጋር እንዲመሳሰል በማድረግም ጭምር አህጉሩን የሰላምና ብልጽግና አናት አደርጋልሁ በሚል ህልም መሆኑን የሚያሰታውሱት የሉላዊነት ማዕከል ባልደረባ ፍራንክሊን ሊስክ (ፕሮፌሰር) የኅብረቱን 10 ዓመታት ስኬትና ተግዳሮት ይዘረዝራሉ። እንደሳቸው ማብራሪያ ኅብረቱ ድርጅት በነበረ ወቅት በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትን ይመርጥ የነበረው መርህ በኅብረቱ ማቋቋሚያ ላይ ዴሞክራሲን ለማበርታታትና ሰላምን ለማረጋጋጥ ሲባል በሰላምና ፀጥታ ምክር ቤቱ አማካኝነት በግልጽ ጣልቃ መግባትና በአባል አገራት ላይ ወታደር እስከማስፈር የሚደርስ መብትን ማስቀመጡ መልካም ጎኑ ነው። ኅብረቱ በኮትዲቯርና ኬንያ ከምርጫ በኋላ ሊከሰት የነበረን ግጭት በማስቀረት እንዲሁም በወታደር መፈንቅለ መንግሥት ሊያዙ የነበሩ ስልጣኖችን ለሕዝብ እንዲመለስ በማድረግ ተጠቃሽ ውጤት ስለማስመዝገቡም ይመሰክሩለታል።
በሌላ በኩል በአፍሪካ አንድ መሪ በአማካይ እስከ 20 ዓመት ሥልጣንን የሙጥኝ በሚልበት አህጉር ኅብረቱ በዴሞክራሲና የሕዝብ ተሳትፎ ላይ የጎላ ሚና ተጫውቷል ለማለት እንደማያስችል የሚናገሩ አሉ። ለአብነትም የገንዘብ እጥረትን እንደምክንያት እየጠቀሱ ምርጫን ሲያራዝሙ በሚስተዋሉ መሪዎች ላይ የወሰደው ማዕቀብም ሆነ ሌላ እርምጃ አለመኖሩን ያነሳሉ።
በ2016 (እ.ኤ.አ) ብቻ ተካሂደው የነበሩትን የኡጋንዳ፣ ኒጀር፣ ቻድ፣ ጋቦን፣ ጋምቢያና ጋና አገራዊ ምርጫዎች አስመልክቶ ቢቢሲ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ በአብዛኞቹ ምርጫዎች አሻጥር ስለመሰራቱ ያትታል። እንደ ጋምቢያ ባሉት የድኅረ ምርጫ ትርምስ ከአፍሪካ ኅብረት ይልቅ የቀጣናው ጥምረት የሆነው ‹‹ኢኮዋስ›› የበለጠ ጠንካራ አቋምን ሲያራምድና ተሸናፊው ጃሜህ ውጤቱን በመቀበል ሥልጣን እዲያስረክቡ ሲገፋ እንደነበር የሚስታወሱ ወገኖች የኅብረቱ ጥንካሬ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። በጽሑፉ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡትና በአፍሪካ ፖለቲካ ትንተናቸው የሚታወቁት የኦክሰፎርድ ዩኒቨርሲቲው ኒክ ቺዝማን አፍሪካውያን ከፖለቲካ መሪዎች ተጽእኖ ክንድ የተላቀቁ ተቋማትና በሕግ የሚጠበቁ የምርጫ ተቋማት እንደሚያስፈልጓቸው አንስተዋል።
ኅብረቱ በ2012 (እ.ኤ.አ) ማላዊ ልታስተናግደው በነበረው የኅብረቱ ጉባኤ በዓለም ዐቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚፈለጉትን የሱዳኑን ፕሬዘዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር አልጋብዝም በማለቷ የስብሰባ ቦታው ወደ አዲስ አበባ መዛወሩን የሚያስታውሱት ፍራንክሊን ይህ ውሳኔ ከዴሞክራሲ አልፎ አፍሪካንና ዓለም ዐቀፉን ማኅበረሰብ በሕግ የበላይነት፣ በፍትሕና የሰዓኣዊ መብት ጥሰትን በመከላከል አጀንዳዎች የጎሪጥ እዲተያይ ያደረገ ስለመሆኑ ያብራራሉ።
አፍሪካውያን መሪዎቸ ግን ዓለም ዐቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ትኩረቱ አፍሪካውያን ላይ ብቻ ነው በሚል ራሱ ተቋሙ ላይ የፍትሐዊና ሚዛናዊነት ጥያቄ ሲያነሱበት፣ በዚህም የተቋሙ አባል አገር ላለመሆን የሆኑትም ለመውጣት ሲወስኑ ይስተዋላሉ።
ሰላም፣ ፀጥታና መረጋጋት በአፍሪካ አለን?
ቀድሞ እንደተገለጸው ኅብረቱ አሳካቸዋለሁ ከሚላቸውና ከቆመላቸው መርሆዎቹ መካከል በአህጉሩ ሰላምን፣ ፀጥታንና መረጋጋትን ማስፈን የሚሉት ይጠቀሳሉ።
ደቡብ ሱዳን ራሷን የቻለች አገር ከሆነች ጀምሮ በሳልቫኪርና በቀድሞ ምክትላቸው ሪክ ማቻር መካካል በተፈጠረው የጎራ ጦርነት በርካቶችን ለሕልፈትና ስደት ይዳረግ እንጂ ኅብረቱ እዚህ ግባ የሚባል መፍትሔንና ጣልቃ ገብነትን እንዳላሳየ እየተነሳ ይወቀሳል።
አህጉሩ የተለያዩ አሸባሪና ታጣቂ ኃይሎች በየቀኑ ንጹኀንን የሚገድሉበት ስለመሆኑ ገልጸው የነበሩት ባራክ ኦባማ ኅብረቱ ይህ እንዲያበቃ መስራት እንዳለበት መምክራቸው ይታወሳል። በናይጄሪያ ቦኮሃራም፣ ከሶማሊያ አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ደግሞ አልሸባብ አህጉሩን ከሚያምሱት አሸባሪዎች መዝገብ ይጠቀሳሉ።
ከሰሞኑ የኅብረቱ ቋሚ መልዕክተኞች አዲስ አበባ ላይ እየመከሩ እንኳን ኬንያን በሽብር ጥቃት የደጋገማት አልሸባብ ሌላ ጥቃት አድርሶ በአስራዎቹ የሚቆጠሩ ዜጎችን ገድሏል።
ኅብረቱ በሰላምና ፀጥታ ላይ ምን ያህል ተሳክቶለታል ያልናቸው ማርቲን ‹‹ማንኛውም ገለልተኛ ታዘቢ ሊል የሚችለው አልተሳካለትም ነው›› ይላሉ። ዋና መቀመጫው በሆነችው አዲስ አበባ ዙሪያ ያለውን አለመረጋጋት ለአብነት ማንሳት እንደሚቻል የሚጠቅሱት ማርቲን በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለነበረውን የድንበር ጥያቄ እንኳን መፍትሔ ማበጀት አለመቻሉን ያክላሉ። ይልቁንም ሳዑዲ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችና አሜሪካ ጣልቃ ገብተው መፍትሄን እዲሹ ሲያደርግ የነበረ ኅብረት ስለመሆኑም በመጥቀስ ስኬት እንደራቀው ያስረዳሉ። ደቡብ ሱዳን እስካሁን በቀውስ ውስጥ ስትሆን፣ ሱዳናውያን ደግሞ ‹‹በአልበሽር ተረከዝ ስር እያቃሰቱ ነው›› የሚሉት ተመራማሪው ይህ ለኅብረቱ ስኬት ሊሆን እንደማይችልም ያነሳሉ። የኅብረቱ የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ‹አሚሶም› በሶማሊያ ያለውን ጦርነት ለመግታት እየተቃረበ መሆኑን ግን አልሸሸጉም።
በማኅበረ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ረገድ ኅብረቱ የት ነው?
ጌት ጎወር ሐምሌ 28/2015 በዘጋርዲያን ላይ ያሰፈሩት ጽሑፍ የኅብረቱ ቃል አቀባይ፣ አፍሪካ ትብብርን በማላቅና ዴሞክራሲን በማስፈንና ግጭትን በመቀነስ በኩል እየተሳካለት እንደሆነ ስለመናገራቸው ያትታል። ጽሑፉ አክሎም አፍሪካ ሰላምና ጸጥታን ከማስፈን ባለፈ አህጉሩ ተሻጋሪ የባሕል፣ የትምህርትና የንግድ ግንኙነትን እያሰፋ ስለመምጣቱም ይዘረዝራል። አህጉር ተሻጋሪ የተባለው ግንኙነት በተለይም ከቻይና ጋር ያለው መሆኑም ተጠቅሷል። በሌላ በኩል አህጉሩን ለቻይና ብቻ አሳልፎ ላመስጠት እንደነአሜሪካ ባሉ አገራት በኩል ያለው ግብግብ በአፍሪካ ላያ እያሳደረ ያለውን ሌላ መልክ ይዘው የሚያትቱ ጸሓፍትም አሉ።
እንደአውሮፓ ኅብረት ያሉ ጠንካራ ስብስቦች ከአውሮፓ አልፈው በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሲሆኑና በአንድ ገንዘብ መገበያየት ሲቀላቸው የአፍሪካውያን አቻው ተቋም ምን ይዞ መጣ ሲሉም ይጠይቃሉ። በቅርቡ የታሰበው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ምስረታ ተስፋ ያለውን ያህል ስምምነቱን ለመቀበል ከሚግደረደሩ አገራት ባሻገርም ለመተግበር የየአገራቱ ፖሊሲ አስቻይነት ተፈትሾ ይሆን? ሲባልም ብዙ ፈተናዎች እንደሚጠብቁት የሚመክሩት ብዙ ናቸው። ማርቲን ኅብረቱ የጋራ ንግድና ታሪፍ ጉዳዮች ላይ ሊጠቀስ የሚችል ውጤት መኖሩን በመጥቀስ የሚቀረው የቤት ስራ እንደሚበዛ ያስረዳሉ።
አፍሪካን የወረረው የሙስና ወንጀልና ሕገ ወጥ የገንዘብ ማሸሽ ተግባር በአገራት መሪዎቹ ሳይቀር በስፋት የሚተገበር መሆኑን የሚያሳዩ ጽሑፎች በበኩላቸው ከምጣኔ ሀብት ቁርቆዛ ባሻገር አህጉሩን ለማኅበራዊ ቀውስ እየዳረገው መሆኑንም ያመለክታሉ።
McKinsey & Company በተሰኘ ድርጅት ውስጥ የአፍሪካ ቀጣና ሊቀመንበሩ አቻ ልቄ ‹‹Reforming the African Union: The vital challenge of implementation›› በሚል ጽሑፋቸው አፍርካ የሐሳብ ድኻ አለመሆኑን ጠቅሰው አህጉሩ ካለው እምቅ ሀብት ባለፈ አፍሪካውያን እንዴት መበልጸግ እንደሚችሉም ያውቁበታል፤ ዳሩ ግን ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ ብልጽግናው የለም ሲሉ ያትታሉ። በዚህ ላይ ኅብረቱ ቁልፍ ሚና ሊወጣ እንደሚገባውም መክረዋል።
እርግጥ ባለፉት 10 ዓመታት አፍሪካ 19 ሺህ ባለዶላር ሚሊዮነሮች እንዳፈራች የሚያሳዩ መረጃዎች በአውሮፓውያኑ 2017 የአፍሪካ ድምር ሀብት ከ13 እስከ ሦስት በመቶ እድገት ማስመዝገቡንም ያሳያሉ። ይሁንና ይህ እድገት አንድ ነጥብ ኹለት ቢሊዮን ለሚሆነው አፍሪካዊ ሕይወት ምን ጠብ ያደረገው አለ የሚለው ዛሬም መከራከሪያ ነው።
በአንድ ወቅት የናጀሪያው አምባሳደር ሰጉን አፓታ አፍሪካ ሪኒዋል ከተሰኘ የበይነመረብ መገናኛ አውታር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከአውሮፓውያኑ 1970 እስከ 2008 ድረስ ብቻ ከአፍሪካ በሕገ ወጥ መንገድ የሸሸው የገንዘበ መጠን 800 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ተናግረው ነበር። ይህም በየዓመቱ በአማካይ 50 ቢሊዮን ዶላር ይሸሻል ማለት ነው።
በሌላ በኩል በየቀኑ አያሌ ቁጥር ያላቸው አፍሪካውያን ባሕር አቋርጠው ይሰደዳሉ። በተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ መሰረት ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት ብቻ የዓለምን 26 በመቶ (18 ሚሊዮን) ስደተኞች ቁጥር ይሸፍናሉ።
ፍራንክሊን እንደሚሉት ኅብረቱ በአብዛኞቹ አገራት ሦስት አራተኛ ድርሻ የሚኖረውን አምራች ጉልበት የያዘውን ወጣት የሥራና የተሻለ ኑሮ ባለቤት ማድረግ ተስኖታል። ‹‹ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲ ገብተው አምራች ኃይል ሆነው ይወጣሉ መጨረሻው ግን ስራ አጥነት ነው›› ሲሉ ነው ፍራንክሊን የአፍሪካ ኅበረት ያልተሻገራቸውን የቤት ሥራዎች ብዙነት የሚያስገነዝቡት። ስራ አጥነት ዋነኛው ችግር ነው የሚሉ ወገኖች ደግሞ ለግጭትና ተቃውሞዎቸ መበራከት ተጠያቂም ያደርጉታል።
ባሳለፍነው ማክሰኞ የተሰበሰበው የኅብረቱ ጉባኤ ማጠንጠኛ ካደረጋቸው አጀንዳዎች መካከል በሰላም እጦት እየሰፋ የመጣው የዜጎች መፈናቀልና የስደተኞች ጉዳይ ይገኙበታል። ኅብረቱ ባለፈው ታኅሣሥ ከሕገ ወጥ ስደት ጋር ተያይዞ ባወጣው ሰነድ ዓለም ዐቀፉን የፍልሰተኞች ድርጅት ጠቅሶ በተለይም ከምዕራብና ከአፍሪካ ቀንድ የሚነሱ አፍሪካውያን አውሮፓ መግባትን ህልም አድረግው እንደሚጎርፉ፣ ዳሩ ግን ያሰቡት ቦታ ሳደረሱ የባሕርና የአራዊት ሲሳይ ሆነው የሚቀሩት የበዙ እንደሆኑ ያመለክታል። ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት በሕገ ወጥ መንገድ ተጉዘው ከሞቱና ከጠፉ ዓለም ዐቀፍ ስደተኞች መካከል 77 በመቶውን የሚይዙት አፍሪካውያን ስለመሆናቸውም ያነሳል።
ኅብረቱ ጉባኤ በጠራ ቁጥር ለመሪዎቹ ከሚደረገው ማሸርገድ (የጎዳና አዳሪዎችን ማሸሽ ጨምሮ) ዘሎ ለምስኪን አፍሪካውያን ሕይወት መሻሻል ምን እሴት ጨመረ የብዙዎች ጥያቄ እንደሆነ አለ። ማርቲን መሪዎቹ ኅብረቱን በኃያልነቱና በተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ሊፈሩት የሚገባበት ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚገባም ይመክራሉ። ብዙዎች ኅብረቱ ከበጀቱ ጀምሮ ከድጎማ ተላቆ የአፍሪካውያን መመኪያ የሚሆንበት ዘመን እንዲመጣ ይጠይቃሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011