ኢትዮ ቴሌኮም የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎትን የሀዋሳ ከተማ ጨምሮ በደቡብ ሪጅን በሚገኙ 12 ከተሞች በይፋ መጀመሩን አስታወቀ።
የ4ጂ አገልግሎት መጀመር የላቀ ፍጥነትና አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ደንበኞች የተሻለ አገልግልት ማግኘች እንደሚችሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አገልግሎቱ የአገራዊ ምርታማነትን ለማሳደግ እና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የዜጎች የኢንተርኔት አጠቃቀም ሁኔታ እያደገ መጥቷል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ በ65 ከተሞች ላይ የ4ጂ አገልግሎት ማስጀመር መቻሉን በማንሳት በዚህም ሚሊየኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው በአሁን ሰአትም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 25 ነጥብ 3 ሚሊየን መድረሱን ገልፀዋል።
አጠቃላይ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር 55 ነጥብ 4 ሚሊየን መድረሱንም ገልፀው በዛሬው ዕለት በ12 ከተሞች አገልግልት መስጠት የጀመረው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ ከ9 መቶ ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ኢትዮ ቴሌ ኮም ዛሬ ያስጀመረው አገልግሎትም ሀዋሳን ጨምሮ ሻሸመኔ፣ ይርጋአለም፣ አለታወንዶ ዲላ፣ አርሲ ነገሌ፣ ቡሌሆራ፣ ያቤሎ፣ ሞያሌና ሻኪሶ ከተሞች ላይ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ያደርጋል ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ መግለፃቸውን ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።






