የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሀገር ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ተገለፀ።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ፈርመውታል።
የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት ኢቢሲ ባለው ሰፊ ተደራሽነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፍ እየተጫወተው ያለውን ገንቢ ሚና ለህዝብ ያሳውቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው፣ ባንኩ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስከ ባቡር ፕሮጀክቶች እና የስኳር ፋብሪካዎች በፋይናንስ የሚደግፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ስምምነቱ ይህን ሀገራዊ አስተዋጽዖ ለህዝብ ለማሳወቅ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በስምምነቱ መሰረት ኢቢሲ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገጽታ ግንባታ፣ አገልግሎትን የማስተዋወቅ እና ሌሎች ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል መባሉን ከኢቢሲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።





