ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ምገባ ፖሊሲና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂን የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
የምገባ ፖሊሲና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ይፋ በሆነበት ወቅትም የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብሩ የተማሪዎችን ለረሃብ ተጋላጭነት በማስቀረት የተሟላ ጤናና ስርአተ ምግብ እንዲሁም የተሻለ የትምህርት አቀባበልና ውጤት እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።
መርሃ-ግብሩ የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት ከማሻሻል ጎን ለጎንም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንዳለውም አስረድተዋል።
ዛሬ የጸደቀው የትምህርት ቤት ምገባ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ዋና አላማም ለሁሉም የቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው በየእለቱ በንጥረ ምግብ የበለጸገ ምግብ ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አገር አቀፍ የትምህርት ፖሊሲና ስትራቴጂ ማጽደቂያ ስነስርአት ላይ እንዳሉት ለጸደቀው የትምህርት ቤት ምገባ ፖሊሲና ስትራቴጂ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባና የሁሉንም ድጋፍና የተቀናጀ ትብብር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።





