አሜሪካ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት መሪነት መቀጠል እንዳለበት አሳሰበች

0
1048

የተባባሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ትናንት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በተወያየበት ወቅት አሜሪካ በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ሕብረት መሪነት መቀጠል እንዳለበት አሳሰበች።

በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶምሰን-ግሪንፊልድ “አለመግባባቱን ለመፍታት የአፍሪካ ሕብረት ትክክለኛው ቦታ ነው” ካሉ በኋላ ሦስቱ አገራት ከስምምነት እንዲደርሱ አሜሪካ ፖለቲካዊ እና ቴክኒካዊ ድጋፎችን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት እና ሦስቱ አገራት አዎንታዊ ውጤት እንዲገኝ የድርድሩ ታዛቢ ከሆኑት ደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ ድጋፍ እና ልምድ እንዲወስዱ አምባሳደሯ ጠይቀዋል።

ሦስቱ አገራት እአአ 2015 ላይ የፈረሙት የመርህ ስምምነትን እና እአአ 2020 ላይ የአፍሪካ ሕብረት መግለጫን እንደ መነሻ ማጣቀሻ መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የአባይ ወንዝ ውሃ ለሦስቱም አገራት ምን ያክል ጠቃሚ እንደሆነ እንረዳለን ያሉት አምባሳደር ሊንዳ ቶምሰን-ግሪንፊልድ፤ ሦስቱን አገራት በፖለቲካ ቁርጠኝነት በግድቡ ውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽን ዙሪያ ከስምምነት ሊደርሱ ይችላሉ ሲሉም ገልፀዋል።

አምባሳደር ሊንዳ፤ የግብጽ እና የሱዳን የግድቡ የደህንነት እና የኦሮፕሬሽን ስጋት ከኢትዮጵያ የልማት ፍላጎት ጋር ሊታረቅ እንደሚችልም ገልፀዋል።

ሦስቱ አገራት በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እና አለመግባባቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር እንዲመክሩ ጋብዘዋል።

በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ ከስምምነት መድረስ በውሃ ሃብት ላይ ሌሎች ተጨማሪ ትብብሮች እንዲኖሩ፣ ቀጠናዊ ልማት እንዲመጣ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል አምባሳደሯ።

በመጨረሻም አምባሳደሯ አሜሪካ በጉዳዩ ላይ ከግብጽ፣ ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠው፤ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራው ድርድር በፍጥነት እንዲቀጥል እና ድርድሩ ውጤታማ እና አዎንታዊ እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን ማለታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here