በትግራይ ኤርትራውያን ስደተኞች መገደላቸው ተገለጸ

0
958

በትግራይ ክልል ሽሬ አካባቢ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች መገደላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ደርሰውኛል ሲል የተመድ ስደተኞች አጀንሲ ገለጸ:: በኢትዮጵያ የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪክ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት፣ ከኦንላይን እና ከሌሎች ምንጮች በትግራይ ክልል ሽሬ ኤርትራውያን ስደተኞች መገደላቸውን የሚገልጽ ሪፖርት ባለፈው ሳምንት እንደደረሳቸው አስታውቀዋል። ቃል አቀባዩ ለአል ዐይን አማርኛ በላኩት ኢ-ሜኤል፣ የደረሱንን ሪፖርቶች በልዩ ትኩረት ነው የምንመለከተው፤ ወዲያውኑ ሽሬ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን ፣ ባልደረቦቻችንና ሠራተኞቻችን አግኝተናል ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ኔቨን ክሬቨንኮቪክ “እስካሁን የደረሱን ማናቸውም ክሶች ማረጋገጥ አልቻልንም፤ ነገር ግን የእነዚህን ዘገባዎች ትክክለኛነት ለመገምገም የሚረዱ ተገቢ መረጃዎችን መሰብሰባችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት የአገር መከላከያ ከትግራይ ወጥቻለሁ ማለቱን ተከትሎ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ግድያ እየተፈጸመ እንደሆነ የተለያዩ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ። በትግራይ ግጭት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞች ያሉበት እንደማይታወቅ በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩ ኤን ኤች ሲአር) ቃል አቀባይ የነበሩት ኤሊዛቤት አርንስዶርፍ ከአንድ ወር በፊት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነራቸው ቆይታ መግለጻቸው ይታወሳል።
ቃል አቀባይዋ ሕፃፅና ሽመአልባ የተባሉት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች መውደማቸውንና ስደተኞቹ የሰብዓዊ እርዳታ የማግኘት ችግር እንደገጠማቸው በወቅቱ ተናግረው ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከ8 ወር በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች ለውጡን በመደገፍ አብረውኝ ሲሰሩ በነበሩ ዜጎች ላይ ጥቃትና ግድያ እየፈጸሙ ነው ሲል ከሷል። መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው እና ወታደሮችን ከመቐለ ያስወጣው በፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑንም መግለጹ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here