በግብጽና ሱዳን ጠያቂነት በግድቡ ላይ ለመምከር ባሳለፍነው ሀሙስ ምሽት ላይ የተካሄደው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ፣ የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት እንዲታይ ወስኗል። ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት በኩል እንዲቀጥል የጠየቀች ሲሆን፣ ግብጽና ሱዳን በአንጻሩ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲመለስ የጎላ ፍላጎት አላሳዩም። ኢትዮጵያን ወክለው የተገኙት የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ(ዶ/ር) የጸጥታው ምክር ቤት ኃላፊነት ጸጥታን በሚያደፈርሱ ጉዳዮች ላይ መምከር እንጂ የኤሌትሪክ ማመንጫ ግድብን በሚመለከት መወያየት ባለመሆኑ ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲሄድ ጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን አቋም ለጸጥታው ምክር ቤት ሲያስረዱ፣ በኢትዮጵያ 65 ሚሊዮን ዜጎቿ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደማያገኙ ገልጸው፣ ግድቡ የሚገነባው ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ ሕይወት ለማውጣት ነው ብለዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕዝብ ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን እንደምትደግፍ አብራርተዋል። አሜሪካን ጨምሮ ኬንያ ፣ ሩሲያ ፣ አየርላንድ ፣ እንግሊዝ እና ህንድ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት እንዲቀጥል ከደገፉ አገራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ምክር ቤቱም የሦስቱን አገራት የጋራ ጥቅም ባከበረ መልኩ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል ወስኗል።
ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013


