ኤጄንሲው 3.6 ቢሊዮን ብር አበድሯል

0
725

የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲ በ2013 በጀት ዓመት በአስር ወራት 3.6 ቢሊዮን ብር ለፕሮጀክት ሥራዎች ብድር መስጠቱን አስታወቀ። ኤጀንሲው በ2013 በጀት ዓመት በአስር ወራት 3.6 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲው ከተላከላት ሪፖርት ተመልክታለች። በበጀት ዓመቱ ኤጀንሲው ለ3 ሺሕ 698 ሼዶች እና 114 ሺሕ 455 ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በማመቻቸት 103 ሺሕ 361 ኢንተርፕራይዞች እንዲቋቋሙ ማድረጉን በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
ኤጀንሲው በ2013 በጀት ዓመት በከተሞች ለ1.4 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ፣ ከክልል የዘርፉ አስፈጻሚና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት፣ ባለፉት አስር ወራት ለ1.5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጿል።

የሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት፣ የብድርና የሥልጠና አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ባለቤት የሆኑ ሴቶች ገቢን ለማሳደግና የሥራ እድል የመፍጠር አቅማቸውን ከፍ ለመድረግ የታሰበ ነው። ከዓለም ባንክ፣ ከካናዳ የልማት ተራድኦ፣ ከእንግሊዝ የልማት ተራድኦ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ከጣልያንና ጃፓን መንግሥታት በተገኘ የ118 ሚሊዮን ዶላር ብድር በ10 ከተሞች(አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ (ሻሸመኔን ጨምሮ)፣ ዲላ፣ አሰላ፣ ባህር ዳር፣ አዳማ፣ መቀሌ፣ ጎንደርና አክሱም) ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ፕሮጀክት ነው።

በአሰር ወራት በአስሩም የፕሮጀክቱ ከተሞች ለ 3 ሺሕ 575 ኢንተርፕረነሮች 893 ሚሊዮን ብር ብድር ለማሰራጨት ታቅዶ፣ ለ560 (15.2%) ሴት ኢንተርፕረነሮች 140 ሚሊዮን ብር (15.7%) ብድር መሰራጨቱ ተገልጿል። ባለፉት 10 ወራት በከተማ ግብርና 270 ሺሕ 667፣ በኢንዱስትሪ 527 ሺሕ 667 እና በአገልግሎት ዘርፍ 489 ሺሕ 56 በድምሩ ለ1.2 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ በከተማ ግብርና 145 ሺሕ 718 (53.8%)፣ በኢንዱስትሪ 533 ሺሕ 570 (101%) እና በአገልግሎት ዘርፍ 841 ሺሕ 611 (172%) በአጠቃላይ ለ 1.52 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ኤጀንሲው ጠቁሟል። የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች 165 ሺሕ 940 የዩንቨርስቲና የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች መሆናቸው ተመላክቷል።

በክልል ደረጃ ሲታይ በኦሮሚያ 576 ሺሕ 871፣ አማራ 339 ሺሕ 889፣ ደቡብ 148 ሺሕ 287፣ ሐረሪ 2ሺሕ 500፣ ቤኒሻንጉል 11ሺሕ 304፣ ሱማሌ 24ሺሕ 115፣ አፋር 7ሺሕ 703፣ ጋምቤላ 9ሺሕ 36፣ ሲዳማ 52ሺሕ 087፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 319 ሺሕ 906 እና በድሬዳዋ አስተዳደር 11 ሺሕ 280 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ በሪፖርቱ ተመላክቷል። አጠቃላይ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 931 ሺሕ 012 (61%) ብቻ በቋሚነት የተፈጠረ ሲሆን፣ ቀሪው 589 ሺሕ 887(39%) በጊዜያዊ የተፈጠረ የሥራ ዕድል ነው። ይህም የተፈጠረው የሥራ ዕድል 80 በመቶ በቋሚነት ለመፍጠር ከተያዘው ዕቅድ አንጻር ሲታይ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው።

በሌላ በኩል ኹለተኛው የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ-ግብር በ72 አዲስና በ11 ነባር ከተሞች በድምሩ በ83 ከተሞች 284 ሺሕ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የሚያስችሉ የቅደመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸው ተጠቁሟል። በመጀመሪያው የከተሞች የሴፍትኔት መርሃ-ግብር በ7 ከተሞች 329 ሺሕ ዜጎች አከባቢን በሚቀይሩ የአከባቢ ልማት ሥራዎች እንዲሳተፉ በማድረግ፣ 672 ሚሊዮን ብር ወርሃዊ ክፍያ እንዲከፍላቸው ተደርጓል።


ቅጽ 3 ቁጥር 140 ሐምሌ 4 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here