ኳታር የኢትዮጵያን የመልማት መብት እንደምትደግፍ እና በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ የያዘችው በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም እንዳልቀየረች አስታወቀች፡፡
በኳታር የኢፈዴሪ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ ከኳታር ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሱልጣን ቢን ሳዓድ አል ሙሬይኪ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የኳታር መንግስት እና የዓረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በያዙት አቋም ላይ ሐሳብ ተለዋውጠዋል።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኳታር የኢትዮጵያን የመልማት መብት እንደምትደግፍ እና በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ይዛው የቆየችውን በመርህ ላይ የተመሰረተ ግልጽ አቋም እንዳልቀየረች፤ እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው ውይይት በአፍሪካ ሕብረት የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ በዚሁ መቀጠል እንደሚገባው መግለጻቸውን ከኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።




