በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በአገር ላይ የሚደረጉ የውጭ ጫናዎችን በመቃወም እና ህፃናትን ለውትድርና እየተጠቀመ ባለው የህወሓት ቡድን ላይ ጫና እንዲደረግ ያለመ የትዊተር ዘመቻ መካሄዱ ተገለፀ፡፡
አሜሪካ በዓመታዊ ሪፖርቷ ኢትዮጵያን የዘር ማጥፋት ወንጀል እና ጭካኔ ከተፈፀማባቸው አምስት አገራት አጋር ለማካተት መሞከሯ ኢትዮጵያዊያኑን የትዊተር ተሳፊዎች ተቃውሟቸውን እንዲገልፁ እንዳስገደዳቸው አመልክተዋል፡፡
በተለይም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን በኢትዮጵያ ላይ የያዙት አቋም ሚዛኑ ያጋደለ እና በአጠቃላይ የምዕራባዊያን አገራት የህወሓት ጁንታ ቡድን ከፊት እያሰለፋቸው ስላሉት ህፃናት ግድ ሳይሰጣቸው ባለየ ማለፋቸው ተገቢነት የለውም በሚል መቃወማቸው ተገልጿል፡፡
እንደ ኢቢሲ ዘገባ ከሆነ በተለይም የሽብር ቡድኑ በመከላያ ሰራዊቱ እና በማይካድራ ላይ የፈፀመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ እንኳን ሊያስታውሱት አለመፈለጋቸው እንዳሳዘናቸውም አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም አሜሪካና ሌሎች አገራት የኢትዮጵያን ጉዳይ በፍትሃዊነት እንዲያጤኑት እና ሉዓላዊነቷን እንዲያከብሩም በትዊተር ዘመቻው ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በትግራይ ስላለው ግጭት እያቀረቡት ያለው መረጃ በእውነታ ላይ ያልተመሰረተና መሬት ላይ እየሆነ ያለውን የሚዳስስ ሳይሆን የሚፈልጉትን አዛብተው ማቅረባቸው የችግሩ አካል እንዲሆኑ አድርጓቸዋል በማለት ሀሳባቸውን በትዊተር ላይ ያስተላለፉ የዘመቻው ተሳታፊዎች መግለፃቸውን ዘገባው አመላክቷል፡፡





