ጨፌ ኦሮሚያ 14 መደበኛ፣ 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 6ኛ ዓመት ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ጉባኤው የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት ማጽደቅን ጨምሮ 11 አጀንዳዎች ላይ ይወያያል።
በጉባዔው ላይም የኦሮሚያ ክልል ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት በክልሉ በ31.7 ቢሊዮን ብር ወጪ 11 ሺህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ የበጀት ዓመቱ አፈፃፀም ለጨፌው አባላት ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ በክልሉ ግብርና ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ ውሳኔዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልፀዋል።
ከነዚህም መካከል አንዱ በሆነው የበጋ ስንዴን የማልማት መረኃግብር 382 ሺህ ሄክታር መሬት እንደታረሰ ገልጸው፣ ከዘርፉ 15 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ይጠበቃል ብለዋል።
ክልሉን የብጥብጥ ቀጠና ለማድረግ የተለያዩ ሀይሎች ሲሰሩ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ የክልሉ ህዝብ ባለው የሰላም ቁርጠኝነት ሴራው ሊከሽፍ መቻሉንም አክለው ገልፀዋል።
በአዳማ ከተማ በገልማ አባ ገዳ አዳራሽ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ጉባዔ በ2013 በጀት ዓመት በአብዛኛው ለካፒታል ስራ የዋለ የ14 ቢሊየን ብር ተጨማሪ ረቂቅ በጀት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።






