መነሻ ገጽሌሎችፓርላማና ምርጫ ማለዳ“ኢትዮጵያ አሸንፋለች” የተባለለት ምርጫ ውጤት

“ኢትዮጵያ አሸንፋለች” የተባለለት ምርጫ ውጤት

ኢትዮጵያ ስደስተኛውን አገራዊ ምርጫ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በመላው አገሪቱ ባይሆንም ባለሳለፍነው ሰኔ 14/2013 አካሂዳለች። ሰኔ 14 በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ያልተካተቱ እና በከፊል ምርጫ የተካሄደባቸው ክልሎች አሉ። ሙሉ በሙሉ ምርጫ ያልተደረገባቸው ሱማሌ ክልል፣ ትግራይ ክልልና ሐረሪ ክልል ሲሆኑ፣ በከፊል ምርጫ ከተካሄደባቸው ክልሎች መካከል አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ደቡብ ክልል ይገኙበታል።

በከፊል ምርጫ ከተደረገባቸው ክልሎች መካከል ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካሉት ሦስት ዞኖች ምርጫ የተካሄደው በአንዱ መሆኑ የሚታወስ ነው። በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምርጫ ያልተደረገባቸው ኹለት ዞኖች መተከልና ካማሺ ዞኖች ሲሆኑ፣ በዞኖች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ አልችልም በማለቱ ነው።

የመጀመሪያው ዙር ምርጫ የተካሄደባቸው ከቤኒሻንጉል ክልል ውጭ አብዛኛውን ክፍል ያካተተ ሲሆን፣ በክልሎች የተወሰኑ አከባቢዎች ምርጫ ሳይከናወን የቀረው በጸጥታ ችግር እና ድምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ላይ ባጋጠመ ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር ለማካሄድ የተገደደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሙሉ በሙሉ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የሱማሌ፣ ሐረሪ እና ሌሎች ክልሎች እንድሁም ተቆርጠው በቀሩ ሌሎች አከባቢዎች ጳጉሜ 1/2013 ምርጫ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ይዟል። ይሁን እንጅ ከጥቅምት 24/2013 ጀመሮ እሰካሁን ድረስ የዘለቅ ችግር ያለበት ትግራይ ክልል ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ስለማካሄዱ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ሰኔ 14/2013 የተካሄደውን የመጀመሪያ ዙር አገራዊ ምርጫ ውጤት ከግማሽ ወር ብኋላ ባሳለፍነው ሐምሌ 3/2013 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ሆኗል። ቦርዱ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት 547 መቀመጫዎች ካሉት ኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 465 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ተካተዋል። ይህም ማለት ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ ተቆርጠው የቀሩ የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት 82 ናቸው ማለት ነው።

የመጀመሪያ ዙር ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከ436 የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫ ገዥው ብልጽግና 410 ወንበሮችን ማሸነፉን አስታውቋል። ቦርዱ በገለጸው ውጤት መሰረት በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 26 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲና በግል ተወዳዳሪዎች እንደተያዙ ያሳያል።

ቦርዱ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት መሰረት፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና በአማራ ክልል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወዳዳሪዎች የማሸነፍ ዕድል አግኝተዋል። በአማራ ክልል የማሸነፍ ዕድል ካገኙ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ምርጫ ከተደረገባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች አምስት መቀመጫዎች ከአማራ ክልል ማግኘቱንም ቦርዱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አራት የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት መቀመጫዎች፣ የጌዲዮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትም ኹለት የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ከደቡብ ክልል ማግኘታቸውን ቦርዱ ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤት መሰረት አራት የግል ተወዳዳሪዎችም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማግኘት የቻሉ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት አንድ የግል ዕጩ ተወዳዳሪ ከአዲስ አበባ፣ ሦስት የግል ተወዳዳሪዎች ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል መሆናቸው ተገልጿል።

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ተሳታፊ የነበሩ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች ያገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤት በአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና 22 መቀመጫዎችን ያገኘ ሲሆን አንድ መቀመጫ አንድ የግል ዕጩ ተወዳዳሪ አግኝተዋል። አዲስ አበባ ያሸነፉት የግል ዕጩ ተወዳዳሪ ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት(ዳ/ን) መሆናቸው ተገልጿል።

አፋር ክልል ስምንት የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ሰኔ 14 ምርጫ በተካሄደባቸው ስድስት መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል።
አማራ ክልል ምርጫ ከተካሄደባቸው 125 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ብልጽግና በ114ቱ ሲያሸንፍ፣ አብን አምስት መቀመጫዎችን ማሸነፍ ችሏል።
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኹለቱ ዞኖች ባልተካተቱበት የመጀመሪያ ዙር ምርጫ፣

ከክልሉ ዘጠኝ የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫዎች መካከል በሦስት የፓርላማ መቀመጫዎች ሰኔ 14 ምርጫ ተካሂዶ በሦስቱም መቀመጫዎች ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ኹለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ብልጽግና ፓርቲ አንዱን መቀመጫ አግኝቷል ተብሏል። አንዱ መቀመጫ በድጋሚ ምርጫ የሚታወቅ ይሆናል።
ሙሉ በሙሉ ምርጫ ሰኔ 14 የተካሄደበት ጋምቤላ ክልል ሦስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ሲኖሩት፣ ሦስቱንም ምርጫ ክልሎች ብልጽግና ፓርቲ አግኝቷል።

ኦሮሚያ ክልል178 የፓርላማ መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ምርጫ ከተካሄደባቸው 170 መቀመጫዎች ውስጥ ብልጽግና 167ቱን ማሸነፉን ቦርዱ ይፋ አድርጓል። ቀሪዎቹን ሦስት መቀመጫዎች የግል ዕጩዎች ማሸነፋቸው ተመላክቷል።
ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ተለይቶ አዲስ የተመሰረተው ሲዳማ ክልል 19 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ 19ኙንም የምክር ቤት መቀመጫዎች ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል።
ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል104 የፓርላማ መቀመጫዎች ሲኖሩት፣ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ከተከናወነባቸው 85 የፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ በ75ቱ ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል። በደቡብ ክልል ድምጽ ያገኘው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች

ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) አራት መቀመጫዎችን አግኝቷል። በዚሁ ክልል የጌድዮ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ኹለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማግኘቱን ቦርዱ ይፋ አድርጓል።
ሰኔ 14 በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ በጥቅሉ ከ547 የፓርላማ መቀመጫዎች በ436 ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፣ ብልጽግና 410፣ አብን አምስት፣ ኢዜማ አራት፣ የግል ተወዳዳሪዎች አራትና ጌህዴድ ኹለት የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫዎችን አግኝተዋል።
የክልል ምክር ቤት መቀመጫ ውጤት ካገኙ ፖለቲካ ፓርቲዎች ብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤትን ሙሉ ለሙሉ አሸንፏል። አዲስ አበባ 138 መቀመጫዎች አሏት። አፋር ክልል ከ96 መቀመጫዎች 51 መቀመጫዎች ብልጽግና ሲያሸንፍ፣ አርጎባ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሦስት መቀመጫዎችን አሸንፏል። በአንድ የምርጫ ክልል ድጋሚ ምርጫ ይካሄዳል።

አማራ ክልል 294 የክልል ምክር ቤት መቀመጫ ሲኖሩት፣ ብልጽግና 128 መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ፣ አብን 13 መቀመጫዎችን አሸንፏል። በ5 ምርጫ ክልሎች ድጋሚ ምርጫ ይካሄዳል። ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 99 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ሲኖሩት፣ ምርጫ በተካሄደባቸው 22 መቀመጫዎች ብልጽግና አሸንፏል። በአንድ የምርጫ ክልል ድጋሚ ምርጫ ይካሄዳል።

ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 189 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ብልጽግና ፓርቲ 189ቱንም መቀመጫዎችን አሸንፏል።ጋምቤላ 56 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ሲኖሩት፣ ብልጽግና ፓርቲ 149 መቀመጫዎች አሸንፏል። የጋምቤላ ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ሰባት መቀመጫዎች አሸንፏል።

ኦሮሚያ ክልል 537 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ሰኔ 14 ምርጫ የተከናወነው በ171 የምርጫ ክልሎች ብልጽግና ፓርቲ 513 መቀመጫዎች አሸንፏል።
ሲዳማ 190 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ሲኖሩት፣ ብልጽግና ፓርቲ 190 መቀመጫዎች አሸንፏል። ደቡብ ክልል 291 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ሲኖሩት፣ ሰኔ 14 ምርጫ በተከናወነባቸው በ89 ምርጫ ክልሎች ላይ ብልጽግና ፓርቲ 245 መቀመጫዎች አሸንፏል። ኢዜማ 10 መቀመጫዎች ማሸነፈፍ ያቻለ ሲሆን፣ የጌዲኦ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ስድስት መቀመጫዎች አሸንፏል።

- ይከተሉን -Social Media

ሰኔ 14 በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር አገራዊ ምርጫ፣ በአዲስ አበባ ለመምረጥ ከተመዘገቡት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊየን መራጮች 99 በመቶ ሲመርጡ፣ በአፋር ከተመዘገቡ አንድ ነጥብ ሰባት መራጮች 97 በመቶ፣ አማራ ክልል ከተመዘገቡት ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊየን መራጮች 94 በመቶ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከተመዘገቡ 162 ሺሕ መራጮች የመረጡት 55 በመቶ ያክሉ ብቻ ናቸው።

ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከተመዘገቡ 208 ሺሕ መራጮች 95 በመቶ ያክሉ ሲመርጡ፣ ጋምቤላ ክልል ከተመዘገቡ 415 ሺሕ መራጮች 89 በመቶ፣ ኦሮሚያ ክልል ከተመዘገቡ 15 ሚሊየን መራጮች 96 በመቶ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ከተመዘገቡ አምስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን መራጮች 91 በመቶ ሲመርጡ፣ ሲዳማ ክልል አንድ ነጥብ ስምንት መራጮች ተመዝግበው 100 በመቶ መምረጣቸውን ቦርዱ አስታውቋል።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከመነሻው አንስቶ በመደበኛ ጊዜ እና ሁኔታ ከተካሄዱት ምርጫዎች መካከል የተለየ እንደነበር ቦርዱ አስታውሷል። ምርጫው እጅግ በጣም ብዙ ፓለቲካዊ እና ማሕበረሰባዊ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሲከናወን እንደነበር ቦርዱ አውቆ ዝግጅቱን የጀመረ ቢሆንም፣ የዓለም አቀፍ ኮቪድ ወረርሽኝ ስጋት ከታሰበበት ጊዜ በ10 ወር ዘግይቶ እንዲካሄድ መድረጉ የምርጫውን ሂደት እቅድና ዝግጅት እንዲሁም ጊዜ እንደ አገርም እንደቦርድም ካሰብነው የተለየ እንዲሆን አድርጎታል ብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 141 ሐምሌ 10 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች