የቡርኪናፋሶ ልዑካን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እና ከፕላንና ልማት ኮሚሽን ጋር የተሞክሮ ልውውጥ ማካሄዳቸው ተገለፀ
ጉብኝቱ በቡርኪናፋሶ የሥራ ፈጠራና ስምሪት ሚኒስቴር የተመራና ልዩ ልዩ ሚኒስቴሮች፣ የፕሬዘዳንት አማካሪዎችና ባለሙያዎች የተካተቱበት ሲሆን በዋናነት ከኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ አዘገጃጀት እና አተገባበር፣ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም አመርቂ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር ከተሠሩት ሥራዎች ልምድ ለመውሰድ የታቀደ መሆኑም ታውቋል።
በውይይቱ መክፈቻ የኢፌዴሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን የኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍና ዘላቂ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን የመፍጠር ዓላማ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የአሥር ዓመት ፍኖተ ካርታ ቀርጾ የሥራ አገራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራውን በተቀናጀ ሁኔታ የሚመራበትን አካሄድ ለልዑካኑ አብራርተዋል።
በተጨማሪም በፕላንና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ እንዳልካቸው ስሜ የኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ፤ የሥራ ዕድል ፈጠራ አገራዊ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድና የሚተገብራቸው ልዩ ልዩ ሥራዎች እንዲሁም ከቢግዊን ፊላንትሮፒ እና ዜንይሲስ ቴክኖሎጂስ ጋር በመቀናጀት ያለማውን የሥራ ስምሪት መረጃን ማጠናቀሪያና መተንተኛ ፕላትፎርም አሠራር ቀርቧል።
የቡርኪናፋሶ ልዑካን ቡድኑ ለሁለቱም ተቋማት ባነሷቸው ጥያቄዎችና ኃሳቦች ዙርያ ውይይት የተደረገ ሲሆን በማጠቃለያቸው የተገኘው ልምድ በተለይም ዕቅዶች ሲዘጋጁ የዜጎችን ፍላጎት ማዕከል ያደረጉና ለረዥም ጊዜ ታስበው የተሰሩ መሆናቸው እንደመልካም ተሞክሮ የሚወሰድ መሆኑን መግለፃቸውን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።








