ከሰሞኑ ለእስራኤል ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርባ ውድቅ የተደረገባት ግብፅ በአባይ ግድብ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባበት ቻይና እንድትፈታላት መጠየቋ ተገለጸ፡፡
ግብፅ በአባይ ግድብ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት ቻይና ትፈታዋለች የሚል ትልቅ እምነትና ተስፋ እንዳላት በፕሬዝዳንቷ በኩል መግለጿን አል ሞኒተር ዘግቧል።
ግብፅ የሕዳሴው ግድብን ጉዳይ ይዛ ወደ ቻይና ፊቷን ማዞሯን የጠቀሰው ዘገባው፤ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ አያያዝ ዙሪያ ስምምነት ላይ የሚያደርስ ድርድር ለማድረግ በቻይና ላይ እምነት እንዳላት ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ መግለጻቸውን አስነብቧል።
ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ በዚሁ ሳምንት በሰሜን ምዕራብ የባህር ዳርቻዋ አላሜይን ከተማ ከቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ጋር ውይይት ማድረጋቸውና ይሄንን ጉዳይ እንዳነሱላቸው ነው ዘገባው ያስታወቀው።
ዋንግ በበኩላቸው ቻይና የሁሉንም ወገኖች ፍላጎት ያማከለ መፍትሄ እንደምትፈልግ መግለፃቸው ተዘግቧል፡፡
ግብጽ የግድቡን ጉዳይ ወደተለያዩ አገራትና ተቋማት እየወሰደች ቢሆንም እስካሁን ይህ ነው የሚባል ምላሽ አላገኘችም። በቅርቡም ጉዳዩን ለእስራኤል አቅርባ እስራኤል የግብጽን ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
በተመሳሳይም ጉዳዩን ወደተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ወስዳ እንዲታይ ያደረገች ቢሆንም፤ ምክር ቤቱ ጉዳዩ መታየት ያለበት በአፍሪከ ህብረት ጥላ ስር ነው የሚለውን የኢትዮጵያ መከራከሪያ መደገፉ አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ የያዘቸው አቋም፤ ጉዳዩ መፈታት ያለበት በድርድር እና በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ነው የሚል መሆኑና ይህንንም በርካታ የዓለም አገራትና ተቋማት መደገፋቸው ይታወቃል ሲል አል ሞኒተርን ጠቅሶ ኢ.ፕ.ድ ዘግቧል።



