የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው የ5ኛ ዓመት 13ኛው መደበኛ ጉባኤ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ማጽደቁን የክልሉ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ አብዱልከሪም አህመድ ገለፁ፡፡
ዳይሬክተሩ እንደገለፁት የክልሉ ምክር ቤት አባላት በቀረበላቸው የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት በማድረግ አፅድቀዋል፡፡
የሀብት ምዝገባ አዋጁን ከማፅደቁም በተጨማሪ የክልሉ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን በማሻሻያ በክልሉ የተለያዩ መስሪያቤቶች ውስጥ የሚገኙ የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች ተጠሪነታቸው ለክልሉ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንዲሆን ምክር ቤቱ መወሰኑንም አቶ አብዱልከሪም ገልፀዋል፡፡
የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጁ በክልሉ ም/ቤት መጽደቁ ሙስናን ቀድሞ በመከላከልና የጥቅም ግጭትን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ይገመታል ተብሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሀገራዊ የሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ሥራዎችን ምሉዕ ለማድረግና ሀገራዊ መልክ ለማስያዝ የአዋጁ መፅደቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው መታመኑን ከፌደራል የስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሶማሌ ክልልን ጨምሮ ሁሉም የሀገራችን ክልሎች የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅን አፅድቀው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡





