በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የፖለቲካ ለውጥ ሒደት በመመልከት እሸቱ ዱብ የለውጡን ዓይነት እና ምንነት በግል እይታቸው ለመተንተን ከሞከሩ በኋላ በዚህ ዓይነቱ የፖለቲካ ለውጥ ወስጥ ተቋማዊ ለውጥ በቀላሉ እንደማይገኝ ይናገራሉ።
ባሳለፍናቸው ሦስትና አራት ዓመታት ወይም በተለይ በመጨረሻዎቹ ዐሥሩ ወራት ያየናቸው ኹነቶች መፃዒ ዕጣ ፈንታችንን በምን ያለ መንገድ እንደሚቀርፁት ወይም ሊቀርፁት እንደሚገባ መነጋገር ይገባናል። መነሻው ደግሞ በምን ውስጥ እያለፍን እንደሆነ በቅጡ መጠየቅ በመጀመር መሆን ይገባዋል። ለሰብኣዊ ባሕርያት ብዙ ሰው ካለው ግንዛቤ ፍፁም በተቃራኒ ድርጊቶች በተሞላበት በዚህ ወቅት ሕይወት ቀላል አትሆንም። እያወራንለት ያለው ወቅት ከቀደሙት 20 ዓመታት በላይ ሕይወት አልነበረውም? ሕይወት ያላቸው ዓመታት ከዜግነትና ከአገር አንፃር ምን ዓይነት ቀለም ያላቸው ዓመታት ሊሆኑ ይችላሉ? ለኔ አብዛኛውን ሕዝብ የናጡ፣ የለወጡ፣ ጥልቅ ጥያቄ ውስጥ የከተቱ፣ ኃይል በተሞሉ ተለዋዋጭ ስሜቶች ያመሳቀሉ፣ ፋይዳቸው ምንም ይሁን ምን ቸል በማይባሉ ድርጊቶች የተሞሉ ሲሆኑ፥ በብሔራዊ ደረጃም ሕይወት የነበረባቸው የጊዜ አንጓዎች አድርጌ እወስዳቸዋለሁ። ይህ ጊዜ ሕይወት አለው። ነገር ግን በቅጡ መረዳት ይቸግራል። ጭካኔና ፍቅር። ሕይወትና ሞት መሳ ለመሳ ሲጓዙ ለዚያውም በእኩል ፍጥነት፣ ብዙ የማይገቡ ነገሮች ይፈለፈላሉ።
ያሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት ፍፁም በድርጊት የተሞሉ ነበሩ። ከፖለቲካዊ ኹነቶች ማዕዘን አንፃር ከቀደሙት ሀያ ዓመታት ጋር ሲታይም ምናልባት 1997 ብቻ ይሆናል ቀረብ ያለ ስሜት የሚሰጥ ድራማ የነበረበት ወቅት። ስለ 97 ተጨማሪ ሊባል የሚችለው ነገር ቅራኔዎች አብጠው አብጠው ዛሬም ድረስ እየተሸጋገሩ እንደነበረ የታየበት ወቅት ሊሆን ይችላል። ዛሬ ባለብዙ ቀለም ብዙ ድርጊቶች እያየን ነው። ለውጡ እንደ ማኅበረሰብ እየናጠን ነው፤ ራሳችንን የአብዮት ዘመን ዜጎች ሆነን አግኝተነዋል። ምን ዓይነት አብዮት? ሥር ነቀል አብዮት? ወይስ ማኅበራዊ አብዮት? ወይስ ሁለቱንም?
አብዮት የሚለው ቃል ምን ዓይነት ስሜት ይሰጠናል? አብዮት በኛ ፖለቲካ አውድ ከብዙ ሰው አፍ ከማይጠፉ ቃላት አንዱ ነው ብዬ አስባለሁ። ቃሉ ከንፈራቸው ላይ ጣዕም የሚፈጥርላቸው፣ ለውጥ የሚባለው ቃል ጉልበቱ እምብዛም የሚሆንባቸው። በየቀኑ በስሜት ወጀብ መመታቱን፣ በግልም በማኅበርም መናጥን መሻት፣ መዳፈር፣ ለአዲስ ነገር መራብ ለቃሉ የሚመጥን የሚሆንላቸው ብዙ ናቸው። አብዮት ቃሉ ብቻ የመከራ ግሳንግስ ይዞባቸው የሚመጣ፣ ከስውሩ አእምሮቸው ሰቆቃ እየበረበረ የሚኮለኩልላቸው ሰዎች ቁጥርም ቀላል አይደለም። ይህስ በመዳንና በመታመም ውስጥ ያለ መመሳቀል የአብዮት ዘመን ሰዎች ሥነ ልቦና የጋራ ስዕል አይደለም?
አብዮት። ቀዩ። ስር ነቀሉ ይሁን፣ ግራጫው። ማኅበራዊው። አብዮቶችን የጋራ የሚያደርጋቸው “ድንገተኛ” ምስቅልቅል የሚያደርግ ለውጥ ውስጥ ሕዝቡን ሁሉ በመክተታቸው ነው። ልዩነታቸው ደግሞ ግልጽ ነው። ቢያንስ በአንድ ግዙፍ መታያቸው ይለያያሉ። ቀዩ አብዮት ቀይ ነው። “ለቀና ምክንያት የሚፈስ ደም ይኖራል። መኖርም አለበት” ይላል። ኃይል (Violence) እና ማኅበራዊ ቅጥ አንባር ማጣት (chaos) መለያዎቹ መሆናቸው በአብዮተኞች ዘንድ የአብዮት አይቀሬ እውነታዎች ተደርገው እንደሚወሰዱ ታሪክ ከበቂ በላይ መዝግቧል። ኢትዮጵያ ደግሞ መመዝገብ ብቻ ሳይሆን እያገረሸ ትኩስ የሚሆን ትዝታ ያላት አገር ነች።
ዛሬ ሁሉን የሚለውጥ፣ ነባሩን ስርዓት “አሽቀንጥሮ የሚጥል” አብዮት ውስጥ አይደለንም። “የለም አብዮት ውስጥ ነን” የሚሉ ድምፆች እንዳሉ እረዳለሁ። እኒህ ሰዎች “በደነደነው ስርዓት ውስጥ መፈንቅለ ሥልጣን ተካሒዷል” የሚል አመክንዮ አላቸው። አንድ አንዴ ክርክሩ ጉንጭ አልፋ ንትርክ የሚመስላቸው ሰዎችም ቀላል በማይባል ቁጥር ሰምቻለሁ። ለነዚህ ሰዎች አብዮት ውስጥ ነን። ቀይ ሆነ ግራጫ ልዩነት አያመጣም። እንደዋዛ ያለንበት ሁኔታ ለውጥ ተብሎ ሲገለጽ ከደረጃ በታች እየተገለጸ እንደሆነ ስለሚያስቡ፣ አይመቻቸውም።
ለኔም እንደሚታየኝ ለውጥ ከፊቱ ሌላ ተቀፅላ ከሌለው በቀር በበቂ መንገድ አሁን ያለንበትን ማኅበራዊ እውነት የሚገልጸው አይመስለኝም። ስርዓቱን ከመሠረቱ የሚቀይር ባሕሪ ባይኖረውም በሒደቱ ደግሞ ብዙ ነውጦችን አሳይቷል። የአሁኑን ኹነት ለውጥም አልነው አብዮት ከበቂ በላይ ኃይል የተቀላለቀባቸው “ሐሳብን የመግለጽ” ወይም “ፍላጎትን የማስፈፀም” ሙከራዎች ታይተዋል። በዚህም የአብዮት ዘመን ሰዎች መሆናችንን አውቀናል። ራሳችንን ከራሳችን ፊት ለሕሊና ፍርድ አቁመናል። ለዚህ ሁሉ ጭካኔ አቅሙን ከየት አመጣን? አለን ብለን በፍቅር ስንጠቅሳቸው የኖርናቸውን ነገሮች መጠራጠር የአብዮት ዘመን ሰዎች ሆነን ራሳችንን ሰለማግኘታችን ሌላው ምልክት ነው።
የእኛ የቅርብ ታሪክ የሚያስታውሰን አብዮት ቀይ ነበር፣ ማኅበረሰብ በነበረው ስርዓት መገዛት ከማይችልበት ጫፍ የደረሰበት፤ በማኅበረሰብም ሆነ በመንግሥት አስተዳደር ዘዬና መዋቅር ሥር ነቀል ለውጥ የተካሔደበት ነበር። አሁን የምናየው ነገር እርግጠኛ መልኩ እና ተፈጥሮው ምን ዓይነት ነው? በእርግጠኝነት መልሱን ከባድ የሚያደርገው የለውጡ ኃይል ሕዝቡ ያለመገዛት፣ የአመፅ ስሜቱን በገፍ ከገለጸበት ገዢው ግንባር ውስጥ መውጣቱ ነው። የሆነው ሆኖ ሰፊ መሠረት ያለው ማኅበረሰባዊ አመፅ ባሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት መመልከታችን ማኅበረሰባዊ ይዘት ያለው አብዮት (social revolution) ውስጥ ራሳችንን እንዳገኘነው ተጨማሪው ምልክት ነው።
ያሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት “ሕዝብ ቶሎ ይረሳል” የሚለውን የማኪያቬሊ አስተምህሮ እንደወረደ የወሰዱት መሪዎች ከላይ እስከታች እንደነበሩን አሳይቶናል። ከ1997 እስከ 2007 የነበሩት ዓመታት በኹለት ማኅበራዊ አብዮቶች መሐከል የነበሩ እጥፋቶች (intervals) ነበሩ። ከ2007 በኋላ የነበሩት ዓመታት ያለማቋረጥ የቀጠሉ እምቢተኝነቶች ስለነበሩ ማኅበራዊ አብዮት በሆነ ጥልቀት መምጣት መጀመሩን፣ እኛም በስሱም ሆነ በደማቁም እየተለወጥን እንደነበረ ነግሮናል። በዚህች ቅፅበት እንኳን በእርግጠኝነት በስሱም በደማቁም እየተቀየርን ነው። ወዴት?
ስለአብዮት ስናወራ፣ የፈረንሳይን አብዮት ባንረሳው መልካም እንደሆነ የታሪክ ምሁራን ያስታውሱናል። አብዮት በደማቁ ማኅበረሰባዊ አወቃቀርን የመቀየር ዓላማ እንዳለው እንዳንረሳና ተስፋችንንም ሆነ ፍርሀታችንን በራሱ የበቃ ትንተና እንዳናደርገው ማስታወሱ ያስፈልገናል። የፈረንሳይ አብዮት በሦስት አንጓዎች የተዋቀረውን (በቀሳውስቱ፣ በልዑላኑና፣ በገበሬው ወገን የነበረውን በተቃርኖ የተሞላ ኢፍትሐዊ ግንኙነት ለማደላደል ሞክሯል።) ከዚያም በኋላ የተከሰቱ አብዮቶች ተመሳሳይ ተቃርኖና ተዛነቅ ያላቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በመሞከራቸው ሲዘከሩ ኖረዋል። ሁሉም ግን ምሉዕ አልነበሩም ማለት ይቻላል። ከዚህ እውነት ሁለት ነገር መማር ይቻላል ወይም መቻል ያለብን ይመስለኛል። እንደኛው አብዮት ያነሳቸውን ጥያቄዎች ሁሉ አይፈቱም። ሁለተኛ፣ አብዮት እንዳይቀለበስ ከበቂ በላይ የሆኑትን ጥያቄዎች መመለስ አለበት።
ስለአብዮት ስናወራ በሌላ ቋንቋ የሕዝብ የብሶት ፅዋ ስለመሙላቱ ነው የምናወራው፤ በዚህ ወቅት ራሳችንን ማግኘት ልብ ይሰቅላል። ብርሀንና ጨለማ በሚገፋፉበት፣ የጅምላ ፍርድን የመሰለ ጨለማ እና ተሰባሪ የሚመስል ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ብርሃንና ጨለማ ጎን ለጎን ሲሔዱ እያየን መሆኑን እናም የአብዮት ዘመን ላይ መሆናችንን እየነገሩን ነው። ውጥረቱ ቀላል አይደለም። የአብዮት ሰዓት ላይ ሁሉ ነገር ደማቅ ነው። ተስፋ ማድረጉም ሆነ ተስፋ መቁረጡ፣ ግራ መጋባቱም፣ ኃላፊነት መውሰድ ፣ ግድየለሽ መሆኑ፣ ማሴሩ ሳይቀር ደማቅ ነው።
አብዮትና ተቋማዊ ለውጥ
ከትናንት የተፋታ አብዮት የለም። ለውጥ ሲባል፣ ለዚያውም በአብዮት ደረጃ የሚገለጽ ለውጥ ያለኮተት እንደማይመጣ የሚያስታውሰን ወቅት ላይ ነን። ከቀዳሚው አብዮታችን እስካሁን በመጣንባቸው ዓመታት የጋርዮሽ ሥነ ልቦናዊ ባሕሪያት ይዘን መጥተናል። ፍርሀት፣ ዋስትና ማጣት፣ መገለል ለብዙኃኑ ተቀዳሚ ስሜቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እኔ ሌላ አንድ ላክልበት – ዕድሎችን የማባከንና የማጣት ሰቀቀን። ይህ ስሜት ለብዙዎቹ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ለሚያሳስባቸው ልሒቃን የከረመ ስሜት በመሆኑ ተስፋ በታየ ቁጥር ሁሉን ነገር ተቋማዊ ስለማድረግ መወትወት የተለመደ ነገር ነው። ከሰቀቀኑ የተፈጠረ ስሜት፣ ፍንጭ አይቶ የማጣት ስጋት የሚፈጥረው ጫና ካልሆነ በቀር ተቋማዊነት በአጭር ጊዜ በሁሉም ግድ በሚሉን ቦታዎች ሁሉ ሊፈጠር እንደማይችል ቢያንስ ለብዙዎች መረዳት አይቸግራቸውም። ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት አብዮት ያነሳቸውን ጥያቄዎች ሁሉ አይመልስም። ሁለተኛም ከበቂ በላይ የሆኑትን ጥያቄዎች ካልመለሰ፣ ማለትም የሚበዛውን አገራዊ አጀንዳ በሚያረካ መንገድ ካልመለሰ ይቀለበሳል። ስለዚህ? ልኂቃን በአብዮት ውስጥ እንኳን ሆኖ ሁሉን ማድረግ አይቻልምና ምርጫ የማይቀር እውነት መሆኑን መርሳት የለባቸውም። በዚህ ለውጥ ውስጥ ስለ ለውጡ አቅጣጫ የሚናገረው ሁሉ እንደመጣበት ዐውድና ፍላጎት “ተቋማዊ ለውጥ አሁን!” ይላል። ሁሉን “አሁኑኑ” ማድረግ ይቻላል? የሚቻልና የማይቻል ነገር አለመለየትም ሆነ መለየት አለመፈለግ የአብዮት አንዱ አስገራሚ. ባሕሪ መሆኑን ልብ ይሏል።
ተቋም ፅንሰ ሐሳቡ በራሱ ድንበር ያለው የማይመስል ውስብስብ ሐሳብ ነው። ለብዙዎች ተቋም ሲባል የሚመጣላቸው መደበኛው የመንግሥት ስርዓት ማሻሻል እንደሆነ እረዳለሁ። ከውስጣችን ወጥቶ እንድንጋፈጠው የተገደድነው ጭካኔ፣ ለከት የለሽ ዘረፋ፣ በጎጥ የተንሸዋረረ ዕይታ ሁሉ ከእሴት መሸርሸር እና መፍረስ ጋርም የተያያዘ ነው። እሱንም ለመለወጥ መሥራት “ተቋም” መገንባት መሆኑም ልብ ተብሎ ዋጋ ቢሰጠው መልካም ነው። ለኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ኢትዮጵያዊነት ነጋ ጠባ መወትወታቸው የተቋም ግንባታ አንድ አካል ነው። ተቋም፣ እምነት እና እሴት ማነፅ ነውና። ይህም ሆኖ መደበኛ፣ ሕጋዊ የሚባሉ አሠራሮችን መትከል ለውጡን መደበኛ፣ ሕጋዊ ማድረጉ የግድ ነው። ባሉት ሕጎች መሥራት ያልተቻለው በለስለሳዎቹ ተቋማዊ መሠረቶች (soft institutional foundations) ላይ አለመሥራቱ መሆኑን ላለመርሳት የመሞከርን አስፈላጊነት ለማንሳት ነው።
ሌላው ተቋማዊ እሳቤ በተግባር እንዳይኖረው የሚያደርገው አባዜ ለውጡን ከፖለቲካዊ ማዕዘን ብቻ የመመልከት ዝንባሌ ነው ። ሐሳባችን ሁሉ ትኩሳቱ ባለበት፣ ጫፍ የወጣ ዜና ባለበት ከሆነ የሚውለው የዜና ፈጣሪ ድርጊቶች ርሀብ እንጂ ስለ ተቋማዊ ለውጥ ማሰብና መታገል አይሆንም። እንቅስቃሴው ሥር የሰደደ ለውጥ ማምጣት ካለበት ተቋሞቻችን ውስጥ አስተዳደራዊ ለውጦች መከሰት አለባቸው ይህ ደግሞ ሞያዊ የለውጥ ምኅዳርና ሪፎርሞችን የማሳካት አቅም መፍጠርን ይመለከታል።
ግዙፉ ለውጥ ጎላ ብሎ እንደምናየው ዛፍ ነው። እሱን ማየት የሚቀለውን ያህል ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት የምንሻባቸውን የበዙ ተቋማት (ጫካዎቹን) ማየት ቀላል አይደለም። ደርዝ ባለው መንገድ ለመሞከር ስለአስተዳደራዊ ሪፎርሞች ጠለቅ ብለን መነጋገር መጀመር አለብን። የበኩሌን በሌላ ጽሑፍ እመለስበታለሁ።
እሸቱ ዱብ በቢዝነስ ስትራቴጂ፣ በፐብሊክ ፖሊሲና በኪነ-ጥበብ ርዕሰ ነገሮች ላይ ልዩ ፍላጎት ያላቸው የቢዝነስ አማካሪ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው eshetu9ethiopia@gmail.com ሊያገኟቸው ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011