ዩንቨርሲቲዎች ለዴሞክራሲ፦ አዎንታዊ ኃይሎች?

0
741

‘ለንደን ስኩል ኦቭ ኢኮኖሚክስ’ በ72 አገራት ያሉ፣ 1500 አካባቢዎች የሚገኙ፣ 15000 ዩንቨርስቲዎች ላይ እ.ኤ.አ. በ2016 ባደረገው ጥናት ዩኒቨርሲቲዎች በምጣኔ ሀብታዊ ፍሬያማነትም ይሁን ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን በማሳደግ ረገድ ቀጥተኛ አስተዋፅዖ እንዳላቸው አረጋግጧል። ከሕዝብ ብዛታቸው አንፃር ብዙ ዩንቨርስቲዎች ያሉባቸው አካባቢዎች የምጣኔ ሀብት ውጤታማነታቸው፣ የፈጠራ ደረጃቸው እና ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን በመገንባት አንፃር ያላቸው ደረጃ ከፍ ያለ እንደሆነ ጥናቱ አረጋግጧል፤ በተቃራኒው አነስተኛ የዩንቨርሲቲ ቁጥር ለብዙ ሕዝብ ያላቸው አካባቢዎች ደግሞ በሦስቱም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ተገኝተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የዴሞክራሲ እሴቶችን እንዲያብቡ የሚያደርጉት የተለያዩ ቦታዎችን ለተለያዩ ሰዎች፣ ለተለያዩ ሐሳቦች እና ለተለያዩ የሕይወት ዘዬዎች ክፍት እንዲሆኑ በማድረግ እንደሆነ በጥናቱ ተገልጧል።

በተመሳሳይ ዓመት፣ የኮመን ዌልዝ አገራት ዩንቨርስቲ አመራሮች በአክራ፣ ጋና ባደረጉት ጉባዔ ዩኒቨርሲቲዎች ዴሞክራሲን ለመገንባት ሊጫወቱ ስለሚችሉት ሚና ተነጋግረዋል። በወቅቱ የአውስትራሊያ ካቶሊክ ዩንቨርስቲ ምክትል ዋና ጸሐፊ ጆን ኪርክላንድ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ ዩንቨርስቲዎች ለዴሞክራሲ ግንባታ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱባቸውን መንገዶች ዘርዝረዋል። በመግቢያቸው ላይ “ለጊዜው ዴሞክራሲ ትክክለኛው እና የተሻለው የአስተዳደር ስርዓት ነው/አይደለም የሚለውን ክርክር እንግታውና ዩንቨርሲቲዎች ዴሞክራሲን እንዴት ማበረታታት እንደሚችሉ እንነጋገር” ይላሉ።

በዝርዝሩም፣ ኪርክላንድ እንደሚሉት፣ ዩኒቨርሲቲዎች ዴሞክራሲን ለማሳደግ አምስት መንገዶችን ይጠቀማሉ። እነዚህም፦ 1) የቀጣዩን ትውልድ መሪዎች በማሠልጠን፣ 2) የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱን ለማገዝ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ መረጃ በማቅረብ፣ 3) አካታች እና ኅብር ያለው ኅብረተሰብ በመፍጠር፣ 4) መሠረታዊ የሒስ ክኅሎትን በማሳደግ፣ እና 5) መቻቻልን በማበረታታት ናቸው። እነዚህ አስተዋፅዖዎቻቸው ዩንቨርስቲዎችን ከየትኛውም የአስተዳደር ስርዓት ይልቅ ዴሞክራሲን ለማምጣት የተሻለ ፋይዳ አላቸው።

በኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ አዎንታዊም፣ አሉታዊም የሆኑ ግጭቶች ይስተዋላሉ። የግጭቶቹ የአጭር ጊዜ ተፅዕኖ አስጨናቂ ቢመስልም ዘላቂ የፖለቲካ ስርዓት መምጣቱ ግን አይቀሬ ይመስላል። ለምሳሌ የ“መሬት ላራሹ” ጥያቄም ይሁን “ሕዝባዊ መንግሥት ይመሥረት” የሚሉ አጀንዳዎች የተመዘዙት ከዩንቨርስቲዎች መሆኑ ይታወቃል። በተጨማሪም “የብሔር ጥያቄ” በመባል የሚታወቀው የአካታችነት ጥያቄ የተወለደው ከዩኒቨርሲቲዎች ውይይት ውስጥ ነው።

በመሆኑም የአካዳሚያዊ ነጻነት ባሉባቸው ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች እና እሴቶች መውጣታቸው የማይቀር ነው። ለዚህም ነው ዩኒቨርሲቲዎች ለዴሞክራሲ ግንባታ አዎንታዊ ኃይሎች ናቸው የሚለው አስተያየት የሚያመዝነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here