“እስካሁን የተሞከረው አዲሱን አስተሳሰብ በአሮጌው መዋቅር ውስጥ [ማሠራት] ነው”

0
845

ዩናስ አዳዬ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም የአካዳሚክ ተባባሪ ዳይሬክተር ሆነው ላለፉት አራት ዓመታት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ዮናስ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋምን ከማቋቋም ጀምሮ የመጀመሪያው ዳይሬክተር ሆነው ለሁለት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፥ በርካታ ከሰላምና ደኅንነት ጋር በተያያዘ ያሳተሟቸው የጥናትና ምርምር ጽሑፎች አሏቸው። ዮናስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ፣ ኹለተኛ ዲግሪዎቻቸውን ደግሞ እንግሊዝኛን ቋንቋ በማስተማር ዘርፍ፣ በፖለቲካ እና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት እንዲሁም በሰላምና ደኅንነት ሠርተዋል። ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ብራድፎርድ ዩኒቨርሲቲ በሰላምና ደኅንነት ዙሪያ የሠሩት ዮናስ ከማስተማርና ምርምር ከማድረግ ባሻገር ለመገናኛ ብዙኃን በቅርበት ሙያቸውን ማዕከል ባደረጉ ጉዳዮች ዙሪያ ትንታኔና ማብራሪያዎች በመስጠት ንቁ ተሳታፊ ናቸው። የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከዮናስ ጋር ወቅታዊና አገራዊ የሰላምና ደኅንነት ሁኔታዎችን እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ቃለ መጠይቅ አቅርቦላቸው፣ መልሳቸውን እንደሚከተለው አሰናድቶታል።

አዲስ ማለዳ፡ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ለማቋቋም ለምን አስፈለገ?
ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፡ እንደሚታወቀው የ1997 ምርጫ ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ተፈጥሮ ነበር። በሌሎች አፍሪካ አገሮች ለምሳሌ በኬኒያ፣ በዚምባቡዌና ሌሎች አገሮች በተመሳሳይ ሁኔታና ወቅት ግጭቶች ተፈጥረው ነበር። ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ብሎም እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ምን ማድረግ አለብን በሚል ሐሳብ ተነስቶ በሰላምና ደኅንነት ዙሪያ ላይ ብቻ የሚያጠና ተቋም ያፈልጋል ተብሎ በመንግሥትም ደረጃ ታመነበት።

የኹለተኛ ዲግሪዬን በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት አጥንቼ እንደጨረስኩ የወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲተ ፕሬዘዳንት አንድሪያስ እሸቴ (ፕሮፌሰር) ተቋሙን እንዳቋቁም ኃላፊነት ሰጡኝ። መሠረቱን ኮስታሪካ ውስጥ ካደረረገው ‘ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፒስ’ ከተሰኘ የተባበሩት መንግሥታት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ተቋቋመ፤ እኔም የተቋሙ መሥራች ዳይሬክተር በመሆን አገልግያለሁ።

ተቋሙ ሲመሠረት ሦስት ምሰሦዎች ነበሩት። እነርሱም የሰላም ትምህርት፣ የሰላም ምርምር እና ማኅበረሰብን ተደራሽ ማድረግ የሚባሉ ሲሆኑ በቅርቡ የተቋሙን ዐሥረኛ ዓመት ስናከብር በአራተኛ ምሰሦነት የማኅበረሰብ ተሳትፎን ጨምረናል። ተቋሙ የኹለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ላይ መሠረት ያደረገ ሲሆን መርሐ ግብሮቹ መደበኛ፣ በሥራ ላይ መካከለኛ ደረጃ ባለሙያዎች የሚሰጥ ‘ኤግዘኪውቲቭ ማስተርስ’፣ ሉላዊ ጥናት እና አጫጭር ሥልጠናዎች ናቸው።
በጥናትና ምርምር ረገድ ተቋሙ ብዙ የምርምር ጽሑፎችን አሳትሟል።

በማኅበረሰብ ተደራሽነት ዙሪያ ዩኒቨርሲቲውን በሰፊው ያስተዋወቀውን ጣና ፎረም መጥቀስ ይቻላል። በዚህ መድረክ ላይ ሥልጣናቸውን የለቀቁ እና በሥልጣን ላይ ያሉ መሪዎች የሚካተቱበት መድረክ ሲሆን የአፍሪካን የሰላምና የደኅንነት ጉዳዮችን በተመለከተ በጥልቀት የሚያወያይ በባሕር ዳር ከተማና የሚዘጋጅ የሁለት ቀናት መድረክ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእናንተ ተቋም ተማሪ የነበሩ መሆናቸው ይታወሳል፤ ምን ዓይነት ተማሪ ነበሩ?
እንደ ተቋም እኛ አገልግዮች ነን፤ በዋናነት የምንሠራው ተማሪዎችን ማብቃት ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰዓት አክባሪ፣ በዕቅድ የሚመሩ፣ ጠንካራ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ሁል ጊዜ የሚያነቡ እንዲሁም ራዕይ ያላቸው መሪ ናቸው። ምክንያቱም ራዕይ የነበራቸው ተማሪ ስለነበሩ። አራቱንም የጻፏቸውን መጽሐፈት አንብቤላቸዋለው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሦስተኛ ዲግሪ የምርምር ጽሑፋቸው በ‘ሶሻል ካፒታል’ ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን የጻፉትንም በተግባር እየተገበሩት ነው ብዬ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። የመደመር ፍልስፍናቸውንም ሥራ ላይ እያዋሉት ነው።

ከሰላምና ደኅንነት አንፃር ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በአንድ ቃል ሽግግር ይባላል። በዓለም ላይ ፍፁም ሰላማዊና ደኅንነት ያለበት አገር የትም የለም። በሰላም መዘርዝር ውስጥ አንደኛ ተብለው የሚጠሩት የስካንዴኔቪያ አገሮች ወይም ደስታን በተመለከተ ቡታንግ መጥቀስ ይቻላል፤ እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች አሏቸው።
ሰላም ሁሉን ዐቀፍ ነው፤ ሰላም ብቻውንም አይጠናም። የኢትዮጵያ ሰላምም ካለችበት ቀጠና እንዲሁም ሉላዊ ዐውድ አንፃር አንፃራዊ ሰላም ያላት አገር ነች።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችንስ በተመለከተ ምን ይላሉ?
እኛ ግጭቶችን ስንከፋፍል መዋቅራዊ፣ ኢ-መዋቅራዊ፣ ጊዜያዊና ታሪካዊ በማለት ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት ግጭቶች የሽግግር ጊዜ ያመጣቸው ጊዜያዊና ኢ-መዋቅራዊ ናቸው። እነዚህ ግጭቶች የመሪዎች ቁርጠኝነትና የሕዝቡ መተባበር እስካለ ድረስ በቀላሉ ሊረግቡ የሚችሉ ናቸው።

በነገራችን ላይ መዋቅራዊ ስንል የእኩልነት ማጣት፤ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮች መገለል የሚያካትት ሲሆን እንደዚህ ዓይነት ግጭቶችን ለመፍታት በጣም አስቸጋሪና ብዙ ጊዜ የሚወስዱ ናቸው።
ለውጡን የሚቃወሙ ሁሉ ቀስ በቀስ ይለወጣሉ። ምክንያቱም ከልዩነት አንድነት፣ ከጎጥና ጎሳ ፖለቲካ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ አዋጭ ስለሆነ።

አሁን ኢትዮጵያ የምትገኝበት የሽግግር ወቅት በተመለከተ በሰላምና ደኅንነት ዙሪያ በተቋማችሁ ያደረጋችኋቸው ጥናቶች አሉ?
በሚገባ አሉ! ለምሳሌ “ነውጠኛ ብሔርተኝነትን እንዴት መከላከል ይቻላል” የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ (ረቡዕ፣ ጥር 15) አቅርበናል። የተጋነነ ብሔርተኝነት ወደ ነውጠኝነት ሲለወጥ ያኔ አደጋ ይፈጥራል።

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ተግዳሮት ብሔርተኝነት ነው ማለት ይቻላል?
ማንኛውም ነገር በጣም ሲጋነን ወይም ከልክ ሲያልፍ አደገኛ መሆኑ አይቀርም። ፅንፈኛ ስንል ራሱ ከተለመደው የወጣ ማለታችን ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ አብሮ ለዘመናት ተጋብተው የሚኖሩ ሰዎችን ‘አንተ የእኔ ወገን አይደለህም፣ የእኔን ቋንቋ አትናገርም፣ ከዚህ አካባቢ ውጣ’ ማለት በአገራችን አልነበረም። ባሕላችን ማቀፍ፣ መከባበር፣ ተጋብቶ አብሮ መኖር ያለበት ነው። በአጭሩ ብሔርተኝነቱ ለአገራችን ተግዳሮት ነው።

ነውጠኛ ወይም ፅንፈኛ ብሔርተኝነት መገለጫቹ ምንድን ናቸው?
መቻቻል ሲቀር፣ ጥላቻ ሲሰፍን፣ ለማስፈራራት ብሎ ፍርሐትን እንዲፈጠር ማድረግ፣ ሁሉንም ነገር ከራስ ጎሳ አንፃር መመልከት የመሳሰሉት ናቸው።
በአገራችን የብሔርተኝነት መሠረታዊ ምንጩ የክልሎች በቋንቋና በጎሳ መካለል ነው። ራሱ ክልል የሚለው ቃል የሚያገለግለው ለእንስሳት ነው።
የክልሎችን ሕገ መንግሥት ብትወሰድ – ለምሳሌ የጋምቤላን፣ የክልሉ ማንነት የሚለካው በአምስቱ ብሔረሰቦች ብቻ ነው፤ ከዛ ውጪ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡት ሕዝቦች ጋምቤላ ውስጥ በክልሉ ምክር ቤት አባልነት ሊመረጡ አይችሉም። በርግጥ አብሮ መኖሩ እንደሚያዋጣ ሲገነዘቡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዚህ ጋር በተያያዘ መለሳለስ ይታያል።

ፖለቲካው አስተሳሰብ፣ አወቃቀር፣ ጎሳን መሠረት ያደረገው ፌደራሊዝም፣ መሬትን ከማንነት ጋር ማያያዙ ለነውጠኛ ብሔርተኝነት መሠረት ናቸው።
ሌላው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አሉታዊ የሆኑ ነገሮች አሉ፤ አንድነቱንና አብሮ መኖሩን የሚጎዱ። ለምሳሌ አንቀጽ 39። በደቡብ ክልል ይሔንን መሠረት አድርገው ነው ሃምሳ ስድስቱም [ብሔሮች] ክልል የመሆን ጥያቄ የሚያነሱት።

ባለንበት የሽግግር ወቅት ተስፋ ያለውን ያክል ተስፋውን የሚያጨልሙ ሥጋቶች አሉ። ችግር አፈታት በተመለከተ የተወሰዱ እርምጃዎች ፀጥታና ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ምን ጉድለት አለባቸው?
አንድ ነገር ስትሠራ ሰዋዊ ውስንነት ይኖራል። ሽግግር ሲካሔድ ሥጋት አብሮ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። በሽግግሩ እንደጉድለት የሚታዩና መሻሻል አለባቸው የምንላቸው በግልጽ እንደምናየው እስካሁን የተሞከረው አዲሱን አስተሳሰብ በአሮጌው መዋቅር ውስጥ ማሠራት ነው። በሌላ አነጋገር በአሮጌው አቁማዳ ውስጥ አዲስ ወይን እንደመጨመር ማለት ነው። ይህ ማለት አዲሱ አመራር እየሠራ ያለው ቅድመ መጋቢት 24/2010 በነበረው መዋቅር ነው።

ስለ መደመር፣ ስለ ይቅርታ እና ስለ መሳሰሉት ጉዳይ ለይተው የማያውቁ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ አመራሮች አሉ። ይህም እንደ አንድ ተግዳሮት ወይም ጉድለት ሊወሰድ ይችላል።
ሌላው ለውጡ ወደ ታችኛው እርከን አልወረደም፤ አካሔዳቸውን ያለወጡት ከሕግ በላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ በፍጥነት መፈፀም ያስፈልጋል።

አሁን ትንሽ ተብለው የሚታሰቡ ግጭቶች ጊዜ በሔደ ቁጥር መልካቸውን እየለወጡ ስለሚሔዱ ነገ መዋቅራዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ በጊዜ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ አምናና ካቻምና የነበረው የፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ አንፃር አሁን ላይ ወደፊት እየሔድን ነው ወይንስ ወደኋላ እየተመለስን?
የሰላምና ደኅንነት መሠረት ተስፋ መስጠቱ ነው። የምሁራን ተሳትፎ፣ ዓለም ዐቀፍ ድጋፍ፣ ቀጣናዊ ሒደትን በተመለከተ የታዩ መሻሻሎች እንዲሁም ሌሎች አገሮች ከኢትዮጵያ እንማር እያሉ ያሉበትን ሁኔታ በአጠቃላይ የሚያመለክቱት ኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ መገኘቷን የሚያሳዩ ናቸው።

መታወቅ ያለበት አምባገነን በሆነ ስርዓት ውስጥ ለቆየ ሕዝብ ሁኔታዎች ወዲያው ሲለወጡ አብሮ የሚፈነዱ ብዙ ነገሮች አሉ። ሶሪያን፣ ግብፅንና ሊቢያን ብንወስድ እኛ እንደነሱ አልሆንንም። እንደተጠበቀው ግጭት ያልተፈጠረበት ምክንያት በሕዝባችን መካከል ያለው መተሳሰር፣ መገመድ፣ መሰናሰል ውስጣችንን የሚይዙ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ የእምነት መሠረቶች ስላሉን ነው።

አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ካለፈው ዓመትም ሆነ ከዛ በፊት ከነበረው ጋር ስናወዳድረው ተስፋ ሰጪ ነው። ወደ ፊትም የተሸለ ተስፋ እንዳለ ማየት ይቻላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጎላ ለመጣው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ግጭትና አለመረጋጋት ዋና መነሻ ምክንያት ምንድን ነው?
ከዛሬ ዐሥራ አምስት ቀን በፊት ባዘጋጀነው የሰላም ኮንፈረንስ ከሁሌ ቦራ ዩኒቨርሲቲ ከመጡ ሰዎች ጋር ተነጋግሬያለሁ፤ ቃለ መጠይቅም አድርጊያለው። በተማሪዎች ላይ ይህ ነው የሚባል ጥፋት አላገኘሁባቸውም። የጥፋቱ መነሻ ቅድም ወዳልኩት ይመልሰኛል።

ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲ መኝታ ቤት የሚመደቡት በብሔር ነው፤ ምግብ ቤት የሚሔዱት በብሔር ተደራጅተው ነው፤ አንድ ለአምስት የሚባለውም መዋቅር በብሔር ነው። አንዱ የሌላውን ባሕል እንዲያውቅ ዕድል አልተሰጣቸውም። እርስ በርስ መስተጋብር እንዳይፈጥሩ ታቅዶና ታስቦ ጎሰኝነት እንዲስፋፋ ተደርጓል። በተማሪዎቹ አዕምሮ ውስጥ ያለው ይኸው ነው።

ስለዚህ እነዚህ ልጆች 27 ዓመት ሲቀነቀን የነበረው ፍልስፍና በአዕምሯቸው ውስጥ አለ። በዋናነት ተማሪዎችን መዋቅራዊ ችግር አስቀድሞ የነበረው ችግር ስላለ የዛ ተፅዕኖ ውጤት ነው። ይህንንም ችግር የሚፈጥር፣ እንዲፈጠር የሚያደርግ ኃይልም አለ።

በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ ያሉት አስተዳደራዊ ችግሮችስ?
የዩኒቨርሲቲዎቹን አስተዳደር በተመለከተ አልፈርድባቸውም። በአንድ ወቅት የትምህርት ሚኒስትር በብቃት መሆን አለበት፤ ቢያንስ ዶክትር መሆን ይጠበቅበታል ለሚለው ምላሽ የኢሕአዴግ ዓላማን እስካስፈፀመ ድረስ ምንም መሆን እንደሚቻል የተገለጸው ፍልስፍና ነው ያለው።

ዩኒቨርሲቲ ሹመት በፖለቲካ ታማኝነት፣ በጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኝነት እንጂ በትምህርት ዝግጅት፣ በክኅሎት፣ በብቃት ላይ የተመሠረተ አልነበረም።
አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በብቃትና በምርጫ ፕሬዘዳንት መሆን ተጀምሯል፤ ይሄ መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አልወረደም።
ይሁንና ለችግሩ በዋናነት ተጠያቂ የሚሆነው ፖለቲካው ነው። በተለይ ቅድመ መጋቢት 2010 የነበረው አመራር።

‘የአካዳሚ’ ነጻነትንስ በተመለከተ?
ቅድመ መጋቢት 2010 አንተ ራስህ እዚህ አትመጣም ነበር፤ እኔም በነጻነት ላናግርህ አልችልም ነበር። ድኅረ መጋቢት 2010 የፍርሐት ደመና ተገፎ ሕዝቡ በነጻነት እየተናገረ ነው ያለው። በሕዝብና መንግሥትም መካከል እምነት እየተፈጠረ መጣ፣ መተማመን መጣ። ይሄ ደግሞ ለአንደ አገር ዕድገት መሠረት ነው። ነገሮች ጎልተው የሚወጡት በ‘አካዳሚክ’ ነጻነት ውስጥ ነው። የትምህርት ተቋማት እንደ አብሪ ኮከብ ናቸው። መሪዎች የሚወጡት ከዩኒቨርሲቲ ነው።

በአንፃራዊነት በአሁኑ ሰዓት በአደባባይ መደገፍም መቃወቃወም ተችሏል። በአጭሩ በፊት በምታስበው ትታሠራለህ፤ አሁን ግን የሕሊና እስረኞች የተፈቱበትን ሁኔታ ነው የምታየው።

አካዳሚክ ነጻነቱ በዩኒቨርሲቲም ሆነ በኮሌጆች በኃላፊነት ምሁራን መናገር፣ መጻፍ እንደሚችሉ ከምስክሮቹ ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ። ራሳችን እውነትን መናገር ነው።
ያለፈው ሁሉ መጥፎ ነበር ማለትም እንዳሆነ መታወቅ አለበት፤ አሁን ግን መሻሻል ታይቷል።

በቅርቡ የተቋቋው ሰላም ሚኒስቴር መኖር ፈይዳ ምንድን ነው? ከተቋማችሁስ ጋር ያለው ግንኙነት ምን እንዴት ይገለጻል?
የሰላም ሚኒስቴር በአፍሪካ የመጀመሪያው እንደሆነ በብዙዎች ይታመናል። በናይጄሪያ የደስተኝነት ሚኒስቴር ለማቋቋም ፓርላማ መቅረቡን አስታውሳለሁ፤ ይሁንና ይፅደቅ አይፅደቅ መረጃ የለኝም።

ለማንኛውም የሰላም ሚኒስቴር መቋቋም የሚያመለክተው የመንግሥቱን ቁርጠኝነት ነው። የኢትዮጵያ ችግር የሰላም ችግር እንደሆነ፣ አመራሩ ምን ያክል ለሰላም የቆረጠ እንደሆነ፣ ምን ያክል ለሰላም እንደቆመ ማሳያ ነው።

ኹለተኛ ሰላም ለብቻው ከአንድ አገር ብቻ የሚመነጭ አይደለም። የደቡብ ሱዳን ፣ የሶማሊያ፣ የኬኒያ፣ የኤርትራ ወዘተ. ችግሮች የኢትዮጵያ እንደዚሁም የእኛ ችግር ደግሞ የእነሱ ችግር ነው። ሰላም በመሠረቱ ሁሉን ዐቀፍ ነው። ስለዚህ ያንን ተገንዝቦ የኢትዮጵያ ችግር ለመፍታት ሰላም እንዲያስፈልግ በማወቅ ታምኖበታል።
የሰላም ሚኒስቴር ከተቋማችን ጋር የሥራ ግንኙነት አለው። ‘ፒስ ቲንክ ታንክ’ (የሠላም የጥናት ተቋም) ብለን አቋቁመናል። የሰሞኑም ሆነ ከ15 በቀናት በፊት የተካሔዱት ዝግጅቶች በሰላምና በግጭት ዙሪያ የተሠሩ የዶክትሬትና የማስተርስ ዲግሪዎች ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳጥረን አቅርበናል። ሚኒስቴሩ ደግሞ ወደ ታችኛው ክፍል ድረስ እንዲወርድ ለማድረግ እየሠራ ለሚገኘው ሥራ ያግዘዋል፤ ምክንያቱም ብዙዎቹ በባሕላዊ የግጭት አፈታት ላይ ስለሚያተኩሩ ነው። በሰላም ግንባታ ላይ የተሠሩ የምርምር ወረቀቶች ደግሞ ወደ ፖሊሲ ለመቀየር ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ኢትዮጵያ ባለችበት ስትራቴጂያዊ የመልክዓ ምድራዊ ፖለቲካ አቀማመጥ አንፃር በቀጠናው ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ከእያንዳንዱ አገራት ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያለውን በንፅፅር ቢያስቀምጡልን?
መጥፎ ነገር እንደሚጋባው ሁሉ መልካም ነገርም ይጋባል፤ ክፋቱ ግን መልካሙ ነገር ልክ እንደ መጥፎው ነገር ቶሎ አይጋባም። በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የሥልጣን ሽግግር ሲኖር በቀጠናው ላይ በጎ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ አሳድሯልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አሉታዊ ነገርም እንደዚሁ በቀጠናው ባሉ አገራት ላይ የራሱ ተፅዕኖ ያሳድራል።

ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳን የጎሳ ፖለቲካ እየተጋባ ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ፌደራሊዝሙ ጎሳን መሠረት ያደረገ እንዳይሆን ተደረገ። ኢትዮጵያ ለቀጠናው በመልክዓ ምድርም ይሁን በፖለቲካው ማዕከላዊ ስለሆነች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መልካም ጅምር ለብዙዎች መልካም አርዓያነትን እያሰራጨ ይገኛል።
ኢትየጵያ ለሰላም የምታደርገው አበርክቶ ለአካባቢው አገሮች ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። ኢትዮጵያ ለቀጠናው የሰላም ምሳሌ እንድትሆን፣ ፖለቲካዊ ውሕደት የማምጣት ትልቅ ተስፋ እንደሚያመጣ እናያለን። ቀጠናው በኢትዮጵያ፥ ኢትዮጵያ በቀጠናው ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።

አሁን ላለንበት ሉላዊነት ብሔርተኝነት እንደተግዳሮት ይታያል እዚህ ላይ ምንድን ይላሉ?
አዎ! ብሔርተኝነት ለሉላዊነት ተግዳሮት ነው። ይህንን በተመለከተ ሦስት መጽሐፍት ተጽፈዋል። የፓንጋጅ ሚሽራ “Age of Anger”፣ የፍራንሲስ ፉኩያማ “Identity” እና የሪቻርድ ሀስ “A world in Disarray” የሦስቱ አጠቃላይ ሐሳብ አሁን እያሠንራራ የመጣው ብሔርተኝነት ከእኛ ዘር ወደኋላ ቀርቷል ትርክት፣ ከታሪክ አለመማርና እና መንግሥታት የሚጠበቅባቸውን ለኅብረተሰቡ ጥያቄ ስለማይመልሱ መሆኑን አስቀምጠዋል። በርግጥ መጽሐፍቶቹ እንደዚህ በአጭር እንደተናገርኩት ሳይሆን ሰፊ ሐሳቦችን የያዙ ናቸው።

የሆነው ሆኖ ሉላዊነት ለቴክኖሎጂ መስፋፋት ለምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ጠቃሚ ሆኖ ሳለ ሉላዊነት በመካከል ሲጠለፍ ግን ሌላ ችግር ይፈጥራል።
ለዚህ ነው የተካረረ ጎሰኝነት ሲፈጠር የተካረረ ኢትዮጵያዊነት መኖሩ የማይቀረው፤ ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here