የሐመር እና ተፈጥሮ ግብግብ

0
926

በቀይ አፈርና በስብ የተለወሰ ጥምል ፀጉር ያላት፣ ጣቶቿ በቀለበት፣ አንገቷ በአሸን ክታብ ያሸበረቀውና ደረቷ በፍየል ቆዳ የተሸፈነው የ55 ዓመቷ ቱርሚ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከንጋት እስከ ከሰዓት ያለውን ቀኗን የምታሳልፈው የጓሮ አትክልቶችን በመትከልና በመንከባከብ ነው።

በርግጥ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሐመር ወረዳ ለሚኖሩ እንደ ቱርሚ ያሉ እናቶችና እህቶች የጓሮ አትክልት መትከል፣ ለገበያ አቅርቦ መሸጥና ለቤት ውስጥ ፍጆታ መጠቀም ያልተለመደ ነገር ነበር። አሁን ግን የዕለት ተለት ኑሯቸው አካል ሆኗል። ከጥቂት ዓመታት በፊት “የጓሮ አትክልት በምንኖርበት አካባቢ ያልተለመደ ነገር ነበር” የምትለው ቱርሚ፥ ወንዶቹ ከብት በማርባት፣ ሴቶቹ ደግሞ ከቤት ውስጥ ሥራ በተጨማሪ ማሽላና በቆሎ በመትከል ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር ታስታወሳለች።
በአንድ ነጥብ 13 ሔክታር መሬት ላይ በማኅበር ተደራጅተውና በብሬስድ ፕሮጀክት ታቅፈው የጓሮ አትክል የሚያለሙት እንደ ቱርሚ ያሉ የሐመር ነዋሪዎች ምርቱን ለገበያ አቅርበው ገቢ ማግኘት፣ ለቤት ውስጥ ፍጆታ መጠቀምና ከሽያጭ የሚያገኙትን ገቢ መቆጠብ ጀምረዋል። የጓሮ አትክልታቸውን ለማልማትም የጠብታ መስኖን እየተጠቀሙ ይገኛሉ።

ከቁጠባ ማኅበራቸው መካከልም አንዱ ኒሺማኮ ሲሆን በውስጡ 6 ሴቶችና 7 ወንዶች፣ በድምሩ 13 አባላት አሉት። የማኅበሩ አባላት በየሳምንቱ እየተገናኙ 12 ብር የሚቆጥቡ ሲሆን፥ ተቀማጭ ገንዘባቸውን ወደፊት በድርቅ ወይንም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰት ሌላ አደጋን ተቋቁመው ለማለፍ እንደሚጠቀሙበት ይናገራሉ።

ከማኅበሩ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ኡርጎ ቤዶ “ከአራት ወር በፊት ያለማነውን የጓሮ አትክል ለገበያ አቅርበን ያገኘነውን ገቢ ቆጥበናል። በቀጣይ ከምናለማው ምርት የሚገኘውን ገቢም ለመቆጠብ ነው የምናስበው። ብሩን በኋላ ላይ ድርቅ ሲመጣ ከሌላ አካባቢ ምግብ ገዝተን የችግሩን ጊዜ እናሳልፍበታለን” በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚፍጨረጨሩት ሐመሮች ብቻ አይደሉም። በርግጥ፣ በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ስብሰባዎች ላይ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆነውና የዓለማችን ስጋት እየሆነው የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የዝናብ ወቅት መዛባት፣ ድርቅና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህ ጉዳቶች መካከል ድርቅ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ያጠቃ ሲሆን፥ ባሳለፍናቸው ዓመታት በድርቅ ከተጠቁት አካባቢዎች መካከል የሐመር ወረዳ አንዱ ነው።

ወደ ሰማንያ ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ የሚኖርባት ሐመር፣ ሕዝቦቿ በአርብቶ አደርነት እና በከፊል እርሻ ላይ በመሠማራት ይተዳደራሉ። ሐመሮች የቀንድ ከብት፣ ፍየልና በግ በዋናነት የሚያረቡ ሲሆን ማሽላና በቆሎ ደግሞ በዝናብ ወቅት ይዘራሉ። ባለፉት ዓመታት ምንም እንኳን የሐመር አካባቢ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተደጋጋሚ ለድርቅ ቢዳረግም፥ የአየር ንብረት ለውጡን ለመቋቋምና የድርቁን ጊዜ በስኬት ለማለፍ ቀድመው ጥንቃቄ የሚያደርጉበት ዘመናዊ ዘዴ አልነበረም።
ይህንን በመረዳት በ2007 ከደቡብ ክልል አስተዳደር ጋር ሥምምነት ላይ ደርሶ ሥራውን የጀመረው ፋርም አፍሪካ ብሬስድ በተሰኘው ፕሮጀክቱ ሥር ያስቀመጠው ዋና ግብ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙና ወደፊት ለሚከሰቱ እንደ ድርቅ ያሉ ችግሮች የአካባቢው ነዋሪዎች ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ የሚችሉበትን ዘዴ ማስተማር ነው።

ይህንን ለማድረግ ደግሞ የአካባቢውን ነዋሪዎች የአኗኗር ዘዬ እንዲሻሻል ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል። የብሬስድ ፕሮጀክት ቡድን መሪ የሆኑት ንጉሡ አክሊሉ እንደገለጹት “የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደየአካባቢው ሁኔታ እና እንደየማኅበረሰቡ የአኗኗ ዘዬ ይለያያሉ። ለምሳሌ ከብት በማርባት የሚተዳደሩ አካባቢዎች በድርቅ ወቅት ዋነኛ ችግራቸው ከብቶቻቸው የሚበሉት ግጦሽ አለማግኘት ነው። ስለዚህ ይህንን ችግር ለመፍታት የድርቅ ወቅት ከመምጣቱ በፊት ለከብቶች ምግብ የሚሆን በቂ ሳር ማጠራቀም፣ የአካባቢው መሬት በግጦሽ ብዛት እንዳይጎዳ ከልሎ ተገቢውን እንክብካቤ መስጠትና ነዋሪዎች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከአየር ንብረትና ፀባይ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማቅረብ ያስፈልጋል” ብለዋል።

እንዲሁም በጂንካ የብሬስድ ፕሮጀት አስተባባሪ የሆነው አምሳሉ አማን የዛሬ ሦስት ዓመት በሐመር ፕሮጀክቱን ለመተግበር ሲታቀድ አራት ዋና ዋና ዓላማዎች እንደነበሩት ይናገራል። ከነዚህ ዓላማዎች መካከል የመጀመሪያው የሐመር ነዋሪዎችን የገንዘብ አቅም በቁጠባ፣ በንግድና በብድር ማጎልበት ነው። ለዚሁም ይረዳ ዘንድ የሐመር ነዋሪዎች በቡድን እየተደራጁ እንዲቆጥቡ ሥልጠና የመስጠት ሥራዎች ተሠርተዋል።

“እኛ ገንዘብ ሳይሆን ዕውቀት ነው የሰጠናቸው” ይላል አምሳሉ። በውበታቸው፣ ለየት ባለ የፀጉር አሠራራቸው፣ በኢቫንጋዲ ጭፈራና በበሬ ዝላይ የሚታወቁት ሐመሮች መኖሪያ አካባቢ በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑት አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። ነገር ግን የገንዘብን ጥቅም ያልተረዱ እንዲሁም የወረቀት ገንዘብ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርቡ ያዩ የመንደሩ ነዋሪዎች አሉ። ከነዚህ ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ብር በቅርቡ እንዳየ ይናገራል። “ብር ምግብ ነው” የሚለው ይህ ወጣት በፋርም አፍሪካ ባገኘው ሥልጠና መሠረት ፍየል ገዝቶ በማደለብ መልሶ ከሸጠው በኋላ ያገኘውን ትርፍ መቆጠቡን ይናገራል። ተጨማሪ ስልጠና ቢሰጣቸው ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆን ያምናል።

በተጨማሪም ፋርም አፍሪካ ከኦሞ ማክሮ ፋይናንስ ጋር በመተባበር የሐመር ነዋሪዎች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ነገር ግን ብድር ለመውሰድ የፈለገ ሰው የሚበደረውን ገንዘብ ሀያ በመቶ ያህል መቆጠብ አለበት። የፕሮጀክቱ ኹለተኛ ዓላማ ነዋሪዎች የተፈጥሮ ሀብታቸውን እንዲንከባከቡ፣ እንዲያለሙና የተጎዱ አካባቢዎችን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ የማቋቋምና በጂንካ ኤፍኤም በኩል በየዐሥር ቀኑ ከአየር ንብረትና ፀባይ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የመስጠት ሥራ ነው። ሦስተኛው ደግሞ ሥራ አጥ ወጣቶች በአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በመሠማራት ገቢ እንዲያገኙ ማስቻል ሲሆን፥ ይህ ግን በሐመር ተግባራዊ አልሆነም። የመጨረሻው ዓላማ የስኬት ታሪኮችን በማደራጀት ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ማሰራጨት ነው።

አምሳሉ ከሦስት ወር በኋላ ፋርም አፍሪካ አካባቢውን ቢለቅም ፕሮጀክቱን በሐመር አካባቢ መተግበር ሲጀምር ያስቀመጣቸው ግቦች እንደሚሳኩና የተጀመሩት ሥራዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ያምናል። ነገር ግን ፕሮጀክቱ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት ቀጣይነት ያላቸውን ክትትሎች ማድረግ አለበት ባይ ነው። አምሳሉ “ምንም እንኳን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁን የጀመሩትን ሥራ እንደሚቀጥሉት ባምንም ፋርም አፍሪካ ፕሮጀክቱን አጠናቆ ከሐመር ሲወጣ መንግሥት ቀጣይ ሥራዎችን መሥራት አለበት” ይላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here