የ2013 በጀት ዓመት ወጭ ንግድ አፈፃፀም 3 ነጥብ 62 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ በማስገኘት የዕቅዱን 88 በመቶ ማሳካቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የዕቅድ አፈፃፀሙ ከ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ19 ነጥብ 5 በመቶ ወይም የ592 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል፡፡
የወጭ ንግድ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ዛሬ ለጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ እንደገለፁት የግብርና ዘርፍ 2 ነጥብ 47 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማስመዝገብ ከአጠቃላይ የወጭ ንግድ ገቢው 68 በመቶ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 390 ሚሊየን በማስመዝገብ የእቅዱን 67 በመቶ ከአጠቃላይ የወጭ ንግድ ገቢው 11 በመቶ፣ የማዕድን ዘርፍ 668 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ በማስመዝገብ የዕቅዱን 102 በመቶ ከአጠቃላይ የወጭ ንግድ ገቢው 18 በመቶ ድርሻ ሲኖራቸው 93 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያስገኙ ሲሆን የአፈፃፀሙን ቀሪ 3 በመቶ ድርሻ የሚይዙት የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከአጠቃላይ የወጭ ንግድ ገቢው 83 በመቶ የገቢ ድርሻውን ያስመዘገቡ ምርቶች ቡና 25 በመቶ፣ አበባ 13 በመቶ፣ የቅባት እህሎች 9 በመቶ፣ ጫት 11 በመቶ፣ የጥራጥሬ ሰብሎች 6 በመቶ እና ወርቅ 19 በመቶ በመያዝ ከወጭ ንግዱ አጠቃላይ ገቢ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ጃፓን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሲንጋፖር፣ እስራኤል እና ቻይና የወጨ የምርቶቹ መዳረሻ ሀገራት መሆናቸውንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።





