ብዙ የሚቀረው ባለብዙ ተስፋው ‹ሞዴሊንግ›

0
833

ሞዴሊንግ በሌሎቸ አገሮች ውስጥ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ እንደ አንድ የሥራ ዘረፍ እየዳበረ የመጣ ሙያ ዘርፍ ነው። ዘርፉ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚተገበር ቢሆንም እንደ ሥራ ግን መታየት የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። በተለይ ባለፉት ዐሥር ዓመታት በኅብረተሰቡ የኑሮ ዘዬ መለወጥ ምክንያት የሞዴሊንግ ሥራ ለብዙ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ተስፋ ሰጪ የሥራ ዘርፍ እየሆነ ይገኛል።

ሞዴሎች በማስታወቂያ፣ በፋሽን ትዕይንቶችና በሌሎች ሥራዎች ውስጥ ተካቶ ቢቀርብም ቀላል በማይባል የማኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሙያው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሞያዎች ይናገራሉ። ነገር ግን ባለፉት ዐሥር ዓመታት ዓለም ዐቀፍ መስተጋብሩ እየጨመረ ሲሄድና የኢትዮጵያ ፋሽን በዓለም እየታወቀ ሲመጣ ሞዴሊንግም በዚሁ ሰበብ እንደ ሞያ እየታወቀ መጥቷል። ድሮ ወጣት ሴቶች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት እንደ ሥራ ማፈላለጊያ የሚሠማሩበት መሆኑ ቀርቶ አሁን ወንዶችም ሴቶችም በሥራው ላይ መግባት ጀምረዋል። በተጨማሪም ትምህርት ቤቶችና የማሰልጠኛ ተቋማት ወጣቶችን በሞዴሊንግ ዘርፍ ለማሰልጠን እየተከፈቱ ይገኛሉ። አቢሲኒያ የሥነ ጥበብና የሙያ ማሰልጠኛ ተቋም፣ ‹ኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ› እና ፍቅር ዲዛይን ከሚጠቀሱት ተቋማት መካከል ይገኛሉ።
ገነት ከበደ የአቢሲኒያ የሥነ ጥበብና የሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያዩት ትልቁ ለውጥ ከሴቶች እኩል ወንዶች ወደ ዘረፉ መግባታቸው እንደሆነ የሚናገሩት ገነት ‹‹ሞዴሊንግ እንደሥራ ዘርፍ መቆጠር እየተጀመረ ነው፤ በማኅበረሰቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በተማሪ ቤተሰቦች ዘንድም ተቀባይነቱ እየጨመረ ነው›› ይላሉ።

እንደ ገነት አስተያየት አቢሲኒያ የሥነ ጥበብና የሙያ ማሰልጠኛ ተቋም በአሁኑ ጊዜ ሞዴሎች በሥራው ላይ ብዙ ምርጫ ማግኘታቸውም ሥራው ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሏል ይላሉ። ገነት ‹‹ፋሽን ብቻ መሥራት የለባቸውም፤ ማስታወቂያ፣ የምርት ወይም የአገልግሎት አምባሳደርነትም ሆነ በግብይት ዘመቻ ሥራ [‹ማርኬቲንግ ካምፔን›] ላይ መሳተፍ ይችላሉ›› በማለት ያሉትን አማራጮችም ዘርዝረዋል።

እንደ አቢሲኒያ የመሳሰሉት ተቋማት ሞዴሊንግ ሲስተምሩ እነዚህን ዘርፎች በመረዳት መሆኑንም ገነት ያሰምሩበታል። ‹‹ተማሪዎች እንዴት መራመድ እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን በራስ መተማመን እንዲኖራቸው ያስተምራሉ።›› በማለት ገነት በምሳሌ ያስረዳሉ። ከእነዚህ ተቋማት የተመረቁት ተማሪዎች በብዙ ዘርፎች ቢሠሩም ማኅበረሰቡ ለሞዴሊንግ ያለው አስተያየት እየተለወጠ ቢሆንም ብዙ ሰዎች ግን እስካሁን የመጣው ለውጥ በቂ እንዳልሆነ ያስባሉ።
ቤተልሔም አበበ የ20 ዓመት ወጣት ስትሆን የዩንቨርስቲ ተማሪ ናት። ወደ ፊት በሞዴሊንግ ሥራ መሰማራት ብትፈልግም ፋላጎቷን በዙሪያዋ ካለው እውነታ ጋር ለማየት ተገዳለች። ሥራውን በጣም ብትፈልገውም የቤተሰቧን አስተያየትና ከማኅበረሰቡ ያለው ጫና ሐሳብ ሆኖባታል። ‹‹አሁን ተማሪ ብሆንም ወደ ፊት ሞዴል መሆን እፈልጋለሁ። ይህም ከድሮ ጀምሮ የነበረኝ ፈላጎት ነው። ልጅ እያለሁ በቴሌቭዥንና በመጽሔቶች የማያቸው ምስሎች በጣም ደስ ይሉኝ ስለነበር እንደዛ መሆን ነው የምፈልገው›› ብላለች።

ቤተሰቦቿ በቀጥታ ሥራውን እንዳትሠራ ባይከለክሏትም ሙሉ ትኩረቷን ለትምህርቷ እንድሰጥ ግን ተጽዕኖ ያሳድሩባታል። ‹‹ቤተሰቦቼ ሙሉ ትኩረቴን ለትምህርቴ እንድሰጥና ተመርቄ ጥሩ ሥራ እንዳገኝ ነው የሚፈልጉት። የሞደዴሊንግ ሥራዎችን እንዳልፈልግ ባይከለክሉኝም ንቀት [በዘርፉ ላይ] እና ትንሽ ንዴትም አይቼባቸዋልው። አስተያየታቸው ቢገባኝም ከልጅነቴ መሆን የምመኘው ሙያ ግን መተው አልፈልግም። ሞዴሊንግም ጥሩ ሥራ መሆን እንደሚችል ለማስረዳት ሞክሪያለሁ። የወደፊት ሕይወቴ በፋሽን ሥራ ላይ እንዲሆን ነው የምፈልገው›› ስትል ያለባትን ተግዳሮትና የውስጥ ፍላጎት በንጽጽር ታስረዳለች።

ዓለም ዐቀፉ የፋሽን ኢንዱስትሪ ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚያመነጭ ዘርፍ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ዳዴ በማለት ላይ ነው ማለት ይቻላል። ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ከብዙ አገራት ልምድ ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፋሽን ባለሙያዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው የፋሽን ሥራዎችን በመሥራት ለአገሪቱ የፋሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው። በዓለም ታዋቂነት ያገኘችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አና ጌታነህ ያቋቋመችው ‹የአፍሪካ ሞዛይክ ብራንድ› እንደ ምሳሌ ይጠሳል።

ገነትም የኢትዮጵያ ፋሽን ኢንዱስትሪ ገና ብዙ ሥራ እንደሚያፈልገው ይናገራሉ። ‹‹የኢትዮጵያ ሞድሊንግ ሥራ ገና በጅምር ላይ ነው፤ የሚያስገኘውንም ጥቅም ገና አላይንም። ሥራውን ለማስተዋወቅ በመንግሥት በኩል ምንም ሥራ አልተሠራም። ዝግጅት ስናዘጋጅ [እንኳን] የመንግሥት ሰዎች በዝግጅታችን ላይ አይገኙም›› በማለት ገነት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ዝቅተኛ ግምት ማሳያ አድገው የመከራከሪያ ነጥብ ያነሳሉ።

እስካሁን ለ250 ሰዎች ሞዴሊንግ ሥልጠና የሰጠው የኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ መሥራች ሳራ መሐመድ የዘርፉን ተግዳሮት በተመለከተ ከገነት ጋር ይስማማሉ። ‹‹ትልቁ ተግዳሮት የመንግሥት ለዘርፉ ትኩረት አለመስጠት ነው›› የሚሉት ሳራ ዝቅተኛ ክፍያም ዘርፉን ወደ ኋላ መጎተቱም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሞድሊንግ ሥራ ገና እያደገ ቢሆንም ዘርፉ ባደገባቸው የዓለም ክፍሎች የሚታዩት አሉታዊ ተጽዕኖዎች መታየት ጀምረዋል። ብዙ ሰዎች እንደሚናገሩት በምዕራብ አገሮች የሚገኙ ሞዴሎች ለብዙ ጉዳቶች ይጋለጣሉ። ለምሳሌ የተወሰነ የሰውነት ክብደት ላይ ለመድረስ አለመመገብን እንዲሁም አደገኛ መድኃኒቶችን መጠቀም ይጀምራሉ። ብዙ የተደራጁ ጥናቶች ባይሠሩም ከብዙ ሰዎች የሚገኘው መረጃ ችግሩ የተስፋፋ መሆኑን ያሳያል። ችግሩን ለመከላከል ፈረንሳይ ሞዴሎች ከተወሰን ክብደተ በታች ላለመሆናቸው የሀኪም ማስረጃ እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ አዋጅ አውጃለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህ ደረጃ ላይ ባይደርስም ሥራው ላይ መግባት የሚፈልጉት ሰዎች የተወሰን ጫና እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ፤ ቤተልሔምም ከእነዚህ መካከል ትመደባለች። ‹‹እውነቱን ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ባያውቅሽም ስለ ክብደትሽና አለባበስሽ የመናገር ልምድ አለ። ሞዴሊንግን ሥራ ላይ መግባት ለፈለገ ሰው ደግሞ ተጨማሪ ጫና ያለ ይመስለኛል›› ትላለች ቤቲ በዘርፉ ላይ መሳተፍ ስለሚያደርሰው ተጽዕኖ ስታብራራ።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሞዴሊንግ ኢንዲስትሪ ብዙ ሊያስገኛቸው የሚችሉ ዕምቅ ችሎታ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ። የማኅበራዊ ግንኙነት ድረ ገጾችና የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ሲጨምር የኢትዮጵያን ፋሽንና ባሕል ለማሰስተዋወቅ ተጨማሪ ዕደሎችም እንደሚፈጠሩ ይናገራሉ። ገነት ‹‹ጥሩ ድጋፍ ከተሰጠን ለአገራችን ብዙ ገቢና ዕውቅና ማስገኘት ይችላል። አሁን ግን ገና መጀመሪያው [ምዕራፍ] ላይ ነን›› ይላሉ።
ይህ ጽሑፍ ከ‹ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው›› መጽሔት ለአዲስ ማለዳ በሚመች መልኩ ተተርጉሞ የቀረበ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here