ብቸኛው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ገድል ትውስታ በ3ኛው አፍሪካ ዋንጫ

0
1282

ከአስተዳደራዊ ችግር እስከ ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ስር የሰደደ ችግር የተተበተበውና ደረጃው ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በታሪክ የማይረሳውን ገድል ያስመዘገበው ከዛሬ 57 ዓመታት በፊት ጥር 13/ 1954 ነበር። ሚኪያስ በቀለ ይህንን ፈር ቀዳጅና ለሌሎች ድሎች መነሻ ሊሆን ሲገባው ከታሪክ ትውስታነት ጭምር እየደበዘዘ የሔደውን ይህንን ደማቅ ድል እንደሚከተለው አስታውሰውታል።

የ2ኛው አፍሪካ ዋንጫ በግብፅ ካይሮ ሊደረግ የቀናት ዕደሜ ብቻ ቀርቶታል። የወቅቱ የውድድሩ ተሳታፊ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ለጨዋታው ከመጓዙ በፊት እንደ አሁኑ ጊዜ የተመቸና ደረጃውን የጠበቃ የመጫወቻ ጫማ ወይም ታኬታ አልነበረውም።

ይህንንም ተከትሎ ይላሉ ፈለቀ ደምሴ በ2005 “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዞ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ እንደሚተርኩት ያለውን ጫማ ጠጋግኖ ወደ ውድድሩ ስፍራ ለማምራት የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ፓስታ ቤት አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ጫማ ሰፊ ጋር አምርተዋል። ነገር ግን ጫማ ሰፊው ጠግኖ የሰጣቸውን ጫማ ለመጨረሻ ልምምድ አስመራ ከተማ ላይ ሲጠቀሙበት ምንም ዓይነት ምቾት ሊሰጣቸው አልቻለም ነበር። በመሆኑም በወቅቱ ያለው ብቸኛ አማራጭ አንድ ብቻ ነበር። ጫማው የአግዳሚ እንጨት እንዲመታበት ተደርጎም ስብስቡ ወደ ግብፅ ተጓዘ። ይሁንና የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ወደ ግብፅ ካመሩ በኋላም ገና የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ሲያደርጉ የመጫወቻ ታኬታቸው በድጋሚ እያንሸራተተ አስቸገረ።

ተጫዋቾቹም በአገር ውስጥ ያጡትን መፍትሔ በሰው አገር ለማግኘት በመመኘት ጫማዎቻቸውን ይዘው ወደ አንድ ግብፃዊ ጫማ ሰፊ ዘንድ አመሩ። የውድድሩ ቀን ደርሶም ለጫማ ሰፊ ተሰጥቶ የነበረውን ጫማቸውን ተጫምተው ባለሜዳዋን ግብፅ ለመግጠም ወደ ሜዳ ገቡ። በሜዳ ላይ ያጋጠማቸው ግን ያልጠበቁት ነበር።
በጥሩ ሁኔታ እንደተጠገነላቸው እምነት የጣሉበት ጫማ በጨዋታው ላይ እየተነቃቀለና እየወለቀ ለሽንፈት አጋለጣቸው። ከጨዋታው በኋላም በግብፁ ጫማ ሰፊ ሴራ ጫማቸው በአግባቡ ሳይጠገን እጃቸው ላይ መግባቱ እያንገበገባቸው ሜዳውን ለቀቁ። በሰው አገር የደረሰባቸውን በደል እያሰላሰሉም በቁጭት ስሜት ውስጥ ሆነው ወደ አገራቸው ለመመለስ ተገደዱ።

የብርቅዬው ድል ሰሞን
በሦስተኛው የአፍሪካ ዋናጫ ላይ ለመሳተፍ በተደረገው የማጣሪያ ጨዋታም 12 ቡድኖች ተፋልመው ኢትዮጵያ፣ ቱኒዚያ፣ ግብፅ (በያኔው አጠራሯ የአረብ ሪፐብሊክ) እና ኡጋንዳ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ለውድድሩ አልፈው በመድረኩ ቀረቡ።

ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ታሪኳ ብርቅ የሆነውን ብቸኛ ዋንጫ ያገኘችበትና የአንድ ሳምንት ዕድሜ የነበረው ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጥር 06/1954 በአዲስ አበባ ስታዲየም (በቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታሲየም) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በቱኒዚያ አቻው መካከል በተደረገ ጨዋታ አሀዱ ተብሎ ተጀመረ።
በውድድሩ ላይም አራቱ ቡድኖች ሁለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችን እንዲሁም ለፍፃሜና ለሦስተኛ ደረጃነት ሌሎች ሁለት ጨዋታዎችን አደረጉ። በውድድሩ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታም አዘጋጇ ኢትዮጵያ ቱኒዚያን ስታስተናግድ የሁለተኛው አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የነበረችው ግብፅ ከኡጋንዳ እንድትጫወት ተደረገ።

በወቅቱ ኢትዮጵያ ቱኒዚያን፥ ግብፅ በበኩሏ ኡጋንዳን በመርታት ለፍፃሜው መብቃትም ቻሉ። ኢትዮጵያና ግብፅ ለፍፃሜ መብቃታቸው ሲታወቅም የሁለቱ ቡድኖች የቀደመ የእርስ በርስ ግንኙነትና መሰል ሁኔታዎች በጨዋታው ዙሪያ ያለውን ውጥረት እጅግ የጨመረ ነበር።

ቁጭት የተሞላበት ፍፃሜ
ግብፅ ከአምስት ዓመታት በፊት በ1949 የተደረገውን የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ የወሰደችው ኢትዮጵያን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በካይሮ የደረሰባቸው የመጫወቻ ጫማ ሴራ ቁጭት ከሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ባላንጣነት ጋር ተደምሮ ፍፃሜውን በሜዳቸው የሚያደርጉትን ስሜት እጅግ ያናረ ነበር።

የአዲስ አበባ ስታዲየምም በ 25,000 ደጋፊዎች ተሞልቶ በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ የምንጊዜውም ልብ ሰቃይና አዝናኙ ጨዋታ የተሰኘው ግጥሚያ ተጀመረ። ጨዋታውም እየጋለ እየጋለ ሄዶ በ35ኛው ደቂቃ ግብፅ አብዱልፈታ በደዊ አማካኝነት ስታዲየሙን በድንጋጤ ፀጥ ረጭ ያደረገች ግብ አስቆጠረች።
የፈርኦኖቹ መሪነት ግን መዝለቅ የቻለውም እስከ 74ኛው ደቂቃ ነበር። በጨዋታው ላይ የቡድኑን አጥቂ ግርማ ዘለቀን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ተክሌ ኪዳኔ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን ዳግም ወደ ውጥረት መለሰው፤ ነገርግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቻነት ቆይታ ሽርፍራፊ ሰከንዶችን መሻገር አልቻለም።
የግብፁ የግብ አዳኝ በደዊ አገሩን ወደ 2 ለ 1 መሪነት የቀየረችውን ሁለተኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳረፈ። የትኛውም የአፍሪካ አገር አንድ ዋንጫ ባላሳከበት ሁኔታም ግብፅ የውድድሩን ሦስተኛ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ መቃረቧ ተገመተ።

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥም ግን ተስፋ ያልቆረጡት የይድነቃቸው ተሰማ ልጆች ወደፊት መግፋታቸውን ቀጠሉ። ከደቂቃዎች በኋላም ሉቺያኖ ቫሳሎ ከወቅቱ የኮተን ተጫዋች ጌታቸው ወልዴ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ጨዋታውን ወደ 2 ለ 2 አቻነት ቀየረ። ከጎሉ አስቆጣሪ ተጫዋች ማንነት ጋር በተያያዘ በወቅቱ የተፈጠረው የታሪክ ብዥታ ግን አሁንም አለ።

የታሪክ መፋለሱ መነሻም ወሳኟን የአቻነት ግብ ከሉቺያኖ ይልቅ የቡድን አጋሩ መንግሥቱ ወርቁ እንዳስቆጠረ በአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ካፍ ህትመቶች ጭምር መፃፉ ነበር። በሌላ በኩል ግን ሉቻኖ ቫሳሎ የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ያስቻለችውን ኳስ ከጌታቸው ወልዴ ሲቀበል የሚሳይ የምስል ማስረጃ ኢትዮጲያዊው ፎቶ አንሺ በዛብህ አብተው በካሜራቸው አስቀርተዋል።

የፍፃሜው ጨዋታም በዚህ መልክ ቀጥሎ መደበኛው የጨዋታ ሰዓት 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ተፈፀመ። በወቅቱም ከጨዋታው ጋር በተያያዘ በመላው አዲስ አበባ የነበረው ውጥረት እስካሁንም ተደጋግሞ ሲነሳ ይደመጣል። ጨዋታው በዚህ መልክ በቀጠለበት ሁኔታ ላይም የጨዋታውን ውጥረት መቋቋም ያልቻሉት ግብፆች በ 101ኛው ደቂቃ የፈፀሙትን የመከላከል ስህተት ተጠቅሞ ኢታሎ ቫሳሎ ለራሱ ሁለተኛውን ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ ኢትዮጵያ የ 3 ለ 2 መሪነት ተቀየረ።

በጨዋታው 117ኛ ደቂቃ ላይም የኢትዮጵያን የማሸነፍ ዕድል ያሰፋች በሌላኛው ፅንፍ የእንግዳዎቹን ፈርኦኖች ልብ የሰበረች ግብ ተቆጠረች። የቡድኑ ቁልፍ ሰው መንግሥቱ ወርቁ ያገኛትን ኳስ በግሩም ሁኔታ እየገፋ ሔዶ አራት የግብፅ ተከላካዮችን በቄንጥ በማለፍ ጨዋታውን ወደ 4 ለ 2 የቀየረች ግብ ከመረብ ላይ አሳረፈ።
ከአራተኛው ጎል መቆጠር ደቂቃዎች በኋላም የዋንጫውን አሸናፊ ያበሰረው የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ተሰማ።

ድህረ ፍፃሜ
የጨዋታው መጠናቀቂያ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ሲያበስር አዲስ አበባ ስታዲየም ከጭንቀት ተላቆ በሆይታና ሁካታ ተሞላ። የድሉም ብስራት ያኔ ብርቅ በነበረው ብቸኛው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሞገድ በመላው አገሪቱ ከጫፍ እሰከ ጫፍ ናኘ። የደስታ አገላለፅ መንገዱም ከአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊነት ይልቅ የዓለም ዋንጫ አሸናፊነትን መንፈስ ያዘለ ብርቱ ፌሽታ ነበረ።

በስታዲየሙ ሁሌም ከጎናቸው ከማትለየው የቤት ውሻቸው ጋር በስታዲየሙ ተገኝተው ጨዋታውን የተከታተሉት የወቅቱ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በደስታ መንፈስ ተውጠው የአሸናፊነት ዋንጫውን ሉቺያኖ ቫሳሎ አበረከቱ።

ብሔራዊ ቡድኑ ድሉን ካሳካበት የፍፃሜ ጨዋታ በኋላም ስብስቡ ስታዲየሙን በመልቀቅ ለውድድሩ ዝግጅት ወደ ከተመበት የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል በሚያመራበት ወቅት የቡድኑን አባላት የያዘው አውቶብስ በደስታ በሰከሩ ደጋፊዎች ተከቦ ብዙ ሰዓትን መንገድ ላይ ለማሳለፍ ተገዶ ነበር።

በወቅቱም ድል ላደረገው ስብስብ በጣም ትልቅ የሚባለው የ500 ብር ሽልማት ለእያንዳንዱ የቡድኑ አባል ተበርክቷል። በሽልማቱም የቡድኑ አባላት በጊዜው ውድ የተባለውን የጣሊያን ጫማ በ20 እና 30 ብር ሲሸምቱ እያንዳንዳቸው እስከ 120 ብር ወጪ በማድረግም ሙሉ ልብስ እንደገዙ ይነገራል።

እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መሪ የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ ግብፆች በሰሩት ደባ ስብስባቸው ተገቢ ባልሆነ መልኩ ተረቶ ከሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውጪ ሲሆን ለተጫዋቾቻቸው በአንድ ዓረፍተ ነገር የገቡት ትልቅ ቃል ኪዳን ተደጋግሞ ይነሳል።

በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያን ከወከሉ ተጫዋቾች አንዱ የሆኑት አቶ አዋድ መሀመድ ታሪኩን አስታውሰው በአንድ ወቅት እንደተናገሩት ከሆነ “አይዟችሁ፤ 3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚዘጋጀው እኛ ጋር በመሆኑ በተንኮል ሳይሆን በጨዋታ አሸንፈን ብድር እንመልሳለን” ነበር የክቡር ይደነቃቸው ተሰማ ቃል። ‘የጂብራልተሩ አለት’ ያሉትም አልቀረ የሚመሩት ስብስብ ከአስቆጪው ሽንፈት ሦስት ዓመታት በኋላ በሜዳው እና በንጉሱ ፊት የአህጉሩን ትልቁን ዋንጫ ከፍ አድርጎ አነሳ፡፡

የወቅቱ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጥ 11 (በ 4-2-4 የጨዋታ ቅርፅ)
ግብ ጠባቂ : ጊላ ሚካኤል ተክለ ማርያም (አዶሊስ፣ አስመራ)
ተከላካዮች : አስመላሽ በርሄ (ከኢትዮ-ሴመንት፣ ድሬድዋ)፣ አወድ መሀመድ (ከኦሜድላ፣ አዲስ አበባ)፣ በርሄ ጎይቶም (ከቴሌ፣ አስመራ) እና ክፍሎም አራያ (ከቴሌ፣ አስመራ)
አማካዮች : ተስፋዬ ገ/መድህን (ከቴሌ፣ አስመራ) እና ሉቺያኖ ቫሳሎ (ከኮተን፣ ድሬድዋ)
አጥቂዎች : ግርማ ዘለቀ (ከኮተን፣ ድሬድዋ)፣ መንግስቱ ወርቁ (ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አዲስ አበባ)፣ ኢታሎ ቫሳሎ (ከኮተን፣ ድሬድዋ) እና ጌታቸው ወልዴ (ከኮተን፣ ድሬድዋ)
የቡድን መሪ : ይድነቃቸው ተሰማ
አሰልጣኞች : ሚሎሶቪች (ከዩጎዝላቪያ)፣ አዳሙ አለሙ እና ፀሐዬ ባህር

ሚኪያስ በቀለ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ስፖርታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ ይታወቃሉ። በኢሜል አድራሻቸው hammermanunited@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here