ኃይለገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) “ባሕልና ትምህርት በኢትዮጵያ” የሚል ጥናት በ2007 አሳትመዋል። ይህንን የኢትዮጵያን ባሕላዊ የትምህርት ስርዓቶች የሚያስቃኝ መጽሐፍ ያነበቡት ብርሃኑ ሰሙ፥ ጠቅላላ ይዘቱ ምን እንደሚመስል በአንድ ገጽ እነሆ ቅምሻ ይሉናል።
የቀድሞ ተማሪዎች ‘ምርቃት’
“ዳዊት ጨርሼ የተመረቅሁ ጊዜ ዘጠኝ ዓመት ይሞላኝ ይሆናል። እናቴ ሱሪ… አሰፍታ አሰናድታልኛለች። የምርቃቱ ዕለት አለበሰችኝ። እምባም ብዙ አፈሰሰች… ጥምጥም ታሰረልኝ። መቋሚያ ያዝኩና… በተማሪዎች ታጅቤ ወደ ቤተክርስቲያን ሔድኩ። የኔታ ዐምደ ወርቅ ፊት ለፊት አቆሙኝ። ከቅዳሴ በኋላ ቄሱ ከሰዎች ሁሉ በፊት በመስቀል ባረኩኝ። ከዚያ በኋላ የየኔታን ጉልበት ሳም አሉኝ፤ ሳምኩ። የኔታም የሽማግሌዎቹን ጉልበት ሳም አሉኝ። ሁሉም በየተራ መረቁኝ።” (ከፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ግለ ታሪክ የተወሰደ)
“ቁራን ያጠናቀቀ ተማሪ በፈረስ ወይም በበቅሎ ላይ ተቀመምጦ በተማሪዎችና ወገኖቹ ታጅቦ ወደ አስተማሪው ይሔዳል፤ ይዘፈንለታልም። ሥጦታም ይሰጠዋል። አቅም ያላቸው በግ ያርዳሉ።… 15ኛውን ጁዝ ለአጠናቀቀ ልጅ፣ ጓደኞቹን ጨምሮ መለስተኛ ግብዣ በወላጆቹ ቤት ይደረግለታል። ሙሉውን ቁራን ሲጨርስ ግን፣ በሉኽ (የእንጨት ሠሌዳ) ላይ የቁራን ጥቅስ ጽፎ፣ በጓደኞቹ ታጅቦ ከአንድ ዘመድ ቤት ወደ ሌላው ይሄዳል። ዕውቀቱን ያስተዋውቃል። ሥጦታም ያገኛል።” (ከጂግጂጋና ሐረር አካባቢ በመስክ ጥናት የተገኘ መረጃ)
ከላይ የቀረቡትን ሁለት ታሪኮች የያዘው የኃይለገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) መጽሐፍ “ባሕልና ትምህርት በኢትዮጵያ (Studies on Education in Ethiopia)” በሚል ርዕስ በሁለት ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን፥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ በ2007 የታተመ ነው።
የአገራችን ባሕላዊና ዘመናዊ የትምህርት ታሪክ አጀማመር፣ ዕድገቱ፣ ችግርና ተስፋዎቹ ምን እንደሚመስል በጥናትና ምርምር ላይ ተመሥርቶ ሰፊ መረጃዎችን በ375 ገጾች ያቀረበው የኃይለገብርኤል መጽሐፍ፥ ዓለማቀፋዊ ነው የሚባል ባሕል እንደሌለና ባሕል ከቦታ ቦታ፣ ከኅብረተሰብ ኅብረተሰብ እንደሚለያይ፣ ከአንድ ዘመን ወደ ሌላኛው በተግባርና በትምህርት እንደሚተላለፍ፣ ባልተጻፈ ሕግ እንደሚመራ፣ ልማድ ሲደጋገም ባሕል እንደሚሆን፣ ባሕል ዓይነቱ፣ ይዘቱ፣ መገለጫው፣ መተላለፊያ መንገዱ እንደሚለያይ፥ ባሕል ጠቃሚ ጎኑ ሳስቶ ጎጂ ገጽታው እየሰፋ ሲሔድ “ለለውጥና ዕድገት” መፈጠር ምክንያትና መነሻ እንደሚሆን …ባሕላዊ ዕውቀት ከቤተሰብ፣ ከኅብረተሰብ፣ ከቤተ ክርስቲያንና ቤተ መስጊድ እንደሚቀሰም፣ ዘመናዊ ትምህርት በተለያዩ ደረጃዎች በተዋቀሩ የትምህርት መስጫ ማዕከሎች እንደሚሰጥ በማብራራት ነው የሚጀምረው።
ዕውቀት እና ትምህርት
“ትምህርት የሚባለው ቃል በባሕላችን ከቀለም ሌላ አያመለክትም። እርሻ ማረስን፣ ብረት መቀጥቀጥን፣ ከብት ማርባት ዓይነት ተግባረ ጥበብን ‘ተማረ’ ማለት አልተለመደም። …አንድ ልጅ ማረስን ወይ መቀጥቀጥ ይለምዳል፤ ከለመደም በኋላ ‹ዐወቀ› ይባላል” የሚሉት ኃይለገብርኤል ዳኜ ባሕላዊ ትምህርት በሚሰጥባቸው ቤተ ክህነትና ቤተ መስጊድ የማስተማሩ ሒደት ምን እንደሚመስል፣ አንዱ ከሌላኛው ጋር በምን እንደሚቀራረብናና እንደሚለያይ በርካታ ማሳያዎችን በንፅፅር አቅርበዋል።
ብዙ ደረጃዎች ካሉት ባሕላዊው የቤተ ክሕነት ማስተማሪያ ተቋሞች መሐል “የንባብ ትምህርት ቤት” አንዱ ነው። ከዚህ ትምህርት ቤት የሚመረቅ ተማሪ ጽሕፈት የማይማርበት ምክንያት የአስማት ሥራ እንዳይሠራበትና ተማሪው የቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉትን መጻሕፍት ማንበብ እንዲችል ማዘጋጀት ነው የሚሉት ኃይለገብርኤል “በሙስሊም ትምህርት ቤቶች ከክርስቲያኑ በተለየ ሁኔታ ተማሪው ጽሕፈት ትምህርት እንዲለማመድ ቢበረታታም ተማሪዎች ቁራንን በቃል እንዲያጠኑ ስለሚደረግና ትምህርቱንም በአረቢኛ ስለሚማሩት ትርጉሙ የማይገባቸው ጊዜ አለ።”
ባሕላዊው ትምህርት ቤቶች አንዱ በግዕዝ ሌላው በአረቢኛ ቋንቋዎች ማስተማራቸው ያስገኘውን ጥቅምና ጉዳት፣ ግዕዝን ማሳያ አድርጎ የሚከተለው መረጃ ቀርቧል። “የግዕዝ መምህራን የሚማሩትም በቃል፣ የሚያስተምሩትም በቃል፣ ዕውቀቱንም የሚይዙት በቃል፣ ሊቅነታቸውም በቃል ስለነበር ችሎታቸውና ዕውቀታቸውን በዝና ከማድነቅ ባሻገር የጽሑፍ ቅርስ እምብዛም አልተገኘም። ዋናው ምክንያት ከጥንት ጀምሮ፣ ጽሕፈት ወደጥንቆላና አስማተኝነት ያመራል ተብሎ ስለታመነ መምህራን መጻፍ ከቻሉ፣ ይጠነቁሉ ይሆናል ተብሎ ስለተፈራ ጽሕፈት ከትምህርት ቤት እንዲወገድ ተደረገ። ተማሪዎች ጽሕፈት አለመቻላቸውን መምህራን አረጋግጠው ይቀበላሉ፣ አንዳንዴም እንዳይጽፉ ያስምሉአቸው ነበር።”
ይህ ክልከላ ከዓመታት በኋላ የብራና ጽሑፎች ውድ እንዲሆኑ አስተዋፅዖ አድርጓል። በአሁኑ ዘመን “የቁም ጸሐፊ” ዕውቀት ያለው ባለሙያ እንደብርቅ የሚታየውና የቀድሞ ዘመን ብቻ ሳይሆን ዛሬም በብራና ላይ የሚጻፉ ጽሑፎች በቅርስነት እንዲመዘገቡ ዕውቅና የተሰጣቸው በዚህ ምክንያት ነው። በቀድሞ ዘመንም በብዙ ውጣ ውረድ ‘የቁም ጸሐፊ’ መሆን የቻለ ባለሙያ ተፈላጊነቱ ሰፊ ነበር የሚሉት ኃይለገብርኤል የራሱን የጽሕፈት መሣሪያዎች አዘጋጅቶ አንድ መጽሐፍ መገልበጥ ደረጃ ላይ የደረሰ፣ ሥራው እንደመመረቂያ ጽሑፍ ታይቶለት፣ ያንን በመረጃነት ይዞ ወደሚፈልገው አድባራትና ገዳማት ሔዶ የማገለግል ወይም የመኳንንትና ነገሥታት ዜና መዋዕል ጸሐፊ የመሆን ዕድል ነበረው ይላሉ።
“የትርጓሜ ትምህርት ቤት” ፋይዳም ተመሳሳይ ነው የሚሉት ኃይለገብርኤል፥ ይህም ባሕላዊ ትምህርት ቤት “ዓለምን ለመረዳት፣ ስለ ዓለም ምድራዊ ሁናቴ ዕውቀት እምብዛም አላመጣም። ከጥንታዊ ግሪክና ሮማዊያን ፈላስፎች እምብዛም ወደ ግዕዝ የተተረጎመ የለም። የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የሚያተኩረው እንደነእስጢፋኖስ ያሉ የሰማዕታት ገድላት ላይ ነው፡”
በዚህ ችግር ውስጥ አማርኛ ቋንቋ የማደግና በተሻለ ሁኔታ የጽሑፍ መገልገያ ሊሆን የቻለበትን ዕድል እንዴት ሊያገኝ እንደቻለ በ“ባህልና ትምህርት በኢትዮጵያ (Studies on Education in Ethiopia)” መጽሐፍ በቀረበው መረጃ “በቅኔ ቤት” እና “በመጽሐፍ ቤት” ዋናው ቋንቋ ግዕዝ ሆኖ አማርኛ በሁሉም ደብር የመማሪያ ቋንቋ የነበረ መሆኑን አመልክቶ፣ “በግዕዝ የተጻፈውን ወደ አማርኛ በቃል እየተረጎሙ ማስተማርና መማር የተለመደ ነበር። ዛሬ አማርኛ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቃላት ቢያጥረውም፣ ከሌሎች የሥነ ጽሑፍ ቋንቋዎች ጋር ሊወዳደር የቻለው ብዙ ዘመናት በነዚህ ትምህርት ቤቶች” በማስተማሪያነት በማገልገሉ ነበር።
ለአማርኛ ቋንቋ ዕድገት መነሻና መሠረት የሆነው ግዕዝ፥ በጥንት ታሪኩ የራሱ ፊደል ያለውና ለጽሑፍም በማገልገሉ ታዋቂ ነበር የሚሉት ኃይለገብርኤል፥ “ሰሜን ኢትዮጵያ ከሳባዊያን ጋር በነበረው ግንኙነት የተነሳ ከ2500 ዓመታት በፊት ጀምሮ የጽሕፈት ሙያ እየተለመደ መጥቷል። በቁጥር የተወሰኑ ቢሆንም የጽሕፈትና የንባብ አዋቂዎች በሰሜን ኢትዮጵያ እንደነበሩ፣ ከሳባዊያን ፊደል በኋላም በግሪክና በግዕዝ ቋንቋ የተቀረፁ ድንጋይ ሐውልቶች ይመሰክራሉ። ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ፣ ሠ፣ ረ፣ ሰ፣ በ፣ ተ፣ የሚል ፊደል መሰል የተቀረፀበት ድንጋይ በትግራይ ውስጥ ተገኝቷል። ይህ ፊደል ከሆነ፣ በዚህ የሚማሩ ተማሪዎች ነበሩ ማለት ነው። ተማሪዎች ከነበሩ፣ መጠኑ አይታወቅ እንጂ አስተማሪዎችም እንደነበሩ ፍንጭ ይሰጣል።”
የግዕዝ ትምህርትና ሥነ ጽሑፍ በማደግ ላይ ሳለ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና ብራናዎች “በግራኝ ወረራ” ዘመን ወደሙ። በጦርነቱ የወደሙትን የብራና ጽሑፎች ለማባዛት ዐፄ ምኒልክ በቤተ መንግሥት የቁም ጽሕፈት ቤት በማቋቋም የተባዛውን ጽሑፍ ለየአድባራቱ በመላክ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርገዋል። በአብነት ትምህርት ቤቶች በየደረጃው የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቀው ከመምህራኖቻቸው ከመሰናበታቸው በፊት ሥራ ፍለጋ ለሚሔዱበት አካባቢ የሚያደርሱት አንድ ድርሳን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸው ነበር። የብራና መጻሕፍትን ማባዣ አንዱ መንገድ ይህ ነበር።
በቤተ ክርስቲያናትና ቤተ መስጊዶች የሚሰጠው ባሕላዊ ትምህርት አሁንም የቀጠለ ቢሆንም ዘመናዊውን የትምህርት አሰጣጥ መወዳደር የሚችሉ ግን አይመስልም የሚሉት ኃይለገብርኤል፥ “በአሁኑ ወቅት የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ከከተሞች አልፎ ወደ ገጠር በፍጥነት እየገሰገሰ ስለሆነ ከባሕላዊው ይልቅ ዘመናዊ ትምህርትን ይበልጥ ተፈላጊ አድርጎታል። ወላጆችም ልጆቻቸው ለኑሮ ውድድር እንዲበቁ ወደነዚሁ ትምህርት ቤቶች መላኩን ይመርጣሉ። የዓለም ዐቀፉ የሚሌኒየሙ የትምህርት ግብም (ሁሉም ልጅ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ያግኝ የሚለው መርሐ ግብር) የዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር አሳድጎታል። በዚህ ምክንያት በከተሞች ትውፊታዊ ትምህርት ቤቶችን መዋዕለ ሕፃናት እየተኳቸው ነው።
ዘመናዊው የትምህርት ስርዓት በዚህ ደረጃ ተፈላጊ ሆኖ ገዢ ከመሆኑ በፊት በራስ ማንነት፣ በአገራዊ ዕውቀት፣ በባሕላዊ መሠረት ላይ የተገነባ የትምህርት መሠረት ተጥሎ፥ “ዕድገቱ” ያንን መነሻ እንዲያደርግ ጥረት ያደረጉለት ነበሩ። ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በፊት፣ ዘመናዊ ትምህርት የማስፋፋት አካል ሆኖ፣ መምህራን ማሠልጠኛ ሲቋቋም ለአሠልጣኝነት ከውጭ አገር ከመጡት መምህራን አንዱ ‘ኤርነስት ዎርክ’ ነበሩ። “በ1921 ‘ኤርነስት ዎርክ’ በተባለ አፍሮ አፍሪካዊ አመራር በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተጠናክሮ መምህራንን ማሠልጠኑ ተጀምሮ፣ በ1922፣ 12 መምህራንን አስመረቀ። ‘የኤርነስት ዎርክ’ ዓላማው ኢትዮጵያ ከውጭ ጥገኛ ሳትሆን የራስዋን ትምህርት ስርዓት እንድትዘረጋ ለማስቻል ነበር። ስለሆነም ስርዓቱም እንግሊዛዊ ወይም ፈረንሳዊ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ምኞቱን ገልጾ ነበር።”
ፋሽስት ጣሊያን ከተባረረ በኋላ “ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች” በስፋትና በፍጥነት ነበር እያደጉ የመጡት። ቀደም ብሎ ቋንቋ በመቀላቀል፣ አንዱን ክኅሎት አሳውቆ ሌላውን በመከልከል ላይ ተመሥርተው ያስተምሩ የነበሩት ባሕላዊ ትምህርት ቤቶች የማይቋቋሙት ባለጋራ ተፈጠረባቸው። ባሕላዊ ትምህርት ቤቶች “መንፈሳዊ ዕውቀት የእግዚአብሔር ፀጋ ስለሆነ አይሸጥም” ሲሉ “ዘመናዊ” ትምህርት ቤቶች በበኩላቸው “ያልተማረ የሚሸጠው ጉልበት እንጂ ዕውቀት አይኖረውም” በሚለው አቋማቸው ፀኑ። አሸናፊው ማን እንደሆነ ለማወቅ ጊዜ አልወሰደም።
ጣሊያን ከተባረረ በኋላ በአዲስ አበባና በየክፍለ አገሩ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ለማቋቋምና ተማሪዎችን ሰብስቦ ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት ተደረገ። ለዚህ አስተዋፅዖ ያደረጉ በርካታ ኢትዮጵያዊያንንና የውጭ አገር ዜጎችን በስፋት የሚያስተዋውቀው የኃይለገብርኤል መጽሐፍ፥ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር የምሥረታ ታሪክ ምን እንደሚመስል፣ የአባላቱ የፖለቲካ ተሳትፎና ውጤት፣ ማኅበሩ ለአገርና ሕዝብ ዕድገትና ልማት ያበረከተው አስተዋፅዖ፣ በተለያየ ዘመን ማኅበሩን እነማን እንደመሩ እና የማኅበሩ ዓለማቀፍ ግኑኙነት ምን እንደሚመስል ሰፊ ታሪክ የያዘ ጥራዝ ነው። “ባሕልና ትምህርት በኢትዮጵያ (Studies on Education in Ethiopia)” መጽሐፍ ደራሲ ኃይለገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር)፥ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርን ከመሩት አንዱ የነበሩ መሆናቸው መጽሐፉ በበርካታ መረጃዎች እንዲታጨቅ አስችሏል።
ቅጽ 1 ቁጥር 11 ጥር 18 ቀን 2011