በ2013 በጀት ዓመት የሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ሥራዎችን ሀገራዊ መልክ ለማስያዝና ውጤታማ ለመድረግ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች መሰጠታቸው፣ የማሠልጠኛ ሞጁሎች መዘጋጀታቸውና የአሰራር ሥርዓት ጥናቶች መካሄዳቸውን የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
በኮሚሽኑ የሥልጠና፣ ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ በበጀት ዓመቱ ከክልል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች፣ ከፌደራል መንግስት ተቋማት፣ ከአዲስ አበበና ድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ባለሙያዎችና የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች በድምሩ 10 ሺህ 846 ለሚሆኑ ሰዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን አብራርተዋል፡፡
የተሰጡ ሥልጠናዎችም በስትራቴጂክ ዕቅድ፣ በዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ትግል ተሞክሮ፣ በሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች ተግባርና ኃላፊነት፣ በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ጉዳዮች፣ በአሰራር ሥርዓት ጥናትና በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራዎች፣ በሥነምግባርና ሞራል እሴቶች ግንባታና ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአሰራር ሥርዓት ጥናት ላይ ሥልጠና መስጠት የሚያስችል ሰነድ፣ የአስቸካይ ሙስና መከላከል ዓላማዎችና መርሆዎች፣ የሥነምግባርና ሞራል እሴቶች መርሆዎች፣ የ1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ሥነምግባር ክበባት አስተባባሪዎች ማሰልጣኛ ማኑዋል እንዲሁም የአሽከርካሪዎች ሥነምግባር ማሰልጠኛ ሰነዶች መዘጋጀታቸውንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የምርመራና ዐቃቤ ህግ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ማቴሪያል፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሲቪል ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙስና መከላከል ዙሪያ ስለሚኖራቸው ሚና የሚገልፅ ሰነድ፣ የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጣኞች፣ የትምህርት ቤት መምህራን እንዲሁም የኃይማኖት ድርጅቶች ሙስናን በመከላከል ረገድ ያላቸውን ሚና የተመለከቱ ሰነዶች ዝግጅት ተጀምረው በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ 8 (ስምንት) የሚሆኑ የአሰራር ሥርዓት ጥናቶች በኮንስትራክሽን ግዥ አፈፃፀም፣ በተሽከርካሪ ግዥና ድልድል አፈፃፀም፣ በንብረት አያያዝ፣ አስተዳደርና አወጋገድ ሥርዓት፣ በግዥ አፈፃፀምና ሽያጭ አፈፃፀም፣ በመኖሪያ ቤቶች ድልድል፣ ጥገና ፣ የግንባታ ግዥና አፈፃፀም እንዲሁም በንብረት አስተዳደር አሰራሮች ላይ መካሄዱን አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም 3ኛው ሀገር አቀፍ የሙስና ቅኝት ጥናት በአግባቡ እንዲካሄድ ኮሚሽኑ ድጋፍና ክትትል መድረጉ ተመላክቷል፡፡
በ2013 በተሰሩ በነዚህ ሥራዎች በተለይ በተሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች በሥነምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል እንቅስቃሴዎች ላይ ትልቅ መነቃቃት መፈጠሩን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ በቀጣይም አቅም የመገንባታትና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መጠቆማቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡



