ኃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ ይባላሉ። በ1973 የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊትን ተቀላቅለው እስከ 1983 ድረስ አገራቸውን በውትድርናው መስክ አገልግለዋል። አብዛኛውን የወጣትነት ዕድሜያቸውን ኤርትራ ውስጥ በውጊያ ያሳለፉት እኚህ የቀድሞ ሠራዊት አባል፣ ከመንግሥት ለውጡ በኋላ በርካታ የመከራ ወቅቶችን አሳልፈዋል። ከቀን ሥራ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ ቆይተው በቅርቡ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው ተቀላቅለዋል። አሁን የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የድጋፍና ልማት ማኅበር ፕሬዝዳንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። ከወታደራዊ ዕውቀታቸው አኳያ ስለወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አጠቃላይ ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያለንበትን አይነት ፈተና ሲገጥማት አሁን የመጀመሪያ አይደለም። ብዙ ተሞክሮና በርካታ የሆነ ልምድ ያካበቱ ዜጎች ያሏት አገር ናት። መሪዎቿ፣ ኃላፊዎቿና የጦር መሪዎቿ፣ እንዲሁም ተዋጊዎቿ ብቁ ናቸው። ከታሪክ ፍሰታችን አኳያ ዛሬ ላይ ስናይ በየጊዜው የሚገጥሟትን ችግሮች ዜጎቿ አንድ ሆነው በኅብረት በመሰለፍ፤ የዘርና የብሔር ፖለቲካን ወደጎን በመተው በጋራ የኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ላይ የማይደራደሩ ሕዝቦች ያሏት ናት። በአንድነት ድንበራቸውንም ሆነ ሉዓላዊነታቸውን ሲያስከብሩ የቆዩ ሕዝቦች እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል።
ዛሬ ትግራይ ላይ የሚታየው፣ የ27 ዓመት አገዛዝን ኢትዮጵያውያን አይተውት በዘር ፖለቲካ ሳቢያ ትልቅ ጠባሳ ጥሎባቸው ያለፈ የፖለቲካ አስተሳሰብ ስለሆነ፣ በዛ አስተሳሰብ ሳቢያ ሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረ የመገዳደልና እርስበርስ የመናቆር ውጤት ነው። በጋራ የምንኖርበትን የጋራ ዕሴት እየጣሉ ለባዕዳን በሯን ከፍታ እንድትሰጥ ያደረጉ ነበሩ። ረጃጅም እጅ ያላቸው የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብተው በርካታ የደም መፋሰሶች የተከሰቱበት ወቅት ነበር። የእርስበርሱ አለመግባባትና ግጭቱ ተባብሶ አንዱ ብቻውን እኔ ያልኩት ብቻ ይደመጥ ሲል የነበረበት ዘመን ነው። በመደማመጥ የማያምን ቁመና ያለው የፖለቲካ አደረጃጀት ነበር በአገራችን ሥልጣን ይዞ የቆየው።
አሁን ያለውን ሁኔታ አንዳንዶች የአማራና የሕወሓት ግጭት አድርገው ይወስዱታል። ሌሎች ደግሞ የኦሮሞና የአማራ ጦርነት ይሉታል። አንዳንዴም የደቡብና የሰሜን ውጊያ ነው ብለው እንዲሁ አስተያየት የሚሰጡ አሉ። ዓላማቸው ሕዝቡን ለመከፋፈል ስለሆነ ጊዜው የተመቻቸው ስለሚመስላቸው ትውልዱን በዘር ተብትበው ስለቀረጹት አሁን እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ገብተናል። በዘር የመቆራቆዙ አባዜ በትህነግ አማካይነት የተከሰተ ነው።
በዘር ተደራጅተው መቆራቆዙን ካስከተሉት ትውልዶች የአሁኑ የተማረው ነገር አለ?
ኢትዮጵያውያኖች በየዘመናቸው ለሥልጣንና መሬትን ለመሳሰሉ አንዳንድ ጥቅማጥቅሞች እርስ በርስ ሲዋጉ ኖረዋል። ይሄኛውን ለየት የሚያደርገው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ግንባር የፈጠሩበት መሆኑ ነው። የተለያዩ አገራት ቀጥታ መጥተው ማሸነፍ ስላልቻሉ አሁን ስልታቸውን ቀይረው በራሳችን ሰዎች መውጋት ጀምረዋል። “የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ” በሚል ዕሳቤ ኢትዮጵያውያን ጎራ ለይተው እንዲገዳደሉ እያደረጉ ነው።
ኢትዮጵያውያንን በጋራ የሚያስተሳስረን ቋንቋ ወይ ዘር አይደለም። አንዱ ለብቻው ነጥሮ እገሌ ነኝ ማለት እስከማይችል ድረስ እርስ በርስ ተዋልዷል። ያልተዛመደ ባይኖርም አሁን ያለውን ልዩነት በመጠቀም ታሪካዊ ጠላቶቻችን እኩይ ተግባር ባላቸው ጥቂት የትህነግ ሰዎች ታግዘው አንድነታችንን ለመበጣጠስ እየሞከሩ ነው። በእነሱ ምክንያት አገር እየታመሰች ትገኛለች። ግጭቱ ከኢትዮጵያውያን ጭንቅላት የመነጨ አይደለም። ሐሳባቸውን እነዚህ ላይ ጭነው ሽምጥ እየጋለቧቸው ይገኛሉ። ለማይረባና ለሚጠፋ ነገር እርስ በርስ እያጋደሉን ነው። የሰው ልጅ ውስን እድሜ ስላለው አገርና ታሪክ እንዳይቀጥሉ እያደረጉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ኃያል አገር እንዳትሆን የነጮቹ ተልዕኮ አስፈፃሚ በመሆናቸው ዛሬ የምንመለከተውን ደም መፋሰስ እንዲከሰት አድርገዋል።
ሕወሓቶች ኹለት ሐሳብ ያላቸው ናቸው። የተወሰኑት ኢትዮጵያዊነትን ይፈልጉታል። የተቀሩት ደግሞ የተልዕኮው አስፈፃሚ መሆን ይፈልጋሉ። በኹለቱ ሽኩቻ አሸናፊው እስካሁን ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ ቆይቷል። በዚህም ዛሬ የምናየውን የዘር አስተሳሰብ አምጥቷል። ይህን ካመጡ ከአንድ ትውልድ በኋላ ከእጃቸው አምልጦ ወጥቷል። ሥልጣናቸውን ለመመለስም ተመልሰው ደም መፋሰስ ውስጥ ሕዝቡን ከተውታል። የአሁኑ ትውልድ የሆነውን ስለሚያውቅ እንደበፊቱ አይሆንላቸውም። ማንም የበላይ ሆኖ ማንንም የሚገዛባት አገር እንደማትሆን ትውልዱ አውቋል። በፊት ከደርግ የተሻለ ነገር ይዘው ይመጡ ይሆናል የሚል ተስፋ በሕዝቡ ዘንድ ነበር። አሁን ግን እንዲህ አይነት ነገር ጨርሶ የለም። ዓላማቸው ኢትዮጵያን መበታተን መሆኑ ታውቋል። ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሥልጣን ላይ እያሉ ቀብረዋቸው የነበሩ ቦንቦች ልክ ሲባረሩ ጀምሮ እየፈነዱ መምጣታቸው ታይቷል። አሁን የምናየው የሠላም እጦት የሕወሓት ሥራ ውጤት ነው።
አሁን በየቦታው ጦርነት ለምን ሆነ? ማብቂያስ የለውም ወይ ብንል፣ መጀመሪያ መደረግ ያለበት መንግሥት አስተውሎት በመውሰድ አስፈላጊውን የወታደራዊ አዘገጃጀት በእጁ መያዝ የግድ ይለዋል። መከላከያ ተቋምን ማደራጀት ያስፈልጋል። የሚፈራ፣ የሚከበር፣ የሠለጠነና የውጊያ ብቃት ያለው ሊሆን ይገባዋል። በኹለተኛ ደረጃ እነኚያ ሰዎች በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በፈጠራ በሚያናፍሱት ወሬ የሚፈጥሩትን ጫና መቆጣጠር ያስፈልጋል። መንግሥት ከሚወስደው እርምጃ አንፃር መሬት ላይ ያለው ሐቅ እንዲታወቅ መደረግ አለበት።
በመገዳደል የሚያምንና አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀን ድርጅት የጥቃት እንቅስቃሴ፣ ከጀመረ አንስቶ ያለምንም ትንፋሽ እስከመጨረሻው ድረስ በአንድ መስመር ተግባራቸውን ማቋረጥ መቻል አለበት። ጀምሮ ማቆም ሳይሆን ቁመናውን አስተካክሎ እርምጃ መውሰድ መቻል አለበት።
ኹለተኛው የጦርነቱ መቆሚያ የትግራይ ሕዝብ በመሆኑ እንዲህ አይነቱን ነገር ከማንም በላይ የሚያስጨንቀው እሱን ስለሆነ ሠላም ማግኘት አለበት። ቀድሞ የሚጎዳው ራሱ ስለሆነ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቹ ጋር ያለው ግንኙነቱ ክፍተት እየተፈጠረበት ስለሆነ አብሮ እኩይ ተግባር ያላቸውን ከሕዝብና መንግሥት ጎን ቆሞ ሊፋለማቸው ይገባል። ተዉ ብሎ ከተግባራቸው ሊያስቆማቸው ይገባል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር ድንበሩና አንድነቱ ሲነካ እንዴት እንደሚነሳ ይታወቃል። ዛሬ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ላይ እምቢ ላገሬ ብለው የተነሱት አንድ ብሔር ስለተነካ ሳይሆን ኢትዮጵያ ስለተነካች ነው። የትግራይንም ሕዝብ የሚነካው ቢመጣ ሆ ብሎ ሕዝብ መነሳቱ አይቀርም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በማንኛውም ረገድ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመሆን እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል። እስካሁን የሚታየው ጥሩ ሲሆን በዚሁ መልክ መቀጠል አለበት። በሕዝብ በኩል የተፈጠረው የሚደነቅ ቢሆንም፣ በትህነግ በኩል የተሰለፉ ግን ኢትዮጵያዊ እንደመሆናቸው ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል። የሠላሙ በር ሳይከረቸም ሊጠቀሙበት ይገባል።
ከአንድ ብሔር የተውጣጣ ቡድን ሌላውን ሳይጨምር ለብቻው ለመዋጋት የደፈረበት ምክንያት ምን ይመስሎታል?
ለኹሉ ነገር መድረሻ፣ መነሻው ነው ምክንያት የሚሆነው። እነዚህ ሰዎች ሲነሱ ሆን ብለው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አቅደው ነው። አገራችን በፈጣሪ ስለምትጠበቅ እስካሁን ሳይሳካላቸው ቀርተዋል። አሁን አማራጭ ሲያጡ ትግራይን ከሌላው ለመነጠል እየሞከሩ ይገኛሉ። በዚህ ሙከራቸው የተቆጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆ ብሎ ተነስቶባቸዋል።
እነሱ ሲነሱ ጀምሮ የነበረውን ጥንስስ ሲጠምቁ ቆይተው አሁን መጨረሻው ደረጃ ላይ እንዳሉ ሁኔታዎች ያሳያሉ። የመገንጠሉ ሐሳብ የጥቂቶች እንጂ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ነው ብሎ ማሰብ አይቻልም። ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የተሰጣቸውን ተልዕኮ ማስፈጸም የሚፈልጉት ሕወሓቶች ሐሳብ እንጂ የብዙኃኑ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያን ከመሰረቱ ግንባር ቀደም ሕዝቦች አንዱ እንደመሆኑ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ነው። የታሪክ አሻራ ያለው ትልቅ ሕዝብ ነው። ይህን ሕዝብ ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ሲሉ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመለየት ሲጥሩ እየተስተዋሉ ነው። ከጠላቶቻችን የተሰጣቸውን ተልዕኮ የሚያስፈጽሙበት ሰዓታቸው ነው።
የአሜሪካ ፖለቲከኞች ከደርግ ጊዜ ጀምረው ይህችን አገር ለማፈራረስ እየሰሩ ነው። አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ያላት አስቸጋሪ አቋም አሁንም አልተቀየረም። ደርግ ወታደራዊ መንግሥት ስለነበረና ድፍረቱም ስለነበረው ከቃኘው በ72 ሰዓታት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ አድርጎ ነበር። ይሄ ግን ከሕዝብ እየተለየ በሚኬድበት ሰዓትና የሠራዊቱ ሁኔታ አደጋ ውስጥ እየወደቀ ሲሄድ የተከሰተ ነው። ነገር ግን ሕዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ እምቢ ለነጻነቴ አሻፈረኝ የሚላት ከሆነ አሜሪካም ብትሆን ኢትዮጵያ ላይ ልታመጣ የምትችለው ነገር የለም። ድሆች ስለሆንን በኢኮኖሚ ልንጎዳ ብንችልም፣ ዋጋ ተከፍሎ አገር መቀጠል አለባት። ድሃም ብንሆን ክብራችንን ጠብቀን መኖር አለብን። አገር የመገንጠል ፍላጎታቸው እንዳይሳካ መከፈል የሚገባው መስዋዕትነት ተከፍሎ አገር መቀጠል አለባት ብዬ አምናለሁ። የትህነጎች ታሪክ በምዕራባውያኑ እገዛ ከደደቢት ቤተ-መንግሥት ከቤተ-መንግሥት ደደቢት ነው። አሁንም መልሰው ከደደቢት ተነስተው የማፈራረስ ዕቅዳቸውን ለማሳካት ይፈልጋሉ። የነአሉላና ዮሐንስ ልጆች ሆነው ኢትዮጵያዊ ባንዳ ሆነዋል። የታላላቅ ኢትዮጵያውያን ልጆች ሆነው የውጭ ጠላቶቻችን ፈረስ ሆነው ማገልገላቸው አሳፋሪ ነው። አንዳንዴ ሳስበው እንዴት ሕዝብ ሁልጊዜ ሲገዛ ይኖራል ብለው ያስባሉ፣ ለሁሉም ነገር ለከት አለው።
ድሮም አሁንም በፕሮፓጋንዳው የበላይ መሆናቸው ይነገራል። ይህን እንዴት ያዩታል?
እነሱ በደርግ ጊዜም የነበራቸው የፕሮፓጋንዳ ዘዴ አለ። ያኔ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚባል ነገር ስላልነበረ የብዙ ሰው መንፈስ የተጠበቀ ነበር። ዛሬ ላይ በየእጃቸን ዓለምን በየሰከንዱ ነው የምናያት። ይህን በመጠቀም ትልቅ የሚባል የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አላቸው። ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘመቻቸው ምላሽ መስጠት ሲችል ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ አይነት ፕሮፓጋነዳን መከላከል የሚችል ጸረ-ፕሮፓጋንዳ ላይ በእጅጉ መስራት አለበት። ይሄ ማለት ግን ውሸት እየፈበረኩ ማውራት ሳይሆን የተባለው ነገር ለምን ዓላማ እንደተባለ ማስረዳት መቻል አለበት። ፕሮፓጋንዳ በአሁን ሰዓት ራሱን የቻለ ሠራዊት ሆኗል። በሬ ወለደ ወሬያቸውን የሚያስተካክል በእጅጉ የታጠቀ ኃይል ያስፈልጋል። እውነቱን ብቻ ሊያስረዳ የሚችል ማለት ነው። አንድ ቦታ ተያዘ ሲባል ያ የተያዘ ቦታ ተመልሶ እንደሚያዝ ማመን የሚችል አእምሮ መፍጠር መቻል አለበት መንግሥት። በውጊያ ደግሞ መሄድም መመለስም እንዳለ መረዳት ያስፈልጋል። ዝም ብለህ ሸምጥጠህ ሄደህ ጥግ ድረስ አትደርስም። ጥይት ነው ሰው ይወድቃል፣ ይቆስላል። በርካታ ነገሮች ይፈጠራሉ። ጦርነት ለማንም ሰው በጎ አይደለም አውዳሚ ነው፤ ገዳይ ነው። ስለዚህ በሰው ኃይልም፣ በኢኮኖሚም ጦርነት ከጉዳት በስተቀር ልማት አያመጣም። በዚህ ሂደት ውስጥ ዛሬ ትይዛለህ ነገ ትለቃለህ። ነገ ይይዛሉ ከነገ ወዲያ ይለቃሉ። እንዲህ አይነት ነገሮች እንዳሉ የማሕበረሰባችን አእምሮ ላይ በደንብ መሥራት ያስፈልጋል። ፕሮፓጋንዳው ትንሽ ያጨናነቀው ይመስላል ሕዝቡን ስታየው። እኛ ግን ወታደሮች ስለሆንን ለምን እንደተባለ ይገባናል ። የሚቀጥለው ሒደትም ምን እንደሚሆን እንጠብቃለን። ለኛ ምንም ችግር የለውም።
ማሕበረሰቡ ግን እጅግ የተጨነቀ የተወዛገቡ ነገሮች አሉበት። መንግሥት ደግሞ እነዚህ ላይ በስፋት መሥራት አለበት። እውነት ነው ፕሮፓጋንዳው ከአቅማችን በላይ ሆኗል። አንዳንድ ጊዜ እኛንም ወታደሮችን የሚፈትነን ነገር እናያለን፣ እንሰማለን። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እኛ በራሳችን መፍትሔ እንሰጣለን። ሀያ ሰላሳ ደቂቃ ግራ ብንጋባም ግን እውነታውን ስለምናውቀው እንመለሳለን። ማሕበረሰቡ ግን በጣም ተጨንቋል፤ እውነት ለመናገር በየቤቱ ብንሄድ ብዙ የሚሰማቸው ነገሮች የማይመቹ ነገሮች አሉ፤ እና ያን ግልጽ የሚያደርግ ጸረ- ፕሮፓጋንዳ በደንብ ያስፈልጋል። ዓለማችንም በዚህ ጉዳይ ነው እየኖረች ያለችው። የኢትዮጵያም መንግሥት በዚህ ጉዳይ ያለበት ክፍተት ላይ መሥራት ያለበት እንደሆነ ይሰማኛል።
የክተት ጥሪው ተገቢ መሆኑንና እንደምትስማሙበት በሰጣችሁት መግለጫ ላይ ተረድተናል። አሁን ለክተቱ መልስ እየሰጡ ያሉ በራሳቸው ትጥቅ የሚሄዱ አሉ። ትጥቅ የሌላችው አሉና ትጥቅን በተመለከተ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
እንግዲህ ወደ ጦር ግንባር ስትሄድ መሰናዶ የሚባል ነገር አለ። ከውጊያ በፊት፣ በውጊያ መሀል እና ከውጊያ በኋላ ናቸው። ከውጊያ በፊት የትጥቅ ዝግጅት የሥልጠና ዝግጅት በደንብ መደረግ አለበት። ይሄ እንዳለ ሆኖ በዚህ ውስጥ የሚካተተው አመራሩ ነው። በብቃት ሠራዊቱን የሚመራ አመራር መዘጋጀት አለበት። ውጊያው መሀል ላይም አስተባብረው ለድል የሚያበቁ ፣ቆረጥ ያሉ የኢትዮጵያ ጀግኖች በመሀል ማሰማራት ያስፈልጋል። ከዛ ውጪ የትጥቁ ሁኔታ ምንም ጥያቄ የለውም።
የተሟላ ጥይት የተሟላ ትጥቅ ካልያዘ አንድ ወታደር በምንም አይነት ከጠላቱ ገጥሞ ድል ሊያደርግ አይችልም። ግልጽ እና ግልጽ ነው። ከዛ ውጪ መሳሪያም መንግሥት ችግር አለበት ብየ አላስብም። በነገራችን ላይ ብዙ ነገር ልንነጋገር እንችላለን ኹላችንንም ጭንቀት የፈጠረብን ነገር ስለሆነ። ነገር ግን መንግሥት በቂ የሆነ የሠራዊት ብዛትና ጥሩ ቁመና ላይ ያለ የሰለጠነ ሠራዊት እንዳለው ይሰማኛል። ምክንያቱም የሚዋጉት ሕጻናቶች ናቸው፤ ሴቶች ናችው ፤ ሽማግሌዎች ናችው። እነዚህን ሰዎች ከፊት አድርገህ እነዚህን እየገደልክ የምትፎክር፣ እንዚህን ሕጻናት እየገደልክ የምታቅራራ ከሆነ መንግሥት ልትሆንም አትችልም በመጀመሪያ ደረጃ። መንግሥት ኃላፊነት አለበት፤ እነዛ እኮ ምንም ኃላፊነት የለባቸውም። ያገኙትን እያሰለፉ ችግር እየፈጠሩ ነው። መንግሥት ግን ሕዝብ አስተዳዳሪ ነው፤ አገር አስተዳዳሪ ነው። ከዚህ አንጻር የሱ ኃላፊነትም ከባድ ስለሚሆን የታጠቀውን ሁሉ እየወረወረ እንደዛ የሚያደርግ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ለዚህ ነው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ያንን ኹሉ መሳሪያ ይዘን እሳት እየተፋ ውኃ ለምነን ሳንተኩስ ሜዳ ላይ የጣልነው፤ ኃላፊነት ስለሚሰማን እኮ ነው። የሕዝብ ልጅ ስለሆንን እኮ ነው እንጂ ብዙ ገንዘብ እያየን፣ ብዙ ኃብታሞች እያየን ባዶ እግራችንን ሸሚዝና አሮጌ ጨርቅ ለምነን ነው የለበስነው። መትረየስ ይዘን እኮ ጥለነው ነው ወደየቤታችን የገባነው። ሕዝባዊ ስትሆን እንደዚህ አይነት ኃላፊነት አለብህ። በግሌ መንግሥት በቂ ቁመና አለው ብዬ ነው የማምነው። ሠራዊቱን ወደፊት ሒድ ብሎ ለማጥቃት ቢያዘው፣ እርግጠኛ ነኝ አሁን እንትንን ያዙ እንትንን ያዙ የሚባለው ነገር የምንሰማው ነገር አይሆንም።
አንድ ግለሰብ ምንም ክፍያ ሳይከፈለው ሕይወቱን መስዋዕት ሊያደርግ ጦር ሜዳ ሄዶ የማረከውን መሳሪያ እንዲያስረክብ የሚገደድ ከሆነ ሥነ-ልቦና ላይ ምን ይፈጥራል? በደርግ ዘመነ መንግሥትም ጦርነት ላይ የሚሳተፉ መስዋዕት ቢሆኑ ለልጆቻቸው የሚደረጉ ነገሮቸ ነበሩ፤ አሁንስ እንደዚህ አይነት ነገር ቢደረግ መልካም አይደለም?
ለኹሉም ነገር ወቅት ወሳኝ ነው። ለምሳሌ በ1969 ሕዝባዊ ጦራችን ወደ ምስራቅ ጦርነት ሲገባ የአንድ ሚሊሺያ ደሞዝ 20 ብር ነበር። ሆኖም 20 ብር ለሕይወት የሚበቃ ዋጋ ነው ወይ ብሎ ይሄንን መገመት ይቻላል። ኢትዮጵያኖች ለአገራቸው የሚከፍሉት ዋጋ ነው። በነገራችን ላይ አገር በነጻ ነው ያገኘነው። አገርንም በነጻ ነው መስዋዕት ሆኖ ማገልገል የሚቻለው። ኢትዮጵያን በነጻ ነው ያገኘናት በነጻ ነው የምንሞትላት። ሞተው ያቆዩልንም በነጻ ነው። አባቶቻችን አድዋ ላይ ሲዋጉ እኮ ቀይ መስቀል ነው ያነሳቸው። የራሳችው መዋቅር እንኳን አልነበራቸውም። ስንቅ ከቤታቸው ይዘው ሔደው ነው እኮ አገር ነጻ ያወጡት። አሁንም ላይ መሳሪያ የመስጠትና የመመለስ ጉዳይ ሳይሆን ኢትዮጵያን ከችግር ታድገን የምንፈልገውን እንጠይቃለን። አሁን ለምሳሌ የቀድሞ ሠራዊት ጡረታ የለውም፤ ህክምና አልተደረገለትም። ሆኖም አሁን እየጠየቅን ያለነው አገሬ ትኑር ነው። ቁጭ ብለን ስለ እግዚያብሄር ብለን የምንለምንባት አገር ትኑረን፤ ምንም ይቅርብን ሰላምና አገር አንድነት ካለ አንድ ቀን ነገሮች ይሳካሉ። የሚሳኩት በአንድነትና በፍቅር ስንኖር ነው። የትግራይ ልጆች እኮ ከቀድሞ ሠራዊት ጋር ሆነው አገር ለማስከበር ደም አፍስሰዋል። ይሄንን ነው ማየትና መመዘን ያለብን።
በአሁን ሰዓት ይሄ ይደረግልኝ ይሄኛው ቀርቶብኛል የምንልበት ጊዜ አይደለም። አሁን በአንድ ላይ ተጣምረን አገርን የማዳን ጉዳይ ነው። በነገራቸን ላይ ኢትዮጵያ በድርድር በውይይት የቆመች አገር አይደለችም። በልጆቿ መስዋዕትነት በደምና በአጥንት የተገነባች አገር ነች። አሁንም ይሄን ነው የምትፈልገው ኢትዮጵያ። የጀግኖች አገር ነች፤ በጀግኖች መስዋዕትነት መቆም ያለባት አገር ነቸ። ዛሬም እንዲሁ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ያለንን ጀግንነት ስለሚያውቁ እርስ በርስ ያፋልሙናል እንጂ ቢባንኑና አይናቸው ቢከፍቱ ማንነታቸውንም ቢያውቁት ቢረዱት ነገሮች ሁሉ ይቆማሉ ብዬ ነው የማስበው። የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስቡ ሰዎች እኔ ካልመራኋት ትበተናለች የሚሉ ሰዎች እንዲህ አይነት ትውልድ እንዲበቅል አደረጉ።
የሽምቅ ውጊያ ላይ ካሎት እውቀት አኳያ አሁን የተጀመረው ዘመቻ ምን ያሀል ጊዜ ይፈጅበታል ብለው ይገምታሉ?
ጦርነት እንግዲሀ ቅድም እንደነገርኩህ መሄድ መመለስ ነው። በዚህ ጊዜ ይቋጫል ብሎ መተንበይ ይከብዳል። በተለይ ደግሞ የሽምቅ ዘዴው በሕዝብ ውስጥ ሆኖ ስለሆነ ከሕዝብ ለይቶ ለመምታት ያሉት ነገሮች ውስብስብ ይሆናሉ። ግንባር ይዞ የሚዋጋ ቢሆን ኖሮ መገመት ይቻል ነበር። ከሕዝብ ውስጥ ግን አንጥረህ ለማውጣት ግን በዚህ ጊዜ ማለት ባልችልም፣ አገራችን ከጀመረችው የለውጥ ሂደት አንጻር ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይመስለኝም። የምጥ ሰዓቶች አሉ፤ ከዚህም በላይ የምናያቸው ነገሮች ይኖራሉ ብዬ ነው የማስበው። በወታደራዊ አመለካከት የሽምቅ ውጊያው በሕዝብ ውስጥ ሆኖ ስለሆነ ለማጥፋት ጊዜ ይወስዳል ብዬ አስባለሁ።
የአሁኑ ዙር ውጊያ እስከመጨረሻው ድረስ መቀጠል አለበት ብለው ያምናሉ?
እንግዲህ የዛኛውም ቡድን ባህሪ ይወስነዋል። እንደ መንግሥት ግን ማድረግ ያለበት ምንድነው፣ በየቦታው እየመጡ እየገደሉ እየዘረፉ የሚሄዱትን ነገር የመጀመሪያ ደረጃ ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው። ሌላ ደግሞ መንግሥት ጫና እየፈጠረ በሚሄድበት ጊዜ ሌላ የዲፕሎማሲ ክስተት ሊከሰት ይችላል። የትግራይ ሕዝብም መከራዎች ችግሮች እየበዙበት ዝም ብሎ ይኖራል ብዬም አላስብም። ያ ጀግና ሕዝብ ከኢትዮጵያ ወንድሞቹ ጋር መኖር የሚናፍቅ፣ የተጋባ፣ የተዋለደና የተጋመደ ነው። እንዲህ በጥቁር መጋረጃ ውስጥ እነሱን ጉድጓድ ድረስ ተከትሎ መሄድ ያስፈልጋል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ ራሱ ብድግ ይላል ብዬ አስባለሁ። አውቀዋለሁ ሕዝቡን። እንደመንግሥት ግን እስከመጨረሻው ድረስ እልባት የመስጠት ተልዕኮ ማራመድ አለበት ብዬ አምናለሁ።
ኤርትራን በተመለከተ፣ የአሁኑ ዘመቻ ላይ ጥሪ ቢደረግላችውና ዘመቻው ላይ ቢሳተፉ ምን አስተያየት ይኖሮታል?
ኤርትራ ራሷን የቻለች አገር ናት ብለን ብናስብም፣ ኢትዮጵያውያን ነን ብለው ያመኑ ጓደኞችና ወንድሞችም አሉን። አሁን አገር ነች ብለን ዕውቅና እስከሰጠን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ማሳተፉ ላይ ዞሮ ዞሮ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ማምጣቱ ስለማይቀር ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ይመስለኛል። በጥንቃቄ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው ብዬ ነው የማስበው።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥዎት።
የትግራይን ሕዝብ እንዳንዘነጋው ነው የምሰጋው። ክፉዎች በርግጥ አድክመውናል፣ አዝለውናል። ብዙ ነገሮቸ ወደዛ ዘልቀን እንዳናይ መጋረጃ ሆነውብናል። የምንጠላው የጁንታው አካል ለኢትዮጵያም ለኢተዮጵያውያንም ግድ የሌለው ነው። ኢትዮጵያውያን ስል የትግራይንም ሕዝብ ጨምሬ ነው። ይሄንን አንድነቱን አብረን ጠብቀን ኢትዮጵያን አንድ ላይ የመስራቱ ጉዳይ ሙሉ ኢትዮጵያዊያኖች በየትኛውም አካባቢ የምንኖር ከኢትዮጵያ በላይ ሐብት አያስፈልገንም። በርካታ ገንዘብ ሰብስበን ሊሆን ይችላል፣ ፎቆቸ ሊኖረን ይችላል፣ ወልደን ከብደን ሊሆን ይችላል፣ ኹሉም የሚኖርው ግን አገር ሲኖር ነው። ካልሆነ ግን የ30 ደቂቃ ጉዳይ ነው ኹሉም ይበታተናል። ይሄ ከመሆኑ በፊት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን መከላከያ ሠራዊታችንን በመደገፍ፣ አንድነታችንን በመደገፍ፣ ከመንግስት ጎን ቆመን ይሄንን እኩይ ተግባር ይዘው የሕጻናት ደም የሚያፋስሱት እንዲወገዱ በምንችለው ኹሉ መሳተፍ አለብን።
ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013



