የሥራ ዕድል እንደ ሰማይ የራቀባቸው ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ዕጣፈንታ

0
1121

ከመዲናችን ከአዲስ አበባ ጀምሮ በየክልሉ በሚገኙ የአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ በሥራ ፍለጋ በየዕለቱ የሚባዝነውን የአምራቹን ወጣት ክፍል መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ሁኔታ መመልከት ይቻላል። በመገናኛና በአራት ኪሎ በተተከሉት የማስታወቂያ መለጠፊያ ሰሌዳዎችና ግለሰቦች ለኪራይ በሚያቀርቧቸዉ ጋዜጦች የቅጥር ማስታወቂያ ለማንበብ ቦታዉን አጣቦ የሚተራመሰው ወጣት ቀላል አይደለም።

አብዛኛውን የሥራ አጥ ቁጥር የሚሸፍኑትም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ምሩቃን ሲሆኑ፣ ትምህርታቸውን በተለያየ ምክንያት ያቋረጡና የመማር ዕድሉን ያላገኙ ወጣቶችም የችግሩ ገፈት ቀማሾች ናቸው። የአምራቹ ክፍል (ወጣቱ)ደግሞ የድህነትን ስር ለማሳረር ተስፋ የተጣለበት የማሕበረሰብ አካል ነው ተብሎ ይታመናል።

በተለይም የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ሳይማር ያስተማራቸው ማሕበረሰብ እጁን ዘርግቶ በተስፋ የሚጠብቃችው ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ በበኩሏ የድህነትን ስር በመንቀል የዕድገት ጎዳናዋን ከመጥረግ አልፎም የስልጣኔ ጫፍ ያደርሷት ዘንድ ራሷን ቀጥ አድርጋ የምታይባቸው መነፀሮቿም እነዚሁ ምሩቃን ናቸው። ነገር ግን፣ አምራቹ ኃይል በትምህርት ካሳለፈው ጊዜ ይልቅ ቅጥር ለማግኘት የሚያባክነው ጊዜ ሚዛን የደፋ በመሆኑ ከታለመው ግብ በተቃራኒ ሥራ አጥነት እየተበራከተ መጥቷል።

በኢትዮጵያ የሥራ አጡን ቁጥር እንዲጨምር ያደረጉ ብዙ ጥልቅ ግንዛቤ የሚያስፈልጋቸው ተግዳሮቶችም አልጠፉም። ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ወላጆች (በተለይም የገጠሩ ማሕበረሰብ) ልጆቻቸውን የሚያወርሷቸው ብቸኛው የሥራ ዕድል አስተምሮ የመንግሥት ደሞዝተኛ የማድረግ ዝንባሌ ነው። ዘመናትን ተሻግሮ የመጣው ይህ አስተሳሰብ ወጣቶቹ በችግሩ ሰለባ እንዲሆኑ ፈር ቀዳጅ ነው።

እንደ ኮሮና ወረሽኝና ጦርነትን የመሳሰሉት ሰው ሰራሽ ችግሮችም ሠራተኞችን ከሥራ ቦታቸው ከማፈናቀል ጀምሮ የሥራ እድል በማሳጣት የሥራ አጦችን ቁጥር ከፍ በማድረግ ኹለተኛውን ደረጃ የሚይዙ የራስ ምታቶች ሆነዋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶችና ከ2012 ጅምሮ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ለዜጎች ቅጽበታዊ ሕልፈተ-ሕይወት ምክንያት ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ኢኮኖሚያዊ ውድመትን በማስከተል ማሕበረሰቡን ከሥራ ገበታው አፈናቅለው ድሃ ማድረጋቸው የማይካድ እውነታ ነው።

በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ሥራ የማግኘት ማነቆ፣ ተማሪዎች የትምህርት ገበታቸውን እየተከታተሉ የተለያዩ የግል ሥራዎችን ከመሥራት ይልቅ የመንግሥት ቅጥርን ብቻ ተሰፋ አድርገው ማሸንከፋቸው ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ ለመቀጠር የሥራ ልምድ አምጡ በሚል ቅድመ ሁኔታ በሩን የሚዘጉባቸው አሉ። አዲስ ተመራቂን አንቀጥርም የሚል ምስጢርን በውስጡ ያነገበ የሚመስለው ችግርም ዋና ተጠቃሽ ነው። ከሚወጡ የሥራ ቅጥሮች መካከል የተመረቁበትን የትምህርት ዘርፍ በዝርዘሩ ውስጥ በማግኘታቸው ተደስተው ሳይጨርሱ፣ ቅጥሩ የሥራ ልምድ መስፈረትን በማቅረቡ ምክንያት ጭላንጭል ተስፋቸው ጫፍ ሳይደርስ የሚቀሩት ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙ ምሩቃን የሚስተዋሉበት ወቅት ሆኗል።

ሌላኛውና የመጨረሻው ዋነኛ ለሥራ አጥነት መስፋፋት ምክንያት የግል ሥራን ለመጀመር ሲታሰብ ቀድሞ የሚጋረጠው የኢኮኖሚ እጥረት ሲሆን፣ ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ አዲስ የሥራ መስክ መፈለግና የተገኘውን ማንኛውንም ሥራ ዝቅ ብሎ የመሥራት ባህል አለማዳበራቸውም ይጠቀሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2014 የበጀት ዓመት ዕቅዱን አስመልክቶ ባደረገው ውይይት ከአንዳንድ አስፈላጊ ቦታዎች ውጭ በበጀት ዓመቱ አዲስ ቅጥር አልፈጽምም ማለቱ የሚታወስ ነው።
በአገራችን ኢትዮጵያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዜጎችን በሥራ በማሠማራት ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱ ተቋማት ናቸው። የመንግሥት ተቋማት በየዓመቱ በርካታ ምሩቃንን በመቅጠር ብዙውን ዜጋ አቅፈው በመያዛቸው ይታወቃሉ። ይህ ሆኖም ግን የሥራ አጡን ብዛት በተፈለገው ልክ መቀነስ አልተቻለም። ተስፋ የተጣለበት መንግስት በ2014 የበጀት ዓመት ከአሁን በፊት እንደተለመደው ቅጥርን እንደማያስተናግድ ከመግለጹ ጋር ተያይዞ የሥራ አጡ ዕጣፈንታ ምን ይሆን? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው።

2014 ለሥራ ፈላጊዎች የራስ ምታት ዓመት ይሆናል ይላል ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገው ስማቸው መለሰ። ተወልዶ ያደገው ጎንደር ከተማ ነው። እድሜው ለትምህርት እንደደረሰ በጎንደር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን መከታተል የቻለ ሲሆን፤ በ2010 ከዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ ለመመረቅ በቅቷል። ሆኖም ግን ከተመረቀ በኋላ ነገሮች እንዳሰባቸው ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ስማቸው ከተመረቀ ከ2010 ጀምሮ ሥራ በመፈለግ ላይ ይገኛል። በትምህርት ካሳለፈው ጊዜ በበለጠ በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ቅጥር በመፈለግ የደከመው ድካም ሚዛን የደፋ ነው። በአዲስ አበባ ሙሉ ጊዜውን ያሳለፈው በመገናኛና በአራት ኪሎ ለቅጥር መለጠፊያ በተተከሉ ሰሌዳዎች (ቦርዶች) በመዘዋወር ነው። የሥራ ቅጥር መለጠፊያ ቦርዶችንና ጋዜጦችን ለማንበብ ማለዳ የሚያዜሙትን ወፎች ድምጽ እንደሰማ የዘወትር ልማዱ የሆነውን ሥራ ፍለጋ ጉዞውን ይጀምራል።
የተለያዩ የቅጥር ማስታወቂያዎች የሚደሰኮሩባቸውን ድረ ገጾች በየዕለቱ መጎብኘትም የሁልጊዜ ተግባሩ ሆኗል። እርሱን የሚጋብዝ ቅጥር በወጣበት ቦታ ሲቪውን ለማስገባት ብዙ ተሯሩጧል። ለዚህም ቅጥር የሚያወጡ የግልም ሆኑ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዘንድ የሚገኙ የሥራ ደብዳቤዎቹ ምስክሮቹ ናቸው። ለኮፒና ለፕሪንት ያወጣው ወጭ በቀላል የሚገመት አይደለም። ሆኖም ግን አንድም ለፈተና እንኳን የጠራው መሥሪያ ቤት የለም።

ስማቸው ከላይ በተዘረዘሩት የሥራ ማፈላለጊያ መንገዶችን ብቻ በመጠቀም ደከመኝ ብሎ ሥራ ከማፈላለግ አበልቦዘነም። ቅጥር ከሚያወጡት ተቋማት የትምህርት ማስረጃውን እያስገባ ሌላ ቅጥር የማግኛ ዘዴ መፈለጉን ተያይዞታል።
አንድ ቀን አእምሮው ካሁን በፊት አንሾካሽኮለት የማያውቅ አዲስ ሐሳብ ፍንትው አድርጎ አሳየው። ይህም ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎችን ለማነጋገር መሞከር ነው። ኤጀንሲዎችን ማግኘቱ ተሳከቶለት አዲስ አበባ 22 ጎላጎል አካባቢ የሚገኙ መሆናቸውን በመግለጽ በቅድሚያ ለምዝገባ 300 ብር ትከፍላለህ መባሉን ይናገራል። ከኪራይ ቤትና ከትራንስፖርት ጋር በመተጋገዝ ኮፒና ፕሪንት ያዳከሟት ከኪሱ የቀረችውን ብር ከፍሎ ተመዘገበ። ተመዝጋቢዎች ቁጥራቸዉ ሰባት እስከሚሞላ መጠበቅ እንዳለበትና ሥራ ሲገኝ እንደሚደወልለት ተነግሮት ተሰናበተ።

ስማቸው ከኪሱ የነበረችው ብር እየተጠናቀቀች ቢሆንም ኤጀንሲዎቹ አልደወሉለትም፤ ሲደውልላቸውም ቀን ከመቅጠር የዘለለ ተስፋ ሊቸሩት አልቻሉም። ሥራ አግኝቶ ራሱን ከመምራት አልፎ አስተምረው ያስመረቁትን ቤተሰቦቹንና ተስፋ የጣለችበት አገሩን የሚያገለግልበት ጊዜ እንደረፈደና ያቀደዉ ዕቅድ ዕውን እንዳልሆነ ተሰማው።

በኢንጅነሪግ ሙያ የሰለጠነው ወጣት ስማቸው ቀኖችን በአጣብቂኝ ሁኔታ እየመራ ነው። አሁንም ቢሆን ለሥራ የደወለለት መስሪያ ቤት የለም። ቢሆንም ግን የቅጥርን ፍለጋ ብቻ ተስፋ ሰንቆ የኖረውን ከንቱ አስተሳሰቡን እንጂ፣ ትምህርት ላይ ያሳለፈውን ጊዜ ሊወቅስ አልወደደም። ዩኒቨርስቲዎችን በመገንባትና ለፍጆታ ከፍተኛ ወጭ በማውጣት ተማሪዎችን አስመርቆ ወደ ሥራ የማስገባት ተግባር ያስለመደውን መንግሥት፣ “ግን ለምን ለኔ ቦታ አጣ” በማለት ሳይበሳጭበት የቀረ አይመስልም።

“ለእውቀት ከመማር ይልቅ ለቅጥር መማርን ከማሰብ የሚበልጥ የሞኝነት አስተሳሰብ የለም’’ በማለት ምክሩን የሚለግሰን ወጣት ስማቸው፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቅጥር በመፈለግ ያባከናቸው ጊዜያት ዋጋ እንደሚያስከፍሉት በማመንና ጎንበስ ብሎ ይቅርታ በመጠየቅ የራሱን የግል ሥራ መጀመር ሌላ ምርጫ የማያሻው ተመራጭ ተግባር እንደሆነ በማመኑ ከዚህ በኋላ ከመንግሥት የሥራ ቅጥርን እንደማይጠብቅ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
አሁን ላይ ሲያስበው በመንግሥትም ሆነ በግል መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ ከሚያገኘው ገቢ ይልቅ፣ በሰለጠነበት ሙያ የግል ሥራውን ቢሠራ የተሻለ ገቢ እንደሚያገኝ ይሰማዋል።

ስማቸው መለሰ ለዚህም ለውጥ መገኘት እንደምክንያትነት የሚናገረው “የመንግሥትም ሆነ የግል መሥሪያ ቤት እኔን የሚቀጥረኝ በምሠራለት ሥራ አማካይነት ለኔ ከሚያወጣው ደሞዝ በተጨማሪ ሥራውን በማከናወኔ ከኔ የሚያገኘው ትርፍ ስላለ ነው፤ በመሆኑም የግል ሥራየን ብሠራ ይህን ትርፍ ለራሴ ገቢ ማድረግ ስለምችል ተቀጥሬ ከማገኘው ገቢ ይልቅ በግሌ ብሠራ የማገኘው ገቢ በጣም የተሻለ ነው’’ ይላል።

የግል ሥራውን ለመሥራት ያቀደው የ2010 የኢንጂነሪንግ ምርቁ ወጣት ስማቸው፣ ካለበት የኑሮ አጠብቂኝ ወጥቶ በግል ድርጂቱ ሌሎችንም የማሳተፍ ሕልም እንዳለው ነው የተናገረው። መንግሥት በ2014 የበጀት አመት አዲስ ተመራቂዎችን ሥራ አልቀጥርም ማለቱ የተመራቂውን ሥነ-ልቦና ይጎዳል። በመማር ላይ ያሉትንም ተስፋ ያስቆርጣል። በመሆኑም መንግሥት ወጣቱን እያደራጀ የሥራ ዕድል ቢፈጥርና ወጣቶችም ለትምህርት ያሳለፉትን ጊዜ ከመርገም ይልቅ የቀሰሙትን ዕውቀት በመጠቀም ለሥራ ፈጠራ መነሳሳቱ ብቸኛው አማራጭ ነው ሲልም ነው ምክሩን የለገሰን።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከኢኮኖሚ ባለሙያው ዋሲሁን በላይ ጋር ቆይታ አድርጋለች። ዋሲሁን መንግሥት በ2014 የበጀት ዓመት አዲስ ተመራቂዎችን አልቀጥርም ያለበት ምክንያት በስሩ የሚያስተዳድራቸው ሠራተኞች የደሞዝ መሻሻል ካልተደረገልን የኑሮ ውድነት እያሸነፈን ነው ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ ለመመለስ በጀት መቆጠብ ስላለበት ነው። የመንግሥትን ቅጥር ተስፋ አድርጎ የሚጓዘው የወጣቱ ክፍል ከዚህ አስተሳሰብ ወጥቶ ሥራ የመፍጠር ባህልን በማዳበር የግል ሴክተሮች እንዲስፋፉ ለማድረግ እና አገሪቱ ካላት ኢኮኖሚ አንጻር ሠራተኞችን የምትቀጥረው በዝቅተኛ ደሞዝ ስለሆነ፣ በዚህም ከእጅ ወደ አፍ እንኳን የማይሆን ደሞዝ እድገት ማምጣት ስለሚያስቸግር እነዚህን ሰፋፊ ችግሮች ለማጥበብ ነው በማለት የግል አስተያየታቸውን አካፍለዋል።

ዋሲሁን መንግስት የያዘዉ አቋም ባይከፋም የግል ሴክተሮችን ለማስፋፋት ወጣቱን በማደራጀት የሥራ ዕድል የመፍጠር ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ሳይጠቁሙ አልቀሩም። በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ ለዘመናት ስር ሰዶ ያለው አስተሳሰብ ከትምህርት የሚገኘው ውጤት ተመርቆ በመቀጠር ድህነትን ማባረር በመሆኑ ይህን አስተሳሰብ በማንገብ የሚማሩ ተማሪዎች ቅጥር በሚያጡበት ወቅት ከፍተኛ የሞራል ውድቀት ይገጥማቸዋልም ብለዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያው ዋሲሁን አያይዘውም፣ ይህ ድርጊት ኢኮኖሚያዊ፤ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ችግር ስለሚፈጥር ይህን ለመፍታት መንግሥት፤ ወላጆችና የተመረቁም ሆነ ያልተመረቁ ሥራ ፈላጊዎች የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። መንግሥት በዩኒቨርስቲና ኮሌጅ የሚመረቁ ተማሪዎች እስካሁን የተለመደውን ትምህርት ከማስተማር ባሻገር አዲስ የሥራ ፈጠራ ትምህርት አጠናክሮ በመስጠት ከቅጥር ዕሳቤ አንዲወጡና የግል ሥራ የመሥራት ባህልን እንዲያዳብሩ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንዳለበት ተናግረዋል።

የግብርና ባለሙያዎች ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ የማስገባት ኃላፊነታቸውን በመወጣት፣ ወላጆችም የሥራ ዕድል ሲጠፋ የልጆቻቸው አእምሮ እንደሚጎዳ በመገንዘብ፣ በግል ሥራ ማሰማራትና ለሥራ ፈጠራ የሚያግዝ ተጨማሪ ትምህርት በማሰተማር፣ ወጣቶች ቅጥርን ከመጠበቅ ይልቅ ጊዜን ተጠቅሞ በግል መንቀሳቀስ ይበልጥ ውጤታማ አንደሚያደርግ ግንዛቤያቸውን በማስፋት፣ የሥራ አጥነት መስፋፋትን መቀነስ እንደሚቻል ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here