ኢትዮጵያና የውጭ አገራት ተጽዕኖ

0
694

ኢትዮጵያ እንደማንኛቸውም የአፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከተጫነባት ከድህነት መውጣት ሊከብዳት እንደሚችል ይታመናል፡፡ ቢሆንም ግን ለኢኮኖሚ ጫና ፍራቻ ተብሎ የአገርን ሕልውና ማስደፈር እንደሌለብን ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ የውጭ አገራት ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ማድረጋቸው ኢትዮጵያን በምን መልኩ እንደሚጠቅም እና እንደሚጎዳ ጂኦፖለቲክስ ያወጣውን ‹‹ከባስማ እስከ ኢትዮጵያ›› ጽሁፍ በመመስረት፣ምሁራንን በመጠየቅ፣ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ሐሳቦችን በመዳሰስ፣ ታሪኮች እና ጥናቶችን በማገላበጥ የአዲስ ማለዳዋ ሰላማዊት መንገሻ የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጋዋለች፡፡

ኢትዮጵያ ችግሮቿን እንደ ቤት ልጅ ሸፋፍና መኖር ሲገባት የእርስ በርስ አለመስማማቶችን እያጎላች ለውጭ ወራሪ ኃይል በር እየከፈተች ያለች ይመስላል። የትኛቸውም የአውሮፓ አገራት የአፍሪካ አገራት ዕድገት ይቅርና በአስተሳሰብ ለውጥ እንኳን እንዲያመጡ አይፈልጉም። ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ›› እንደሚባለው አሁን ላይ ያሉ ጦርነቶች፣ መፈናቀሎች እና የእርስበርስ ግጭቶች የእያንዳንዳችን ጉሮሮ ወደሚዘጋ እንቅስቃሴ እየሄዱ ያለ ይመስላል።
‹ጂኦፖለቲክስ› ከኹለት ሳምንት በፊት ‹‹ከባስማ እስከ ኢትዮጵያ›› በሚል ያወጣው ጥናት አውሮፓውያን ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራቸው ምን እንደሚመስል ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። አውሮፓውያን የአፍሪካ አገራትን ከሚያስፈራሩበት አንዱ መንገዳቸው የኢኮኖሚ ጫና ማሳደር ነው። ይህን የኢኮኖሚ ጫና የሚፈጥሩት ደግሞ አገራቱ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን በማድረግ ነው።

የአሜሪካ የዓለም ዐቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስ ኤይድ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ለአራት ቀናት በሱዳን ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው በርካታ ኢትዮጵያውንን ስጋት ላይ የጣለ ነበር። ወደ አዲስ አበባ ይዘው የሚገቡት አጀንዳ ምን እንደነበር ብዙ ግምቶች ነበሩ። በሱዳን የቆዩትም ምናልባት ለአሸባሪው የሕወሓት ቡድን በር ለማስከፈት ይሆናል የሚል ስጋትም ነበር። ምናልባት ይህን ስጋት ከሚያረጋግጡ ጉዳዮች አንዱ በኢትዮጵያ በቆዩበት ወቅት የተናገሩት የሰብዓዊ ዕርዳታ ለትግራይ መድረስ አለበት የሚል የደግነት ተልዕኮ የሚመስል፣ ነገር ግን ሕወሓትን የሚደግፍ ሴራ ያዘለ መልዕክት ነው። በትዊተር ገጻቸው ላይም ‹‹ኢትዮጵያ በመጋዘኗ ውስጥ 58ሺሕ ሜትሪክ ቶን ምግብ ክምችት አላት። ይህ ክምችት እንኳን ለትግራይ ሕዝብ ከዛም ላለፈ ማሕበረሰብ እንደሚጠቅም እና በፍጥነት እንዲደርስ›› የሚል ትዕዛዝ መሰል መልዕክት አስተላልፈዋል።

አንዳንድ የምዕራብ አገራት በሰብዓዊ ዕርዳታ ሰበብ በሱዳን በኩል የማጓጓዣ መንገድ እንዲከፈት የሚያደርጉ ጥያቄዎች እያነሱ ይገኛሉ። የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የከፈተው ድምበር አለፍ ጦርነት ደግሞ በሌሎች አማራጭ መንገዶች ማለትም በአፋርና በአማራ ክልል የሚገቡትን እርዳታዎች እያስተጓጎለ ይገኛል።

አሜሪካም ይህንን የሕወሓቶች ማስተጓጎል በመደገፍ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ጫና በመፍጠር ላይ ትገኛለች። ለዚህም ነው የሳማንታ መምጣት አንዱ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ከሚደረጉ ተግባራት መካከል ነው ተብሎ የተፈራው።
በሱዳን በኩል እንዲከፈት የተፈለገው የዕርዳታ ማስገቢያ መንገድ የጦር መሳሪያ እንዲተላለፍ ከመፈለግ አንጻር እንጂ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ አይደለም የሚሉ ሰዎችም አሉ። የሰብዓዊ እርዳታ በአማራና በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ክልል መግባት እየቻለ በሱዳን በኩል ሌላ አማራጭ ይከፈት ማለት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራ መሆኑን የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል። የብሔራዊ የአደጋና ስጋት አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው፣ አሸባሪው ሕወሓት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ 170 ተሽከርካሪዎችን እንዳስቆመ ገልጸዋል።

ምዕራባውያን አፍሪካ አገራት ላይ የሚፈጠሩ እሳቶችን እፍ እፍ እያሉ ማባባስ የሁልጊዜም ተግባራቸው ነው። አሁን ደግሞ ከጊዜ በኋላ መንግሥት ሕወሓትን አሸባሪ ብሎ በመፈረጁ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲበረታ አድርጎታል። ምሁራን የሚስማሙበት ሐሳብም ምዕራባውያን ከሕወሓት ጎን በመቆም ከመንግሥት ጋር እንዳይስማሙ የተፈለገው አሜሪካ በኢትዮጵያ የምትገዛው መንግሥት እንዲኖር ለማድረግ መፈለጉ የሚለውን ነው።

አሜሪካ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመራርን እጅ መጠምዘዝ ስላልቻለች ጫናዋን ያበረታች ይመስላል። ምስራቅ አፍሪካ የምታድግ ከሆነ ምዕራባውያን አይናቸው ደም ለብሶ መታየታቸው አይቀርም። የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ክሶች እያነሳች የምትገኘው አሜሪካ ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ተቀባይነት እንዳታገኝ እየጣረች እንደሆነ ግልጽ ነው። የአሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት መግለጫዎችና ፖሊሲ አውጪዎቻቸው በተለያዩ ገጾች የሚጽፉትም ኢትዮጵያን የሚንቅ ነው። በአጸፋውም ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የወሰነችው ውሳኔ የዓለም ዐቀፉን ተጽዕኖ ችላ ማለቷን የሚያሳይ ነው።

የአሜሪካው የባይደን አስተዳደር ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካ ማዕቀቦች በመጠቀም እያስፈራራ ይገኛል። የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጀት ለኢትዮጵያ ብድር እንዳይሰጡ በአሜሪካ ጫና እየተደረገባቸው ነው።
የአሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ሰኔ 14 ለተካሄደው ምርጫ ዕውቅና መስጠት አለመፈለጋቸውም አንዱ ማዕቀቡን የሚያጎላ ነው።

ጂኦፖለቲክስ ያወጣው ‹‹ከባስማ እስከ ኢትዮጵያ›› (Basma to Ethiopia) የተሰኘ የC2FC ፕሮጀክት የአውሮፓውያን ሴራ በስፋት ይዞ እናገኘዋለን። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ2019 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው አንዱ አውሮፓውያኑን ቂም እንዲቋጥሩ ያደረገ ተግባር ነው። የሰላም ሽልማት ያገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር የአገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ አልቻሉም በማለት የተለያዩ ሪፖርቶችን እያወጡ ነበር። በወለጋ፣ ጉጂ፣ መተከል እና ጋምቤላ ላይ የነበሩ መፈናቀሎችን እና አለመረጋጋትን የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር አድርጎ የአውሮፓ ሕብረት አውጥቶት የነበረው ሪፖርት ለዚህ ማሳያ የሚሆን ነው።

የአሜሪካን መንግሥት አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በማለት በዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት ለማቆም ሽርጉድ እያለ እንደሆነ ጂኦፖለቲክስ አስነብቧል። ጽሑፉ አክሎም ለመጨረሻ ጊዜ ከተከሰሰው የዩጎስላቪያው መሪ ስሎቮደን ሚሎሶቪች ቀጥሎ በዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት የሚከሰሱ መሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው የገለጸው። በዚህም ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደርን ከጨዋታው ውጭ ለማድረግ እና የቀድሞው አገዛዝን (ሕወሓት) ወደ ሥልጣን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በዚህ ወቅት ይላል ጽሑፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሥልጣን መብቱን እንደ ቻይናው ዢጂንፒን እና እንደ በሽር አል አሳድ የሥልጣን ወንበሩን ካላስከበረ ከባድ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ እንደሚከቱት ይገልጻል። ለዚህም ይላል ጂኢፖለቲክስ በጽሑፉ፣ ዐቢይ አሕመድ ጠንካራ የሆነ የአስተዳደር መስፈርቶችን መጠቀም እና የሚዲያ ፕሮፖጋንዳዎችን አጠናክሮ መያዝ ይገባዋል ይላል።

በተለይ የመረጃ ፍሰት ዋነኛው የፕሮፖጋንዳ ማሳተላለፊያ ሰንሰለት መሆኑን አንስቷል። የመረጃ አቅምን መገንባት ለማንኛውም የፕሮጋንዳ ዘመቻ ቁልፍ ነው። የባስማ ፕሮጀክት ተብሎ የተነደፈው ፕሮጀክት ሶሪያን ለማፈራረስ አውሮፓውያን የተጠቀሙበት አንደኛው መንገድ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ላይ ለመተግበር ዝግጅት ላይ እንዳሉ የሚያሳይ ነው።ባስማ ማለት ከማሕበረሰቡ የተወጣጡ ጋዜጠኞች ስብስብ የሚመሰርቱት መዋቅር ሲሆን፣ በርካታ የውስጥ መረጃዎች ሾልከው እንዲወጡ የማድረግ አቅም ያለው ትልቅ ፕሮጀክት ነው። ይህንን ፕሮጀክትም ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ አክቲቪስቶች የሚመለመሉ ሲሆን፣ በተለያዩ ሚዲያዎች አገር አፍራሽ ሐሳባቸውን እንዲያሰራጩ የሚያደርግ ነው።

እነዚህ ጋዜጠኞች ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ጥሬ መረጃን ይሰበስባሉ፣ መረጃውም በማኅበራዊ ሚዲያ እንዲሰራጭ ይደረጋል። በትግራይ ክልል ያሉት የሕወሓት አባላትም ይህንን ፕሮጀክት እየተገበሩት ይገኛሉ። እነዚህ በታለመላቸው መንገድ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በ2021 በኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሚንቀሳቀሱ ወይም ለኢትዮጵያ መንግሥት ተባባሪ የሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን በመለየት ለአሜሪካ ረዳቶቻቸው ያስተላልፋሉ።
የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ የምዕራቡ ዓለም ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል አዲስ አበባ ላይ በአማጽያን ጥምረት ሥልጣን የሚይዝ የብሔር መንግሥት ማደራጀት አንዱ ነው።

በኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት፣ በኦሮሚያ ክልል ያለው የታጠቀ አማጺ ቡድን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት እና የትግራይ በሔራዊ መንግሥት አገዛዝ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚያስተባብሯቸው አካላት ዋናዋናዎቹ ናቸው።

ሕወሓት በአማራ ክልል የትግራይ ሕጻናትን ጠመንጃ በመስጠት በጦርነት ሲማግዳቸው ከርሟል። በትግራይም የእርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት 2.3 ሚሊዮን ዜጎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል፤ 5.2 ሚሊዮን ሰዎች ለረሀብ ተጋልጠዋል። 87 በመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማት ወድመዋል። 71 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ተቃጥለዋል። የትግራይ ተወላጆችም ይህ የተደረገው ከኤርትራ እና ሱማሊያ ወታደሮች እንዲገቡ ተደርጎነው ይላሉ።
ኹሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያውቀው ሶሪያ፣ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ የመን እና አፍጋኒስታን ላይ የደረሰው ጦርነት አውሮፓውያን እና አሜሪካ የፈጠሩት ነው።

በኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ የሕወሓት ደጋፊዎች፣ ምሁራን፣ ጠበቆች፣ የዲሞክራሲ አራማጆች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የስለላ ተቋማት ዐቢይ አሕመድ በዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት በሰው ልጆች ላይ በሚፈጸም ወንጀል እንዲከሰሱ የተቀናጀ ጥሪ እያደደረጉ ነው። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ማዕቀብና አለመረጋጋት እንዲመጣ መንገድ የሚከፍት ነው።

ምዕራባውያን አፍሪካን ባለፉት 500 ዓመታት ከጥሬ ዕቃ አንስቶ እስከ ተፈጥሮ ሀብት በመዝረፍ ሀብታም ሆነዋል። ላለፉት 150 ዓመታት ደግሞ ሽኩቻን በመጠቀም አፍሪካ ያላትን ሀብት ሲዘርፉ ነበር። አፍሪካውያንን በብሔር ግጭት እና ጦርነት አእምሮአቸውን እያጠበቡ ምዕራባውያን ያለንን ሀብት ሲቀራመቱ ቆይተዋል።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ያከናወነችው የዓባይ ግድብ ሙሌት የውጭ ኃይላን ልዩነታችንን ለማጠንከር በሚጥሩበት ወቅት መሆኑ እጅግ አስደንግጧቸዋል።
አውሮፓውያን አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ አድርገናል አላሉም ሲሉ የምጣኔ ሀብት ተንታኙ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

‹‹የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ እርዳታ ያደረጋል። አሜሪካ፣ ቻይናና ጃፓንም ከፍተኛ እርዳታ የሚያደርጉ ናቸው። በምርጫ 97 ጊዜ የተቃዋሚዎችን መታሰር ተከትሎ በርካታ አገራት በሌሎች መንገዶች እርዳታ ሲያደርጉ ነበር። ይህንንም ያደረጉ የነበረው ግራንት የሚያስቀሩ ከሆነ በኢኮኖሚው ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል በሚል ነው›› ሲሉ ቆስጠንጢኖስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የካፒታሊስት አስተሳሰብ ያላቸው ምዕራባውያን ይህ ዓለም እና የተፈጥሮ ሀብቱ የእነሱ እንደሆኑ ያምናሉ። ሌሎች ነጭ ያልሆኑ አገሮች ሀብቶቻቸውን፣ ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሳድጉ ሊፈቀድላቸው አይገባም። በተለይ ጥቁር አፍሪካ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ወጥነት ያለው ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ሥርዓት እንድታዳብር ሊፈቀድላት አይገባም ብለው ያምናሉ።

በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርተው ሌሎች አገራት ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሳድጉ መፍቀድ ማለት እነዚህ አገሮች ራሳቸውን ችለው በራሳቸው ይኑሩ ማለት ነው። ስለዚህ በአፍሪካ አገራት ውስጥ ጦርነቶችን በማነሳሳት ከውስጥም ከውጭም መረበሽ አለባቸው።

ምዕራባውያን ሀብቶቻቸውን እንዲሰርቁ አፍሪካ የጦርነት ቀጠና መሆን አለባት። ሆኖም ለአህጉሪቱ ውድቀት ምዕራባዊያን ብቻ ተጠያቂ አይደሉም። የአፍሪካ ምሁራን፣ በተለይም ኢትዮጵያውያን ይህንን መረዳት ያስፈልጋቸዋል። እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ምሁራን አሜሪካ ኢትዮጵያን እንደምትወድ ያምኑ ነበር፣ ስለሆነም የተበላሸች ወይም የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ማየት ለእሷ ጥቅም የለውም። አሁን አሜሪካ እና ብሪታኒያ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ኹሉንም ነገር ሲያደርጉ እናያለን።
ይህ ታሪካዊ እውነታ ነው። በባሪያ ንግድ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ተይዘው በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል ተሽጠዋል። ይህ ሲያልቅ ጥሬ ዕቃዎቻችንን ዘረፈዋል። ከአፍሪካ ቅኝ ተገዥነት በኋላ ፣ ለየራሳቸው ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማምጣት የሞከሩ ብዙ የአህጉሪቱ መሪዎችን ገድለዋል ወይም አሳደዋል። የጋናው ክዋሜ ንክሩማ ፣ የኮንጎ ፓትሪስ ሉሙምባ ፣ የናይጄሪያ ታፈዋ ባሌዋ እና የ ቡርኪና ፋሶው ቶማስ ሳንካራ የሚታወሱ የምዕራባውያን ሰለባ የሆኑ አፍሪካውያን መሪዎች ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ማተኮራቸው እና ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከዓለም ካርታ ለማጥፋት መፈለጋቸው አያስገርም። ኢትዮጵያ ነጭ ዘረኞችን በብዙ መንገድ ትቃወማለች፤ ለአፍሪካ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ዘመቻ መነሻም ሆናለች።

የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየሆነ እንዳለ በጥንቃቄ መመልከት እና ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የምታደርገውን ትግል መደገፍ አለባቸው። ዛሬ ባደጉት አገራት መንግሥታት እና ሚዲያዎቻቸው የገንዘብ ድጋፍና ዲፕሎማሲ የሚዘወረው ኢትዮጵያን የማጠልሸትና የመበታተን ሴራ ነገ ጂቡቲ፣ኬንያ ወይም ታንዛኒያ አለበለዚያም የትኛውም የአፍሪካ አገር ላይ ላለመደገሙ ማረጋገጫ የለም።
‹‹ከባስማ እስከ ኢትዮጵያ›› ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ላይ እንዳይተገበር ማድረግ እንደሚገባን ምሁራን ይስማማሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here