በ16ቱ ቀናት

Views: 431

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ፆታዊ ጥቃትን በመቃወም የሚደረገው የ16 ቀናት ንቅናቄ በዓለም ደረጃ “በእኩልነት የሚያምን ትውልድ አስገድዶ መድፈርን ይጠየፋል” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል። ይህ ንቅናቄ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1991 በዓለም አቀፉ የሴቶች አመራር ተቋም (Center for Women’s Global Leadership) አስተባባሪነት ነው።

ይህ ንቅናቄ ዘንድሮ በዓለም ለ28ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ ነው እየተከበረ ያለው። ይህን አስመልክቶ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው ዘገባ፤ በጠቅላላ በዓለማችን ካሉ ሴቶች ሃምሳ በመቶ የሚሆኑት አንድ ወይም ሌላ ዓይነት ጾታዊ ጥቃት ያጋጥማቸዋል ይላል።

በኢትዮጵያም 26 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፤ ይላል ዘገባው። በሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የተለያየ መልክ ቢኖራቸውም ዋነኛ መንስኤዎች የስርዓተ-ጾታ እኩልነት አለመከበር፣ የተዛቡ አመለካከቶች፣ ልማዶች እና ባህሎች ናቸው።

ይህ ከኅዳር 16 እስክ ኅዳር 30 የሚዘልቀው ንቅናቄ በኢትዮጵያ ላለፉት 14 ዓመታት የተከበረ ቢሆንም ጥቃቱን ግን ማስቀረት አልቻለም። ጥቃት ይቅርና አመለካከት ላይ እንኳ ገና አርባ ዓመት ቢሠራም የማያልቅ የሚመስል የቤት ሥራ ተሸክመን እንዳለን እንዲሰማን ያደርጋል። በእርግጥ በሌላው ማኅበራዊና ሳይንሳዊ ዘርፍ ሠለጠኑ በተባሉ አገራትም ችግሩ ያለ መሆኑ፤ ዓለምም ገና ያልተረዳውና ያልገባው እውነት እንዳለ ሹክ ይለናል።

ዘንድሮ ትኩረቱ ጥቃት ላይ ነው። ይህም በሴቶች ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ዓይነት ጥቃቶች ይቁሙ የሚባልበት ንቅናቄ ነው። ንቅናቄው በአገራችን የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ጋር በተገናኘ እንደተደረገው እንቅስቃሴ፣ ፍሬያማና ውጤታማ እንዲሆን አድርጎ መተለምና መንቀሳቀስ ሳያስፈልግ አይቀርም። ይህን በተመለከተ በተለይ በጉዳዩ ላይ የሚሠሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የንቅናቄ ሰሞኑን በድግስ፣ እንደው ተከውኗል ለማለት የሚደረግ ሳይሆን የማይረሳና የትልቅ ለውጥ ጅማሮ አድርጎ ማሳለፍ ተገቢ ነው።

ሴቶችንና ሕጻናትን በተመለከተ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ብዙውን ጊዜ የሚባክኑ ሆነው ይሰሙኛል። ግንዛቤ ከማስጨበጥ አቅም እንኳ ጫን ተብሎ ሲሠራ አናይም። ዶክተር ቦጋለች ገብሬ (ነፍስ ይማር) በዚህ ላይ ሊደነቁ የሚገባቸው ሴት እንደሆኑ አምናለሁ።

በተለይም ለሴቶች መብት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ በከንባታ ነዋሪ የሆኑ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ወጥተው እንዲናገሩ መድረክ በመፍጠር፣ ወድደው ባልሆኑትና ባላደረጉት ነገር ሳይሸማቀቁ፤ ብርታታቸው ለሌሎች እህቶቻቸውና ልጆቻቸው ምሳሌ እንዲሆን፤ ጥቃት ፈጻሚዎችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና ልብ እንዲገዙ፤ ሕግም አቤት እንዲል መንገድ ሲከፍቱ፤ ያም በተግባር የታየ ለውጥ ሲያመጣ አይተናል።

በእርግጥ ንቅናቄውም ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ማሳወቅ፣ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል ወንዶች ያላቸው ሚና ላይ ትኩረት አድርጎ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግ፣ ጥቃቱን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ያሉ የሕግ፣ የፖሊሲና ተቋማዊ ሥራዎችን ማጠናከርና የመሳሰለው ዓላማው ነው።

ከንቅናቄው ጋር ተያይዞ ዓለም ዐቀፍ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የማስወገድ ቀን፣ ዓለም ዐቀፍ የሴት ሰብዓዊ መብት ተሞጋቾች ቀን፣ ዓለም ዐቀፍ የኤድስ ቀን፣ ዓለም ዐቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን፣ ዓለም ዐቀፍ የበጎ አድራጎት ቀን፣ በካናዳ ሞንትሪያል የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እ.ኤ.አ በ1989 የተገደሉትን 14 ሴቶች የማሰብና የማስታወስ ቀን እንዲሁም ኅዳር 30 ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን በ16ቱ የንቅናቄ ቀናት ውስጥ የሚከበሩ ናቸው።

የወንዶችን ተሳትፎ የሚመለከተው የነጭ ሪቫን ንቅናቄም አብሮ የሚካሔድ ነው። ወንዶች ነጭ ሪቫን ሲያደርጉ በሴቶች ላይ ጥቃት አልፈጽምም፣ የሚፈጽሙትን አወግዛለሁ፣ ሲፈጸምም ዝም አልልም ሲሉ ነው። ወንድሞች ሆይ! እባካችሁ ቃላችሁን አክብሩ!
በሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com