የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል አስገነባ

0
1662

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ አግልግሎቴን ያፋጥንልኛል ያለውን የመረጃ ማዕከል/Data Center/ 49.6 ሚሊዮን ብር ወጪ አድረጎ ማስገንባቱን የኤጀንሲው ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አብድራሒም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ኤጀንሲው ያስገነባው የመረጃ ማዕከል ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ዘመናዊ የሆነ ሞጁላር የመረጃ ማዕከል ነው ሲሉም ይገልጻሉ። አስተማማኝ የአደጋ መከላከያ ስርዓትና ከፍተኛ የሆነ መረጃ የመያዝ አቅም ኖሮት ተገንብቷል።
የመረጃ ማዕከሉን ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጋር በመሆን ከወረዳዎች ጋር የማገናኘት ሥራ ለመሥራት እየተዘጋጁ መሆናቸውን መሐመድ ይገልጻሉ።
ይህ የመረጃ ማዕከል ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያጋጥሙ የኔትወርክ መቆራረጥ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ከወረዳ እስከ ማዕከል ለማገናኘት የሚያስችል ፕራይቬት ኔትወርክ/VPN/ ለመዘርጋት ያስችለው ዘንድ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት ማድረጉን መሐመድ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ እየተጠቀመበት ያለው ወረዳ ኔት፣ ኹሉም የመንግሥት ጽሕፈት ቤቶች የሚጠቀሙት በመሆኑ ሲስተም ሳይቆራረጥ አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ ለመሥራት እንዲቻል ተቋሙ የራሱን ፕራይቬት ኔትወርክ /VPN/መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኘቷል። ኤጀንሲው በ108 ወረዳዎች ላይ ራሱን የቻለ የወረዳኔት መስመር እንዲኖራቸው በማድረግ ለሕብረተሰቡ ሲስተም ሳይቆራረጥ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል ሥራውን ለመጀመር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት መደረጉን ኤጀንሲው አስታውቋል።
በአሁን ሰዓት እንደዚህ ያሉ አገልግሎቶችን በብቸኝነት ከሚሰጠው ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን ያሉትን መሥሪያ ቤቶች ለይቶ ወደ የዳሰሳ ጥናት ሥራ መገባቱንም ይጠቅሳሉ።
በሌላ በኩል፣ ኤጀንሲው ከ1935 ጀምሮ ያሉትን ፋይሎች ወደ ዲጂታል የመቀየር ሒደት መጀመሩን የሚያነሱት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ዶክመንት ማኔጅመነት ሲስተም የሚባል ስርዓት በመጠቀም ያሉትን መረጃዎች ወደ ዲጂታል ለመቀየር እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ብቃት ባለው ስካነር ሥራው ይከናወናል። ይህ መሳሪያም የገቡለትን መረጃዎች በዘጠኝ አየነት መንገድ ማስቀመጥ እንደሚችልም ታውቋል። ይህ ስርዓት መረጃን ከማስቀመጥ ባለፈ መረጃቸውን እንዲያስተካክሉ ፍቃድ ለተሰጣቸውም መረጃን ለማስተካከል የሚያስችል አሠራርም አለው።
ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራውን ለማስጀመር የሚረዱ መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ ሥራቸው ተጠናቆ፣ ሠራተኞች በስልጠና ላይ እንደሚገኙ የኤጀንሲው ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here