በኮሮና ቫይረስ ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩ ተገለጸ

0
553

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ሳምንታዊ አማካይ የሞት መጠን በእጥፍ ጭማሪ እያሳየ መሆኑ ተገለጸ። የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ ወደ ህክምና ተቋማት የሚገቡ የህሙማን ቁጥርም የ2 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይተቷል።
ሳምንታዊ አማካይ የሞት መጠን ደግሞ ከ13 ወደ 36 አድጓል ያሉ ሲሆን በፅኑ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ የቫይረሱ ስረጭት እየጨመረ ቢሆንም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው ብለዋል።
በዚህም በአዲስ አበበ 59 በመቶ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች ደግሞ 20 በመቶ ብቻ የአፍና አፍንጫ ማስክ የሚጠቀሙ እንደሆነ ጠቅሰዋል። አሁን ቫይረሱ ያለበት ስርጭት 3ኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ የስርጭት ማዕበል የጀመረ መሆኑን ያመለክታል ያሉት ዶክተር ሊያ ህብረተሰቡ ቫይረሱ የሚያደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ከሌሎች ሀገሮች በመማር ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ከመጋቢት 4/2013 ጀምሮ እስካሁን 2 ሚሊየን 254 ሺሕ 270 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ወስደዋል ብለዋል።
ከ300 ሺሕ በላይ ሰዎች ደግሞ ሁለተኛ ዙር ክትባት መውሰዳቸውን ሚኒስትሯ ቀሪውን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እይተሰራ እንደሆነ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ቫይረሱ ካለው የስርጭት አሳሳቢነት በመነሳት ከዚህ ቀደም የኮሮና ቫይረስ ክትባት ያልወሰዱ እድሜያቸው ከ35 አመት በላይ የሆኑ ፣በሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ደግሞ እድሜያቸው ከ55 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች ክትባቱ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ሰዎች በስራቸው ምክንያት ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም ይሰጣል ብለዋል። ክትባቱም በአዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ በሁሉም ክልሎች ደግሞ ከነሀሴ 14 ጀምሮ እንደሚሰጥ ገጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here