በ2 ቢሊዮን ብር የሚሰሩት ማረሚያ ቤቶች ግንባታ ተጓቷል

0
372

በኢትዮጵያ ከኹለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነቡ ያሉ ማረሚያ ቤቶች መጠናቀቅ ከሚገባቸው ጊዜ በሦስት ዓመት እንደተጓተቱበት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ገለጸ።

በፌደራል ደረጃ በአዲስ አበባ፣ ደሬድዋ፣ ዝዋይና ሸዋሮቢት እየተገነቡ የሚገኙት ማረሚያ ቤቶቹ በ2003 ግንባታቸው ሲጀመር በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ግንባታውን ማጠናቀቅ አልተቻለም። ከኹለት ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበላቸው አራት ማረሚያ ቤቶች 20 ሺህ የሚጠጋ ታራሚ የመያዝ አቅም እንዲኖራቸው ታስበው እንደተጀመሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

የማረሚያ ቤቶቹ ግንባታ ይጠናቀቃል ከተባለለት ጊዜ ሦስት ዓመታትን ዘግይቷል። ግንባታውን በበላይነት አየተቆጣጠረ የሚገኘው የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ግንባታውን በተለያዩ ምክንያቶች ማጠናቀቅ አለመቻሉን ገልጿል።

የማረሚያ ቤቱ የግንባታ ፕሮጀክት ኃላፊ እሸቱ አጥናፉ አሰሪው መስሪያ ቤት፣ ተቋራጮችና ቁጥጥር የሚያደርገው አካል አለመናበብ ለግንባታው መዘግየት ዋና ምክንያት እንደሆኑ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተለይም በግንባታው ላይ የተሳተፉ 60 ተቋራጮች ያጋጠማቸው የአቅም ማነስ ግንባታው ለመዘግየቱ ዋና ምክንያት ሲሆን በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ ሲያጋጥም የነበረው የበጀት ችግርና የንድፍ (ዲዛይን) ክለሳ ሌለው ምክንያት እንደሆነም እሸቱ አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው ማረሚያ ቤትም ከጎርፍ ጋር በተያያዘ ሥራውን ለማጠናቀቅ አዳጋች እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል። ሥራውን ለመጀመር ሲታሰብ በቅድሚያ በቂ ጥናት ልተደረገም ወይ? ለሚለው የአዲሰ ማለዳ ጥያቄ እሸቱ ‹‹ሥራዎች ሲከናወኑ ያለበቂ ጥናት አይጀመሩም ወደ ሥራ ከመገባቱም በፊት ብዙ ነገሮች ታይተዋል›› ብለዋል።

በተቋራጮች በኩልም በወቅቱ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መልምሎ ወደ ሥራ እንዳስገባቸው ኃላፈው ገልጸዋል። ሥራውን በአግባቡ በማያከናውኑ ተቋረጮች ላይም እርምጃ መወሰዱን አክዋል።

በተጨማሪም ግንባታው ዘመናዊ ከመሆኑ የተነሳ ሥራውን አወሳስቦታል የሚሉት እሸቱ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ከሚገኙት ማረሚያ ቤቶች በተሻለ ሁኔታ ለታራሚዎች አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ተደርገው እየተሰሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

የዘገዩትን የማረሚያ ቤቶች ግንባታ እስከመጪው ሰኔ 2011 መጨረሻ ድረስ ግንባታቸውን አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም እሸቱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አሁን ላይ የህንፃዎቹ ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን የቀሩት የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሥራዎችም እየተገባደዱ ነው ተብሏል።
በአዲስ መልክ እየተገነቡ የሚገኙት ማረሚያ ቤቶችም በውስጣቸው ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ምቹ ማረፊያ ክፍሎችንና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን ይይዛሉ ተብሏል።

ባለፈው ዓመት መጨረሻ የፌድራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በማረሚያ ቤቶች ባደረገው ምልከታ አብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች ለታራሚዎች ምቹ አለመሆናቸውን መግለጹ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here