የምርጫው ጉዳይ ከወዲሁ ይታሰብበት!

0
873

የዴሞክራሲ ስርዓት ከሚገለጽባቸው መርሖዎች አንዱ እና ዋነኛው ሕዝቡ በሚያምነው እና በሚቀበለው ወቅታዊ የምርጫ ሒደት ብዙኃን ይሁንታ የሚሰጧቸውን ወኪሎች መምረጥ ነው። በምርጫው አብላጫ ድምፅ ያገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች በዚሁ መሠረት ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ይመሠረቱና እስከ ቀጣዩ የምርጫ ጊዜ ድረስ የብዙኃንን አመራር እና የኅዳጣንን መብት በሚያስከብር መልኩ ያገለግላሉ። ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ መከናወኑ አስፈላጊ የሆነውን ያክል ምርጫው በነጻ እና ርትዓዊ በሆነ መንገድ መዘጋጀቱም በእኩል ደረጃ አስፈላጊ ነው።

በኢትዮጵያ እስካሁን አምስት አገር ዐቀፍ ምርጫዎች ወቅታቸውን ጠብቀው የተካሔዱ ቢሆንም፥ ሒደታቸውም ይሁን ውጤታቸው ሕዝባዊ ቅቡልነት ማግኘት አልቻለም ነበር። ስለሆነም ቅቡልነት በጎደለው ሒደት የተከናወኑት ምርጫዎች ላይ ተመርኩዞ ሲቋቋም የነበረው መንግሥት ራሱ ቅቡልነት በማጣቱ ከፍተኛ ተቃውሞን ሲያስተናግድ ቆይቶ ዛሬ ላይ ደርሷል። አሁን ምንም እንኳን ካለፉት ዐሥርት ዓመታት አንፃር የፖለቲካ ምኅዳሩ ቢከፈትም በገዢው ቡድን እና በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የዝግጁነት ሰፊ ልዩነት ይስተዋላል። ከዚህም በላይ ለቅድመ ምርጫ ሒደት ወሳኝ የሆኑት ብዙኃን መገናኛዎች እና ሲቪል ማኅበራት ዝግጅት እጅግ አነስተኛ ነው። ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ ለማካሔድ የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ልኂቃን ፈቃደኝነት ቢኖርም እንኳን፥ ሌሎች መንግሥታዊ የሆኑ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ዝግጁነት ግን አጠያያቂ በመሆኑ አሁንም ቢሆን የጫወታ ሜዳው ርትዓዊ ነው ለማለት ይቸግራል።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ካሳለፈችው የሕዝባዊ አመፅ ሙሉ ለሙሉ አልተላቀቀችም። አሁንም ሰላም እና መረጋጋት ሙሉ ለሙሉ አልሰፈነም፣ የሕግ እና ፍትሕ ማሻሻያ ሥራዎች አልተጠናቀቁም፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን መልሶ ማዋቀሩ ገና በቅጡ አልተጀመረም፣ የፀጥታ አካላትን እና ሌሎችንም ነጻ እና ገለልተኛ የማድረግ እንዲሁም በመንግሥት እና ገዢው ፓርቲ በኩል ያለውን መቀላቀል የመለየት በቂ ሥራ አልተሠራም፣ ከስደት የተመለሱ እና የምኅዳሩን መከፈት ተከትሎ እየተመሠረቱ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫ ቦርድ እስካሁን አልተመዘገቡም፣… ሆኖም ለምርጫው የቀሩት 15 ወራት ብቻ ናቸው።

እነዚህን ስንክሳሮች በመጥቀስ “ምርጫው መራዘም አለበት” የሚሉ ድምፆች እየተደመጡ ነው። እርግጥ ነው ምርጫዎች መካሔድ ያለባቸው ወቅታቸው ስለደረሰ ብቻ ሳይሆን ሕዝቦች በበቂ መረጃ ላይ ተመሥርተው ይወክለኛል የሚሉትን ዕጩ ያለ ፍርሐት እና መጭበርበር መምረጥ እንዲችሉ ለማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ምርጫውን ለማራዘም የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊም ይሁን ሕጋዊ መንገድ አልተቀመጠም።

አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ በወቅቱ ሳይካሔድ ሊያልፍ የሚችለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተጣለ ብቻ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣል ደግሞ የሕዝቡን በርካታ መብቶች የሚገፍ እንደመሆኑ አግባብ አይሆንም ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ጋዜጣችን ከፖለቲከኞችና የሕገ መንግሥት አዋቂ ምሁራን ጋር ባደረገችው ቆይታ ኹለቱም (“ምርጫው ይራዘም’ ወይም “በወቅቱ ይካሔድ”) የሚሉት ወገኖች በቂ መከራከሪያዎች እንዳሏቸው ተረድታለች። ምርጫውን በወቅቱ ማካሔድም ይሁን ማራዘም የየራሳቸው የሆኑ አስቸጋሪ ውጤቶች ሊኖራቸው እንደሚችል አዲስ ማለዳ ተረድታለች። ይሁንና በመንግሥት በኩል ይህንን ከግንዛቤ ያስገባ ልዩ ትኩረት ለጉዳዩ የተሰጠ አይመስልም። አዲስ ማለዳ የ2012ቱ ምርጫ ጉዳይ ከወዲሁ ካልታሰበበት ‘ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ’ እንደሚባለው ሆኖ የሕዝቡን እና የአገሪቱን ሁለንተናዊ ደኅንነት እና ኅልውና አደጋ ውስጥ የሚጥል መዝረክረክ እንዳይደርስ ማሳሰብ ትፈልጋለች።

ምርጫው በተያዘለት ጊዜ የሚካሔድ ከሆነ፦

(ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈን በተጨማሪ) የፖለቲካ ምኅዳሩን በማጥበብ ሲወቀሱ የነበሩት አዋጆች እና ሕግጋት ሁሉ ተከልሰው መቼ ነው የሚያልቁት? የዴሞክራሲ ተቋማት በነጻነት እና በገለልተኝነት መልሰው በመዋቀር ሕዝባዊ አመኔታቸውን ገንብተው ውድድሩን ማስተናገድ የሚጀምሩት መቼ ነው? ሁሉም የመንግሥት ተቋማት በተለይም ደግሞ የፀጥታ አካላት ከገዢው ፓርቲ ጋር ያላቸው መቀላቀል ተለይቶ ወገንተኝነታቸው ለሕገ መንግሥት እና ለሕዝብ ብቻ የሚሆኑት መቼ ነው? እነዚህ ጥያቄዎች ፈጣን መልስ ማግኘት ካልቻሉ፥ የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልስ ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ ለማካሔድ ይረፍዳል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ምርጫው የሚራዘም ከሆነ፦

የሽግግር መንግሥት ይመሠረታል ወይስ ያለው ምክር ቤት በሕግ አውጪነት ይቀጥላል? ወትሮም ሞራላዊ ቅቡልነት ያልነበረው እና አሁን “የለውጥ ቡድን” በሚባሉት አመራሮች መምጣት ብቻ ጊዜያዊ ቅቡልነት ያገኘው መንግሥት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅቡልናውን ከየት ያገኛል? በተራዘመበት ጊዜስ ምን ምን ሥራዎች ይሠራሉ? እነዚህን ሥራዎች ሠርቶ ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ ይበቃል? ይህንንስ ማን እና እንዴት ነው የሚወስነው? እነዚህ ጥያቄዎችን መመለስ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ቢካሔድስ የሚለው ጥያቄ ከሚፈጥራቸው የሥራ ጫና ሥጋቶች የማይተናነሱ እንደሆኑ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ከሁሉም በላይ ከጉዳዩ አንገብጋቢነት እና ውስብስብነት አንፃር በቂ ትኩረት ተሰጥቶት ውይይት እየተደረገበት እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ተረድታለች። ስለሆነም አስቸኳይ ትኩረት ተሰጥቶ መላው ሕዝብ ከሥጋት የሚወጣበት እና ብዙኃኑን አሥማሚ መፍትሔ የሚዘረጋበት ፍኖተ ካርታ ባስቸኳይ እንዲተዋወቅ አዲስ ማለዳ ጥሪዋን ታቀርባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here