የጊዮን ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ከኃላፊነታቸው ተነሱ

0
897

በጊዮን ሆቴል ሕገ-ወጥ ግዢና አስተዳደራዊ በደሎች እንዲበራከቱ አድርገዋል በሚል በሰራተኞቹ ቅሬታ ሲነሳባቸው የቆየው የሆቴሉ ሥራ አስከያጅ ሙሉጌታ እሸቴ ከኃላፊነታችው መነሳታቸው ተነገረ።

ረቡዕ ጥር 15 የሆቴሉ ሰራተኞች ሆቴሉን በበላይነት ከሚያስተዳድሩት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚንስቴር የሥራ ኃላፊዎችና ከሌሎች የቦርድ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ከተደረገ በኃላ ሥራ አስኪያጁ ከኃላፈነታቸው መነሳታቸው ታውቃል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሆቴሉ ሰራተኞች ለአዲስ ማለዳ እደገለጹት በእለቱ በነበረው ስብሰባ አብዛኛው ሰራተኛ የተገኘ ሲሆን በሆቴሉ ውስጥ የተንሰራፋውን አስተዳደራዊ በደልና ሌሎች ችግሮች በማንሳት ለቦርድ አመራሮቹ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

በተለይም ሆቴሉ አሁን ላይ ‹‹ሥሙ ብቻ ነው የቀረው፣ ችግሮች ሲፈጠሩ የመንግሥት አካላት የት ነበራችሁ? ሆቴሉ በኪሳራ ላይ የሚገኝ በመሆኑ አፋጣኝ ምላሽ ልትሰጡን ይገባል፣ የሚልና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ለቦርዱ አባለት እንዳቀረቡ ሰራተኞቹ ነግረውናል። የቦርድ አባለቱም ችግሮችን ለመፍታት የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርጉና ችግር የፈጠሩ ኃላፊዎችም ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መግለጹንም ተናግረዋል።

የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅም ስብሰባው ከመደረጉ ከቀናት በፊት ‹‹ከሥራ አሰናብቱኝ›› የሚል ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የገለጹት ሰራተኞቹ ቦርዱ ጥያቄያቸውን ውድቅ እንዳደረገው አስታውሰዋል። በስብሰባው ዕለትም ቦርዱ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ እንደሚፈታ አስታውቆ ከስበስባው እንደወጡ ገልጸዋል። በማግሥቱም ሆቴሉን ቢጊዜያዊነት የሚመራ ተጠባበቂ ሥራ አስኪያጅ እንደተመደበ ማወቃቸውን የገለጹት ስራተኞቹ አሁን ላይ በሆቴሉ የሚገኙ ሰነዶች እየጠፉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
ሆቴሉ ሕጋዊ ጨረታን ባልጠበቀ መልኩ የተለያዩ ግዢዎችን መፈጸሙን በተደጋጋሚ የሚያነሱት ሰራተኞቹ አሁንም ቢሆን የሆቴሉ አስተዳደር ክፍል በአዲስ መዋቀር እንዳለበት ያምናሉ። ይህ እስካልሆነ ድረስ ግን ችግሩ ሊቀጥል እንደሚችልም ሰራተኞቹ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

‹‹ሆቴሉን ለማደስ በሚል ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ቢፈጸምም የታየ ለውጥ የለም›› የሚለው ስራተኞቹ ከዚህ ቀደም ሲያነሷቸው ከነበሩ ቅሬታዎች አንዱ ነው።

ሰራተኞቹ እንደሚሉት ከሆነ ቦርዱ ይሄን ገዳይ በሚመለከትም ተገቢው መጣራት ተደርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደሚሰጥ ተናግሯል።
ከምግብ ግብአቶች ጋር በተያያዘም አቅራቢ ድርጅቶች ምርታቸውን ለሆቴሉ የሚያቀርቡት ያለ ሕጋዊ ጨረታ ነው ሲሉም ሰራተኞቹ መውቀሳቸው ጣወሳል።

አዲስ ማለዳ ስለጊዮን ሆቴል የሰራተኞች ቅሬታ በጥር 4/2011 ኅትመቷ በሰራችው ዘገባ ሥራ አስኪያጁ ሙሉጌታ ሆቴሉን በሚመለከት አሁን ላይ ያጋጠመ ችግር እንደሌለና በተያዘው ዓመትም የተሻለ ገቢ እየተመዘገበ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል። ሰራተኞቹ አለ የሚሉት ሕገ ወጥ ግዥና የገንዘበ ብክነትመ ከእውነት ራቀ ስለመሆኑ ማስተባበላቸው አይዘነጋም።

በ1941 የተቋቋመው ጊዮን ሆቴል 397 ቃሚ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በመንግሥት የልማት ድርጅት ስር የሚተዳደር አገልገሎት ሰጪ ተቋም ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here