ፆታዊ ትንኮሳ

0
866

ብርሃኔ አሰበ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናት። ባለትዳር እና የአንድ ልጅ እናት ስትሆን፣ የምትተዳደረው ልብስ በማጠብ ነው። ባለቤቷ የቀን ሠራተኛ እንደሆነ ትናገራለች። ከምትሠራው ሥራ እንደ ልፋትዋ መጠን እንደማታገኝ ታስረዳለች። ሆኖም ግን ገቢዋ ልብስ በማጠብ ብቻ የሚገኝ በመሆኑ ክፍያውን ለመቀበል ተገድጃለሁ ትላለች።
የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆንዋ የምታገኘው የገንዘብ መጠን ለኑሮ የሚያስፈልጋትን ለመሸፈን እንዳላስቻላት ትናገራለች። ብርሃኔ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ብዙ የሥራ ዕድል ባለመኖሩ በቂ ገቢ ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ታነሳለች። አሁን ያለው የኑሮ ውድነት ሌላ ሥራ ላለመሥራት አማራጭ እንዳልሰጣት ታስረዳለች።
ብርሃኔ የገቢ ምንጭ በማድረግ የወሰደችው የልብስ አጠባን ይሁን እንጂ፣ የተለያዩ ሥራዎችን ከተገኙ እንደምትሠራ ታነሳለች። ሆኖም ግን በሥራ ቦታዎች ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ግን መታገስ እንዳቃታት ጠቁማለች።
በሥራ ወቅት ከሚገጥሟት እንቅፋቶች መካከል ፆታዊ ትንኮሳን በዋነኛነት ትጠቅሳለች። አሠሪዎችዋ ወይም በምትሠራበት አከባቢ የሚገኙ ወንዶች ፆታዊ ትንኮሳዎች በተደጋጋሚ እንደሚያደርሱባት ትናገራለች።
ብርሃኔ የሥራ ፍላጎትና አቅሙ ቢኖራትም፣ በውድ በሚገኘው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳትሆን ፆታዊ ትንኮሳ ችግር ሆኖባታል።
ይህን አይነት ድርጊት ሴቶች ላይ በሚፈጽሙ ወንዶች ላይ የሚመለከተው አካል ተገቢውን እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም ትጠይቃለች።
ሌላዋ ሐሳቧን ያካፈለችን ተማሪ ዮርዳኖስ ትዕግስቱ ናት። የሲቪል ኢንጅነሪንግ ተማሪና የዘንድሮ ዓመት ተመራቂ ነች። በብዛት ጊዜዋን በማንበብና የተለያዩ ለትምህርቷ ሊረዷት የሚችሉ ተግባራትን ስታከናውን ቀኑን እንደምታሳልፍ ታነሳለች።
ዮርዳኖስ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በየዕለቱ በሚባል መልኩ ሴቶች በፆታቸው ምክንያት ትንኮሳዎች ሲደርሱባቸው ይስተዋላል ትላለች።
እሷም የፆታዊ ትንኮሳ ሰለባ እንደሆነች በማንሳት፣ ትንኮሳውን በሚያደርሱ ሰዎች ላይ ምንም አይነት ዕርምጃ ባለመወሰዱ ምክንያት ትንኮሳውን የሚያደርሱ ሰዎች ድርጊቱን በስፋት እያከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሳለች።
እንደ እሷ ገለጻ በትምህርት ቤት፣ በመጻሕፍት ማንበቢያ ቦታ፣ የመመገቢያ ስፍራዎች በይበልጥም በሕዝብ ትራንስፖርቶች ላይ ፆታዊ ትንኮሳ እንዳጋጠማት አንስታለች።
በሴቶች ላይ ፆታዊ ትንኮሳዎች ከሚፈጸምባቸው አውዶች ውስጥ የሥራ ቦታዎች፣ የትራንስፖርት አግልግሎት መስጫዎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ወዘተ. የሚጠቀሱ ናቸው።
ሴቶች ሥራ ለማግኘት፣ በተለያዩ መስኮች ላይ ዕድገት ለማግኘትና ያላቸውን አቅምና ችሎታ ለማውጣት፣ እንዲሁም የኪነጥበብ ሙያ ውስጥ ለመግባት በአንዳንድ ወንዶች ፆታን መሰረት ያደረገ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ይስተዋላል።
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታዊ ትንኮሳዎችን ለመግታት በሚመለከተው አካል ተገቢ ሥራ እየተሠራ ባለመሆኑ ትንኮሳዎች በሴቶች ላይ እየተባባሱ መሆኑን ዮርዳኖስ ትናገራለች።
ለፆታዊ ትንኮሳ አጋላጭ ተብለው የሚጠቀሱ ስፍራዎችን ማዘውተር ሴቶች መቀነስ ይኖርባቸዋል የምትለው ዮርዳኖስ፣ ይህ ካልሆነ ግን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ትላለች።
ሴቶች በማንኛውም ቦታ ፆታዊ ትንኮሳ በሚያጋጥማቸው ወቅት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የሕግ አካል በመቅረብ ትንኮሳ አድራሹ ሰው እንዲቀጣ ማድረግ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ቢነገርም ተፈጻሚ ሲደረግ አይታይም።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here