የታገቱት ሕንዳዊያን በፍርድ ቤት የሒሳብ እግድ ምክንያት ሊፈቱ አልቻሉም

0
699

አይ ኤል ኤፍ ኤስ እና ኤልሳሜክስ በተሰኙ የሕንድና ስፔን መንገድ ተቋራጮች ኪሳራ ምክንያት የድርጅቱ ሠራተኞች የደመወዝ ይከፈለን ጥያቄ ባለመመለሱ አራት ሕንዳዊያን ከኅዳር 2011 ጀምሮ በቡሬ ካምፕ እንደታገቱ ናቸው። የሠራተኞቹ ደመወዝ እንዲከፈልና የታገቱት እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ ተደርሶ የነበረ ቢሆንም የድርጅቱ ሒሳብ በባንክ በመታገዱ ሠራተኞቹ ሊፈቱ አልቻሉም። በሌላ በኩል ቁጥራቸው 207 የሚደርሱ የድርጅቱ ሠራተኞች እስካሁን ድረስ ደመወዝ ሳይከፈላቸው በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የድርጅቱ ሠራተኞች የታገቱትን ሕንዳውያን ለመልቀቅ በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ 377/96 መሠረት የ10 ወር ደመወዝ እና የስንብት ክፍያ ጠይቀው ነበረ ቢሆንም ከኹለቱም ወገን በኩል በተደረገ ድርድር ክፍያው ወደ አራት ወር ደመወዝ ዝቅ እንዲል ተስማምተውም ነበር። በዚህም የተባለው ገንዘብ ሲደርሳቸው የታገቱትን ሕንዳውያን እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ መደረሱም ታውቋል።

ይሁንና ታኅሣስሥ 30 በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተሰጠ የእግድ ትዕዛዝ ተቋራጩ በሥሩ ከያዛቸው ንዑስ ተቋራጮች ጋር ባለበት የፍረድ ቤት ክርክር ምክንያት በድርጅቱ የባንክ ሒሳብ ውስጥ የሚገኘውን ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ትእዛዝ አስተላልፏል። የታገደው የድርጅቱ ገንዘብም ስድስት ሚሊዮን አርባ ሦስት ሺሕ አራት መቶ ሰባት ብር መሆኑም አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ አረጋግጣለች። ድርጅቱ ከ207ቱ ሠራተኞች የደመወዝ ይከፈለን ጥያቄ በተጨማሪ በተለያዩ ጉዳዮች በአራት ክሶች ተመስርተውበት ይገኛል።

ፍርድ ቤቱ የድርጅቱን ሒሳብ በማገዱ ምክንያት ሠራተኞች ደመወዛቸው ሊከፈላቸው፣ የታገቱትም ሊለቀቁ አልቻለም።
አዲስ ማለዳም ሠራተኞቹ ስላሉበት ሁኔታ ለማወቅ ባደረገችው ጥረት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የሠራተኞቹ ተወካይ ‹‹በአሁኑ ወቅት ሠራተኞቹ ያሉበት ሁኔታ እጅግ በጣም አሳሳቢ መሆኑንና ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን›› ገልጸዋል። ከራሳቸውም በላይ ቤተሰቦቻቸው ችግር ውስጥ እንደገቡና አማራጭ ከማጣት የተነሳ፣ ከማሽን ኦፕሬተርነት ወርደው የቀን ሥራ እየሰሩ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እየተገደዱ ያሉ ሠራተኞች እንዳሉም ምንጫችን አስረድተዋል።

በፍርድ ቤት ክስ መስርተው እግዱን ለማስነሳት በሒደት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ሠራተኞቹ፣ በደመውዘ ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ የገባውን የ207 ሠራተኞችና የቤተሰቦቻቸውን ጥያቄ ለማስመለስ እንደሚጥሩ አክለዋል።

ተወካዩ አክለውም ታግተው የሚገኙት አራት ሕንዳውያን ‹‹በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን፣ የሚያሰፈልጋቸውን እያቀረቡላቸው እንደሆነ እንዲሁም የማገት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑንና ደመወዛቸው እንደተከፈላቸው በአስቸኳይ እንደሚለቋቸው›› ገልጸዋል፤ መንግሥትም በአፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድላቸው ጠይቀዋል።
ያጋጠመው ነገር አሳዛኝ ክስተት ስለመሆኑ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሳምሶን ወንድሙ ባለሥልጣኑ በጉዳዩ ላይ የባለቤትነት ድርሻ ባይኖረውም ከሰብኣዊነት እና በአገሪቱ ላይ ከሚፈጥረው ገጽታ አኳያ ጉዳዩ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

የሕንዱ ኢግዚም ባንክ ጥር 3/2011 ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጻፈው ደብዳቤ ባንኩ በአፋጣኝ ክፍያዎችን እንዲፈፅም እና የታገቱት ሠራተኞች እንዲፈቱ ጠይቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here