ሮቤል አለሙ ከበደ ይባላል። የተወለደው በጎጃም ከተማ ሲሆን በዚህ ወቅት አዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ የጎዳና ሕይወትን እየመራ ይገኛል። ሮቤል አሁን የአስራኹለት አመት ልጅ ነው። ከአባቱ ጋር የተለያዩት በስምንት አመቱ ነው። ከእናትና ከአባቱ ጋር በነበረበት በስድስት አመት ውስጥ የወረሰው ነገር በመግባባት ፈንታ መነቃቀፍን፣ በመከባበር ፈንታ መናናቅን፣ በመፈቃቀር ፈንታ መደባደብን ነው። ሮቤል እናትና አባቱ ሲጨቃጨቁና ሲነታረኩ፣ ከዚያም አልፈው አባቱ እናቱን ሲመታቱ ሲመለከት ኖሯል። ነገር ግን ያለው አቅም እናቱ ስታለቅስ እርሱም ተመሳሳይ ድርጊት መተግበር ነበር።
በዚህም ለአባቱ ያለው ፍቅር እየቀነሰ መምጣቱ አልቀረም። በእንደዚህ ኹኔታ ወራቶች ዓመታትን እየተኩ ሮቤልም ዕድሜው እየጨመረ መጣ። ብዙውን ጊዜ ከቤት ለመዋል ፍላጎት አልነበረውም፣ እፎይታ የሚሰማው ከጓደኞቹ ጋር በሚያሳልፈው የዕቃቃ ጨዋታ ቢሆንም፣ በጨዋታው ውስጥ ሆኖም አእምሮው ቤተሰቦችህ ለምንድን ነው የሚጣሉት? የሚል ጥያቄ ያነሾካሹክለታል።
ከጓደኞቹ ጋር ከሚያሳልፈው የጨዋታ መልስ ወደ ቤት ሲገባ የሚጠብቀዉ የተለመደው ጭቅጨቅ ቤት ከመግባቱ ቀድሞ በአእምሮው ያቃጭልበታል። ከዕለታት በአንደኛው ቀን ከተለመደው በተለየ መልኩ አባቱ እናቱን ሲደበድባት ተመለከተ፤ ምርር ብሎም አለቀሰ።
ከአባቱ ጋር የተለያየው ያኔ ሲሆን፣ እናቱ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ይዛው መጣች። አሁን አሁን ነገሮች ከተለመደው ችግር እየባሱ መጥተዋል። አናቱ በእንጀራ ጋጋሪነት ተቀጥራ መሥራት ብትጀምርም ውለው የሚያድሩበት ደሳሳ ጎጆ አልነበራቸውም። ኬንዳ ከልለው መንገድ ዳር መዋል ማደራቸው እየተለመደ መጥቷል። የወር ደሞዝ እስከሚደርስ የዕለት ጉርሻ ያገኙ ዘንድ ያላቸው አማራጭ በጎዳና እየተዘዋወሩ መለመን ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ የሚገኙ ሲሆን፣ ሮቤል ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ የጎዳና ሕይወትንና ክረምቱን እንዲህ ይገልጸዋል፤ ’’የምንኖረው ኬንዳ ከልለን ሲሆን፣ መሠረታዊ ፍላጎታችንን የምናሟላውም በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በምሰበስበው ድቃቂ ሳንቲም ነው’’ ይላል።
’’ካገኘን በልተን ካጣንም ጸሎት አድርገን መኖር ለኛ የሕይወታችን መገለጫ ነው። የሰው ፊት እንደሚያቃጥል በዐይን የማይታይ ነበልባል ነው። የዕለት ምግባችንን ለመስጠት የሚራሩ ብዙ ስዎች ቢኖሩም አስር ሳንቲም ላለመጣል ተሳድበው የሚያልፉም አይጠፉም። የእኛ መኝታ የባለጸጋዎችን መጸዳጃ ቤት ያክል ጽዳት የለውም። የምናድረው ላስቲክ ለብሰን ሲሆን፣ መኝታችን ደገሞ የተሰራንበት አፈር ነው።
የቤታችን ግርግዳ ጣሪያ ኬንዳ ሲሆን፣ አሁን ክረምቱን አስመልክቶ የቤታችን ጣሪያ ዝናብ ፤ ግርግዳው ነፋስ፤ ልብሳችን ብርድ፤ ፍራሻችን ጭቃ የሚሆንበት ጊዜ ነው። ዓመት ጠብቀን የምናከብረውን አጥነት የሚበሳውን የክረምት ዓመታዊ በአላችንን እያከበርን እንገኛለን።’’
“ብርዱ ቆዳ ይሸበሽባል፤ ዝናቡ ያበስብሳል፤ ውርጩ አጥንትን ይሰብራል፤ ደግሞ በክረምት ርሃቡም ይጨምራል፤ እንዲህም ሆኖ ግን እኔና እናቴ የርሃብን አሰቃቂነት ሰለምናውቅ ከለመነው ከፍለን ለምነው ላላገኙት ካልሰጠን እርሃባችን እርካታ አያገኝም’’ በማለት ይናገራል።
የሰው ልጅ በፍላጎቱ ልክ ይኖር ዘንድ ከታሰበ ተዘርዝረው የማያልቁ እልፍ አእላፍ ቁሳቁሶች ያስፈልጉታል። ሰው በመዳፉ ከጨበጠው የሚገለገልበት ቁስ በዘለለ ይኖረው ዘንድ በአእምሮው ውስጥ የሚርመሰመሰው ቁሳቁስ ተቆጥሮ አያልቅም ብሎ ለመናገር የእያንዳንዱ ሰው አእምሮ ምስክር ነው።
የሆነው ሆነና ለመኖር ቢያንስ ሦስት ነገሮች ያስፈልጋሉ። እነዚህም ምግብ ፡ መጠለያና ልብስ ናቸው። አንድ ሰው እነዚህ ሦስቱ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ከተሟሉለት መኖርን ባይኖር እንኳን አለመኖርን መኖር ይችላል።
በምንኖርባት ዓለም ኹለት አይነት ሰዎች ይገኛሉ። የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዙት ለመብላት የሚኖሩ ሰዎች ሲሆኑ፣ በኹለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት ደግሞ ለመኖር የሚበሉት ሰዎች ናቸው። ለመብላት መኖር የቅንጦት ሲሆን፣ ለመኖር መብላት ደግሞ የሕይወት ግዳጅ መሆኑን ባለጸጎችንና ከእጅ ወደ አፍ የሚኖሩ ሰዎችን ሕይወት መመልከት ይቻላል። ለቅንጦት የሚያስፈልጉትን ቁሶች ለማግኘት በሚደከመው ድካምና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማግኘት በሚደረገው ድካም መካከል ሰፊ ልዩነት የመኖሩን ጉዳይ ቆም ብሎ ለሚያስሰተውል ባለ አእምሮ ሰው እውነታው የተቀበረ አይደለም።
በቅንጦት ለመኖር የሚያስፈልጉ ቁሶችን መኖርን ለሚኖሩባቸው ሰዎች እንተዋቸውና ’’መሠረታዊ ፍላጎቶቻችን እንደሰማይ ርቀውብናል’’ በማለት የሚናገሩ አሉ። የጎዳና ኑሮን ቤታቸው አድርገው የሚኖሩ ከአዛውንት ጀምሮ እስከ ጨቅላ ሕጻናትን የምናይበት ወቅት ላይ ለመድረሳችን በአገራችን ወስጥ የሚገኙ ቦታዎችን በተለይም ብዙ የሕዝብ ክምችት የሚገኝባት መዲናችንን አዲስ አበባ ከተማን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል።
በአገራችን በጠቅላላ 88ሺሕ 960 የሚደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚገኙ ይነገራል። ከእነዚህም መካከል 3000 የሚሆኑት መከታ በሆኗቸው የመንግሥትና የግል መርጃ ድርጆቶች ከጎዳና ሕይወት መገላግል የቻሉ ቢሆንም፣ 85ሺሕ 960 የሚሆኑት ቀሪዎቹ የጎዳና ሕይወትን በመምራት ላይ ያሉ ናቸው። በጎዳና ከሚኖሩትም ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠግተው የሚገኙ ናቸው።
በመዲናችን ውስጥ ሕፃናትን ጨምሮ 50ሺሕ ገደማ የጎዳና ተዳዳሪዎች መኖራቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ። የዕድሜ ጸጋን ከፈጣሪ ዘንድ የተቀበሉ አዛውንቶች፡ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የአካል ክፍል ጉድለት የገጠማቸው ሰዎች በጎዳና ሕይወታቸውን ሲገፉ መመልከት እየተለመደ መጥቷል።
የሆነው ሆነና ለዚች ምድር የቅርብ እንግዳ በመሆናቸው አትኩሮት የሚገባቸው ሕፃናትም የችግሩ ሰለባዎች ናቸው። መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት መንገድ ዳር ላስቲክ ዘርግተው በክረምት ፀሐዩ፡ በበጋው ዝናብና ቁሩ የሚፈራረቅባቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትን ድምፅ ጆሯችን ፡ ኑሯቸውን አይናችን እየተመለከተ ዘመናት ተሸኝተዋል።
በአገራችን ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርታቸውን የመከታተል ዕድል ያገኙ፡ ፍላጎታቸው በላይ በላዩ የሚሟላላቸው፡ ከሶፋ ሶፋ እየዘለሉ፡ መዝናኛ ጊዜ ተመድቦላቸው የጨቅላነት ዕድሜያቸው ያልባከነባቸው፣ በቤተሰብ እንክብካቤ ተንደላቀው የሚያድጉ ሕፃናት መኖራቸው ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተቃራኒው ደግሞ በመማር ፈንታ መንገድ ዳር ላስቲክ ዘርግረው የሚውሉ፣ የፈለጉትን በነጻነት የማግኘት ዕድላቸው ከስሞ በጨቅላነት ዕድሜያቸው አስቤዛ የማብቃቀት ኃላፊነትን የተሸከሙ፣ በመቦረቅ ፈንታ በየመነኻሪያው፣ በቤተ እምነቶች እንዲሁም በተለያዩ ካፌና ሬስቶራንቶች በመዘዋወር መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለመሙላት ለጥቂት ሳንቲም የሚባዝኑ ሕፃናትም አልጠፉም።
በሰው ልጅ ሕይወት የሚጋረጡ ውጣ ውረዶች የራሳቸው የሆነ ምክንያትና ቀመርን ያነገቡ ናቸው። በመሆኑም ሰዎችን ለጎዳና ኑሮ የሚዳርጉ ተፈጥሮ የቀመራቸውና የሰው ልጅ በራሱ ጊዜ የሚፈጥራቸው የተለያዩ ምክንቶች ለመኖራቸውም ለችግሩ ሰለባ የሆኑ የጎዳና ላይ ነዋሪዎች አይነተኛ ምስክሮች ናቸው፡።
ሕፃናት ምድራዊ ኑሯቸውን በጎዳና እንዲያሳልፉ ከሚዳርጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ሞት እና ድርቅ በተፈጥሮ ቀመር ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን፣ የቤተሰብ አለመስማማት፣ ጦርነት፣ አስገድዶ መድፈር ደግሞ ከሰው ሰራሽ ክስተቶች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው።
ከላይ ከተዘረዘሩት ለጎዳና ኑሮ በር ከፋች ከሆኑት ምክንቶች መካከል በቤተሰብ አለመስማማት ምክንያት ለጎዳና ህይወት መዳረጉን ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ታሪኩን ያካፈለው ልጅም በአብነት ተጠቃሽ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ከጎዳና ሻወር አስተባባሪዎች ከአቶ ኤርሚያስ ዝና እና ከአስመሮም ተፈራ ጋር ቆይታ አድርጋለች። ኤርሚያስ ዝና በተለይ በክረምት ወራት ጎዳና ተዳዳሪዎች ከባድ እንግልት እንደሚደርስባቸው በመግለጽ፣ በዚህ ወቅት 32 ሕፃናትን ከጎዳና ላይ በማንሳትና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የማደረግ የበጎ አድራጎት ሥራ እየሠሩ ቢሆንም፣ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ አሁንም ቢሆን ጎዳና ላይ ዝናብና ፀሐይ የሚፈራረቅባቸው ሕፃናት በከተማው ውስጥ እንደሚገኙ ነው የገለጸው።
ለእነዚህ ሕፃናት ለጎዳና ሕይወት መዳረግ የወላጆች የጤና ችግርና ሞት፤ የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ ለቤት ኪራይ የሚሆን የብር ዕጥረት ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል። እነኤርሚያስ በሚያደርጉት ትብብር ከእነዚህ ሕፃናት በተጨማሪ 270 ጧሪ የሌላቸው አዛውንቶችም በየዕለቱ እየመጡ እየተመገቡ የሚመለሱ መሆኑንም ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
ተመግበው የሚመለሱበት ምክንያት የቦታ ጥበት ስለተጋረጠብን ነው ያሉት አስመሮምና ኤርሚያስ፣ ከእነዚህ ተመላላሽ ተመጋቢዎች መካከል ከሰባት አመት በላይ በጎዳና ላይ በላስቲክ ተጠልለው ላስቲክ ለብሰው የኖሩ ጧሪ የሌላቸው እናቶች እንደሚደገኙም ነው የገለጹት።
ለዜጎች ለጎዳና ሕይወት መዳረግ ብዙ ምክንያቶች ሲኖሩ፣ ለአዛዉንት እናትና አባቶች ዋነኛ ምክንያታቸው አካለ ጎደሎ ሆኖ መፈጠርና በአንድም በሌላም ጧሪ ልጅ ማጣት ነው። ለሕፃናት የጎዳና ላይ መውደቅ ትልቁ ምክንያት ደግሞ የሴት ልጅ ተገዶ መደፈርና በሞት ምክንያት እናቶችን ማጣት ዋነኛ ችግር መሆኑን ኤርሚያስና አስመሮም ከሚያስተዳድሯቸው ጎዳና ላይ ከነበሩ ዜጎች ታሪክ መረዳት መቻላቸውን ነው የገለጹት።
አክለውም ጎዳና ላይ በማንሳት እርዳታ ከሚያደርጉላቸው ዜጎች መካከል በ14 አመቷ የተደፈረች እና በአሁኑ ወቅት የአንድ አመት ልጅ ይዛ የምትገኝ ልጅ እንዳለች በመግለጽ፣ አስገድዶ መድፈር ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ልጃገረዶችንና የሚወልዱትን ሕፃናትን ጨምሮ ለጎዳና ተዳዳሪነት የሚዳርግና ሊወገዝ የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።
አያይዘውም ጎዳና ላይ ያነሷቸውን ዜጎችን ያገኟቸው በመንገድ ላይ በመውደቅ ላስቲክ ለብሰው ሲሆን፣ ለቀሪዎቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ድጋፍ ለማድረግ ቢፈልጉም የቦታ ጥበት ችግር እንደሆነባቸውም ሳይናገሩ አላለፉም። አሁንም የክረምቱ ዝናብና ብርድ የሚፈራቅባቸውን መንገድ ላይ የወደቁ ዜጎችን መንግሥት ፊቱን አዙሮ መፍትሄ ሊቸራቸው እንደሚገባም ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።
ኤርሚያስና አስመሮም እስካሁን ለጎዳና ተዳዳሪዎች እያደረጉት ባለው በጎ አድራጎት ከግለሰቦችና ከግል ድርጅቶች ውጭ መንግሥት ምንም አይነት ድጋፍ እንዳላደረገላቸው በመግለጽ፣ ከዚህ በኋላም ቢሆን ቢያንስ ከችግሮቻችን መካከል የሚጠቀሰዉን የቦታ እጥረት ለመሸፈን ቢረዳን ሌሎች ብዙ ጎዳና ላይ የወደቁ ወገኖቻችንን ለመርዳት ዝግጁ ነን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013



