‹‹ከባንክ ውጭ ሰዎች ጋር የሚገኝ ብር መብዛቱ ኢኮኖሚው ላይ ምንም ተጽእኖ የለውም››

0
850

አብዱልመናን መሐመድ ይባላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቲፋይድ አካውንታንት፣ በፋይናንሻል ማኔጅመንት የማስተር ዲግሪ አላቸው። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ፋይናንሻል ሴክተር ፒኤችዲ እየሠሩ ሲሆን በቅርቡ ይጨርሳሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ የኤክስተርናል ኦዲት ኦዲተር ማናጀር፣ በእንግሊዝ አገር ለንደን በፕሮፐርቲ ድርጅት ውስጥ የአካውንት ማናጀር ናቸው።
በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ከ10 ዓመት በላይ ተሳትፎ እያደረጉ ሲሆን ‹ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው› መጽሔት፣ ‹ፎርቹን› እና ሲራራ ጋዜጦች ላይ በመጻፍ እንዲሁም በዶቼ ቬሌ፣ ቪኦኤና ቢቢሲ ላይ በመሳተፍ ይታወቃሉ።
ከአዲስ ማለዳዋ ሰላማዊት መንገሻ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው የዋጋ ንረት ከምን የመጣ ነው ብለው ያስባሉ?
ኢትዮጵያ ውስጥ የዋጋ ንረት በተለይም ደግሞ በፈረንጆች 2008 ላይ 64 በመቶ የደረሰበት ሁኔታ ነበር። በመቀጠል ደግሞ ከ2010 ጀምሮ ያለው ከ10 እስከ 20 ባለው ውስጥ እየተቀያየረ ቆይቶ ነበር። ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ 20 ቤት ውስጥ ቆይቶ በአሁኑ ሰዓት 26.5 ደርሷል።

ይህ ቁጥር ኢትዮጵያ በአለም ደረጃ በዋጋ ንረት ከፍ እንድትል ያደርጋታል። ለዚህ የዋጋ ንረት መከሰተ ዋነኛው ምክንያት የብሔራዊ ባንክ እና ከተለያዩ ባንኮች መንግስት የሚበደረው ነው። ከብሔራዊ ባንክ ብር መበደር ማለት ብር ማተም ማለት ነው። ይህን ደግሞ መንግሥት ያስተዋለው አይመስልም። መንግሥት በመሠረተ ልማትም ሆነ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በመክፈት ኢኮኖሚ ውስጥ ተሳታፊ ሲሆን ገንዘብ በሚያጥረው ሰዓት ያለምንም ገደብ እንዲበደር በር ይከፍትለታል። ስለዚህ ገደብ የሌለው የገንዘብ መበደር የዋጋ ንረት ከሚያስከትሉ ጉዳዮች ዋነኛው ነው። ኹለተኛው የዋጋ ንረት የተከሰተው የምርት በቂ አለመሆን ነው። የህዝብ ቁጥር 110 ሚሊየን ሆኖ ሲጨምር የግብርና ምርቶች እና የኢንዱስትሪ ምርቶች አልጨመሩም። የመንግስት ብድር እና በቂ አቅርቦት አለመኖር ከ10 ዓመት በላይ ሲነሱ የነበሩ ችግሮች ናቸው።

የምርት ውጤት ሳይኖር የመሰረተ ልማት መስፋፋት ላይ ትኩረት መደረግ የለበትም። የዩኒቨርስቲዎች፣ የፋብሪካዎች እና የመንገድ መሰረተ ልማት ከማሳለጥ ባለፈ ለህዝቡ የሚጠቅም ፍጆታዎቻችን እንደ ዘይትና ዳቦ በበቂ ሁኔታ እያመረትን አይደለም። የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፤ ይህ ሕዝብ ወደ ገበያ ሲወጣ ተመጣጣኝ የሆነ የምርት አቅርቦት ስለማይገኝ ምርት ዋጋ ይጨምራል። ይህ ደግሞ የግብርና ምርት አለመጨመር ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ሕብረተሰቡን መጥቀም የሚችል ምርት እየተመረተ ስላልሆነ ነው።
በቅርቡ ደግሞ አገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት ተፈጥሯል። ይህ ደግሞ በተፈለገው መጠን ገበሬው እንዳያመርት ያደርጋል። ቢያመርት እንኳን የትራንስፖርት አገልግሎት አይገኝም። የትራንስፖርት ችግር ከተፈጠረ ምርት ላይ ዋጋ ይጨምራል።

ይህ እያለ የገንዘብ የመግዛት አቅም ማነስ መጣ። መንግስት ኢኮኖሚውን ያስካከለ መስሎት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አስተዳደር እና አሰራራቸውን በማሻሻል ከዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ፈንድ ተቋማት እንዲበደሩ እያደረገ የብርን የመግዛት አቅም እያዳከመ ነው። ከ2020 ጀምሮ የብር የመግዛት አቅሙ በ20 በመቶ እየተዳከመ መጥቷል። ይህ ደግሞ ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን በቀጥታ የሚጎዳ ነው። ለምሳሌ ነዳጅን ማየት እንችላለን፡ ነዳጅ ከውጭ ስናስገባ በ20በመቶ ከፍ አለ ማለት ከባድ ነው። መድሃኒቶች እና መሰረታዊ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ እቃዎች ላይ በተመሳሳይ ጭማሪ ያሳያል። ኢትዮጵያ 80 በመቶ የምናስመጣቸው እቃዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው። እነዚህ የውስጥ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ጦርነቶች ሲመጡ ደግሞ የዋጋ ንረቱን ያጋንኑታል።

መንግስት የኢኮኖሚ አሻጥር ነው የሚለውን ሀሳብ እንዴት ይገልጹታል?
ኢኮኖሚ ላይ ችግር ካለ ለአሻጥር ይመቻል። ባለፈው ሳምንት የትይዩ ገበያ ላይ የነበረው የዶላር ልውውጥ ከ60 ወደ 70 ብር ደርሶ ነበር። ይህ የሚያሳየው ኢኮኖሚያችን እንደተጎዳ መሆኑን ነው። እንደዚህ አይነት የምንዛሬ መጠን በጥቂት ቀናት ውስጥ ሊጨምር የሚችለው የሆነ ሰው ወይንም የተደራጀ ሀይል ያላቸው ተነሳሽነት ምን እንደሆነ ባልታወቀበት ሁኔታ በጣም በርካታ ዶላሮችን በፈለገው ዋጋ አምጡልን ብለዋል ማለት ነው። እነዚህ ያዘዙት የገንዘብ መጠን ደግሞ በጣም ጫና የሚፈጥር ስለሆነ ነው። በጣም ትልቅ የዶላር መጠን ጠይቀው እንዲያመጡላቸው ካስደረጉ በፈለጉት ያህል እንደሚወስዱላቸው ድርድር አድርገዋል ማለት ነው። ይህን የሚያደርጉት ለምን አላማ እንደሆነ የሚያውቁት አድራጊዎቹ ናቸው። ነገር ግን ትልቅ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲፈጠር ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል። ይህን መንግስት አንድ ቀን ይደርስበት ይሆናል። በጣም የኢኮኖሚ መዳከም ስላለ በጣም በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ውስጥ መውደቅ ይችላል። እንዴት እነዚህ ጥቂት ሰዎች ተቆጣጠሩት የሚለውን ጥያቄ መንግስት መጠየቅ አለበት። አሻጥር ሁልጊዜም መኖሩ አይቀርም። ነጋዴውም ላይ አሻጥር ይሰራበታል።
ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው መቶ በመቶ ባንኮች ብድር እንዲያቆሙ የተደረገው ለምንድን ነው?

ብድር በታሪክ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ማቆም አለበት የሚያስብል ደረጃ የደረስነው ምን ያህል ደካማ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ እንዳለን የሚያሳይ ነው።
ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን አታበድሩ ያለው ያለፈው ሀሙስ ቀን ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሬ በጣም የጨመረው መመሪያው ከመውጣቱ ሳምንታት በፊት ነው። ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን እስከማገድ ደረጃ እርምጃዎችን ሲወስድ የጥቁር ገበያው ግብይቱ ወደ 60 እየወረደ ነበር። ይህ በብሔራዊ ባንክ አረዳድ ካፒታል ፍላይት ይባላል። አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በሙሉ ማወጣት የሚችሉበት እድል አለ። ሳውዝ ኢስት ኤዥያ በ90ዎቹ እንደተከሰተው አካውንት ውስጥ ያለውቸውን ዶላር በአንድ ጊዜ ሲያወጡ ባዶ ይቀራል። ብሔራዊ ባንክም እነዚህ ገንዘብ የሚያወጡት የገንዘብ ምንጫቸው ብድር ነው ብሎ በማሰብ ብድሮች ከቆሙ ገንዘብ ወስደው አያሸሹም በሚል ነው ሕጉን ያወጣው። ይህን እርምጃ ሲወስዱ የጥቁር ገበያው መውረድ ጀምሯል፣ ብድር ደግሞ በረጅም ሂደት የሚሰጥ ስለሆነ መፍትሄ ብሎ የወሰደው ከድንጋጤ የመጣ ነው። መንግስት ተረጋግቶ የብድር መጠንን በመቀነስ፣ የተበደሩት ብድር ለተገለጸው አላማ መዋሉን በማረጋገጥ ለማረጋጋት መሞከር ይችል ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ካፒታል ፍላይት የማይታሰብ ነው። እንኳን ተበድረው ገንዘብ ሊያሸሹ ይቅርና የውጭ ድርጅቶች ኢትዮጵያ መጥተው አትርፈው በህጋዊ መንገድ ለሚደራጁት ብዙ ስቃይ ነው ያለው። ይህ የብሔራዊ ባንክ እርምጃ ስሜት የሚሰጥ አይደለም።

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የሚበደሩት ብድር ተሰርዞ ለሌላ በመንግሥት ለተቋቋመ ድርጅት ማስተላለፍ የሚባለው ትክክለኛ አካሄድ ነው ብለው ያስባሉ?
ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ገንዘብ ይበደራል የሚባለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ነው። እስከ አሁን የተበደረውም የሀገሪቱን አጠቃላይ የባንኮች የማበደር አቅም 30 በመቶ ያህል ጋር እኩል ነው ብዬ አስባለው። የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ሌሎች ተቋማት ብድር ያለባቸው ናቸው። ባንኮች የማበደር አቅማቸውንም በተመለከተ ለመንግስት እና ለግል ባንኮች የተለያየ ሕግ መኖር የለበትም። በዚህም የተነሳ እነዚህ የልማት ድርጅቶች የሚበደሩት ብድር ከንግድ ባንክ ስለሆነ ያለምንም ገደብ ይበደራሉ። ይህም የተጠራቀመ የብድር መጠን እንዲኖራው አድርጓል። ባንኮች ብድር ሲሰጡ ካፒታላቸውን መሰረት በማድረግ ገደብ አለባቸው። አንድ ተበዳሪ ከባንክ የሚወስደው ላይ ገደብ አለበት። መንግስት ደግሞ የተበደሩትን እዳ ዋስትና ወስዶ የሚያስተላልፉበት ተቋም አመቻቻለሁ ይላል። የልማት ድርጅቶች መክፈል የማይችሉትን ያህል ተበድረው መክፈል ሲያቅታቸው ለሌላ ጊዜ ከውጭ ሀገራት ለመበደር ጥቁር ነጥብ ይጥልባቸዋል። የውጭ ሀገራት የግል አበዳሪዎች ለማበደር ሲያስቡ የተቋሙን የቀድሞ የኦዲት ሪፖርት ያያል። በዚህ ጊዜ የተጠራቀመ ትልቅ ብድር ይኖራል። ይህን እያዩ ደግሞ አያበደሩም። ስለዚህ ይህ ችግር እንዳይፈጠር የሀብቶች እና እዳዎችን የሚቆጣጠር ተቋም (Asset and liability management company) መንግስት መሰርቷል። ከዚያም ያለባቸውን ብድር ወስዶ ባለዕዳ ይሆናል። ይህ ድርጅት ካበደራቸው ባንክ ጋር ግንኙነት ይፈጥራል። ይህ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም። ተበዳሪዎች ብድራቸው ከፍ በማለቱ ወደ ካፒታል ተቀየረላቸው ከተባለ ብድራቸውን የወሰደላቸው ተቋምስ ከየት አምጥቶ ሊከፍል ነው? ይህ ዕዳውን አለባብሶ በማለፍ ተበዳሪዎችን የሚጠቅም ቢሆንም አበዳሪው ባንክ ደግሞ ያበደረውን ማግኘት አለበት። ይህ አዲሱ ድርጅት የተለያየ ገቢ ይኖረዋል ተብሏል። ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮም ፕራይቬታይዝ ሲደረግ የገንዘብ ምንጭ ያገኛል። ድርጅቶቹ ከሚያገኙት ትርፍ ያካፍላሉ ተብሏል። ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አትራፊ ስለሆኑ ሊከፍሉ ይችላሉ። እንደነ ሜቴክ እና ስኳር ኮርፖሬሽን ያሉት ከየት አምጥተው ይከፍላሉ የሚለው ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋል። መጀመሪያ የተበደረው መንግስት ነው። ችግሩን እፈታለሁ ብሎ ዋስትና የሚሰጠው መንግስት ነው። ይህ ደግሞ ዘላቂ አይደለም ብዬ አስባለው።

ከውጭ የምንበደረው ብድር እየበዛ መምጣቱ በኢኮኖሚው ላይ ምን አይነት ጫና ይፈጥራል?
ብድር የምንብደረው ከሀገር ውስጥ ባንኮች፣ ብሄራዊ ባንክ እና ከውጭ ነው። የውጭ አበዳሪዎች ደግሞ በሁለት ይከፈላሉ። ከፍተኛ ወለድ ያላቸው እንዲሁም የሁለትዮሽና ሶስትዮሽ ናቸው። የሁለትዮሽና ሶስትዮሽ ብድሮች የረጅም ጊዜ ብድር ስለሆኑ ከባድ አይደለም። በጣም ከባድ የሚሆነው የከፍተኛ ወለድ ያላቸው ብድር ነው። ከዚህ ከፍተኛ ወለድ ያለው አንድ ቢሊየን ዶላር እንደ ሀገር ተበድረን የነበረ ሲሆን፣ አሁን የመክፈያ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሶስት አመታት ቀርተውታል። የኢትዮጵያ መንግስት አንድ ቢሊየን ዶላር መክፈል የሚችል አይመሰለኝም። ሊያውም ደግሞ በዚህ ጦርነት ወቅትና የገንዘባችን የመግዛት አቅም በደከመበት ወቅት ከባድ ነው። ብድር እየጨመረ ሲመጣ የወለድ መጠንም ያድጋል። ባለፈው ሚያዚያ የጂ20 ሀገራት ስብሰባ ላይ የጸደቀው በኮቪድ-19 ምክንያት ለተጎዱ ታዳጊ ሀገራት ፋታ እንዲሰጥ የተደረገበት ሁኔታ አለ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደግሞ መጎዳት የጀመረው ከኮቪድ ወረርሺኝ በፊት ነው። ኮቪድ እና ጦርነቱ ደግሞ አባብሶታል። ስለዚህ የተለያዩ ማስተካከያዎች በማድረግ የኢትዮጵያ ያለባትን እዳ መቀነስ ወይም መሰረዝ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
የአለማቀፍ የገንዘብ ፈንድ ባዋቀረው ኮሚቴ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲከታተል ተደርጓል። የአለም አቀፍ የግል አበዳሪዎች ጋር ያለንን ብድር መመለስ ሳንችል ይቀነስል ወይም ይሰረዝልን የምንል ከሆነ ለቀጣይ ጊዜ መበደር አንችልም። የግል አበዳሪዎች ያለንን ሪከርድ ስለሚያዩ በወቅቱ የመክፈል አቅም ከሌለን ወለድ ይጨምሩብናል ካልሆነ ላያበደሩ ይችላሉ። ይህንን አሰራሩን መንግስት መፈተሸ ይኖርበታል፡

ያለን ተቀማጭ የዶላር መጠን መቀነሱ የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ጫና ምን ይመስላል?
የአለማቀፍ የገንዘብ ፈንድ( IMF)2019 ላይ ካጸደቀው 2.9 ቢሊየን ዶላር ውስጥ የተወሰነ ብናገኝም ያለንን ተቀማጭ አያሻሽለውም። እንደ ሀገር ለተለያዩ አገልግሎት ልንጠቀምበት የምንፈልገው ገንዘብ አለ። ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የምንጠቀመው ዶላር በመሆኑ የተቀማጭ ዶላር መቀነስ ኢኮኖሚ ላይ ጫና ይፈጥራል። ባንኮችም ያላቸውን ተቀማጭ የገንዘብ መጠን እያሳደጉ እንደሚገኙም እየገለጹ ነው።ያለምንም ጥያቄ ደግሞ ያለንን ተቀማጭ ገንዘብ ለተፈጠረው ጦርነት እንድናውል ያደርገናል። በዚህ ጊዜ ተቀማጭ የገንዘብ መጠን ማነስ ለመሰረታዊ ፍጆታ ልንጠቀም የታሰበውን ያሳጣናል።

ከባንክ ውጭ ሰዎች ጋር የሚገኘው ገንዘብ መጠን መብዛት ለኑሮ ውድነት ምክንያት ነው ብለው ያስባሉ?
ገንዘብ ሰዎች ጋር በብዛት መኖሩ የኑሮ ውድነት ላይ ተጽእኖ የለውም። ሰዎች በብዛት ገንዘብ የሚይዙት ኢኮኖሚው ጥሬ ገንዘብ ስለሚፈልግ ነው። በየቦታው ግብይት የምንፈጽመው በካሽ ስለሆነ ብዙ ገንዘብ ይዞ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ ሀገራችን በቴክኖሎጂው አላደገችም። ኢኮኖሚው ጥሬገንዘብ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የቱንም ያህል የገንዘብ መጠን ባንኮች ጋር ቢኖር ተመልሶ መውጣቱ አይቀርም።

ባንኮች ሰው ያለውን ገንዘብ እንዳያወጣ ገደቦችን መጣል ሲጀምሩ ሰዎች ጋር ያለው የገንዘብ መጠን 109 ቢለየን ብር ደርሶ ነበር። አሁን ግን ወደ 130 ቢሊየን የሚደርስ ብር ከባንክ ውጭ ይገኛል። አንድ ሰው ካሽ በእጅህ መያዝ አትችልም ተብሎ ባንክ እንዲያስቀምጥ ሊገደድ አይገባም።

የገንዘቡ ምንጭ ህጋዊ ከሆነ እንዴት መጠቀም እንዳለበት የሚያውቀው ባለቤቱ ነው መሆን ያለበት። ባንኮች የተለያዩ ገደቦችን ጥለው ሰዎች ጋር የነበረውን የገንዘብ መጠን ቀንሰው የነበረ ቢሆንም አሁን ተመልሶ ወጥቶ ሰዎች እጅ ይገኛል። ለምንድነው ካልን ኢኮኖሚው ጥሬገንዘብ ግብይት ላይ የተመሰረተ ነው። ባንክ ረጅም መንገድ ተጉዞ በሚገኝበት ሀገር ላይ ብራችሁን ባንክ አስቀምጡ ማለት ለኔ ትክክል መስሎ አይታየኝም። የኑሮ ውድነት የሚያባብሰው ብር ሰዎች ጋር መኖር ሳይሆን የብድር መጠናችን ከፍ ማለቱ ነው።

የግሽበት መጠን 26 በመቶ እና ማበደሪያ 21 በመቶ ሆኖ የቁጠባ መጠን ደግሞ 7 በመቶ ነው። ይህ ማለት አንድ ሰው በመበደሩ ተጠቃሚው ሀገር ነው። ብሔራዊ ባንክ የቁጠባ የወለድ መጠን (Saving intereset rate) 15 በመቶ ቢያደርግ ቁጠባ ሊበረታታ ይችል ነበር። ነገር ግን ይህን ማድረግ የማይችለው የልማት ድርጅቶች የተበደሩት በ7 በመቶ የወለድ መጠን በመሆኑ ነው። የቁጠባ የወለድ መጠን ከጨመረ የእነዚህ ድርጅቶች የወለድ መጠን ስለሚጨምር ማሳደግ አይችልም።

መፍትሄው ምንድነው ይላሉ?
የትኛውን መፍትሄ እናስቀድም ከሚለው ስንነሳ ያለብንን ችግር ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። የኑሮ ውድነት፣ የስራ አጥ ቁጥር መብዛት፣ የብድር መጠን መብዛት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የንግድ ዘርፍ መተረማመስ ተፈጥሯል። መንግስት የቱን ማስቀደም እንደሚገባው ማወቅ አለበት። እንደኔ መንግስት ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው የኑሮ ውድነት ማረጋጋት ላይ መስራት አለበት። ወደ ውጭ የምንልካቸውን ምርቶች መጠን ማሳደግ አለብን። ሌላኛው የቁጠባ የወለድ መጠን ማሳደግ ነው። ሰዎች እቃ ገዝተው ከማትረፍ ባለፈ ገንዘብ ቆጥበው ወለዱን ትርፍ የመጠቀም አማራጮችን ይጠቀማሉ። አሁን ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የወለድ መጠን ውጭ ሀገራት በ90ዎቹ ይጠቀሙት ከነበረው ራሱ ያነሰ ነው። በወቅቱ የአለም አገራት 10.5 የወለድ መጠን ነበራቸው። ሰዎች ገንዘቤን ምን ላይ ላውለው የሚለውን ጭንቀታቸውን ይፈታል። የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ከግብርናና ከማኑፋክቸሪንግ ወደ ውጭ የምንልካቸውን ምርቶች መጠን ማሳደግ አለብን። መንግስት ያለበትን ድክመት መቀነስ አለበት።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here