ከ“ሕግ ማስከበር” ወደ “ሕዝባዊ ጦርነት”

0
1115

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በሕወሓት እና በፌደራል መንግሥት መካከል የተፈጠረው ልዩነት ጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቶ አሁን ላይ ክልሎችን ያጣቀሰ ችግር ሆኗል፡፡ በኹለቱ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ በመቀጠሉ አንዱ ሌላወን “ሕገ ወጥ” ከማለት አልፎ ጥቅምት 24/2013 ወደ ኃይል መማዘዝ ተቀይሯል፡፡
የኹለቱ ኃይሎች ልዩነት ወደ ጦርነት ማደጉን ተከትሎ በሽብርተንነት የተፈረጀው ህወሓት እና የፌደራል መንግሥት ለስምንት ወራት በትግራይ የተገደበ ጦርንት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጅ የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ዐውጆ ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ ችግሩ ወደ አጎራባች ክልሎች ሰፍቷል፡፡ በዚህም በአማራ እና በአፋር ክልል በህወሓት በኩል ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፣ የአማራ ክልል መንግሥት ጥቃቱን ለመከላከል ከ “ክተት አዋጅ” እስከ “ሕዝባዊ ጦርነት” ጥሪ አቅርቧል፡፡
የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ከህወሓት ጋር ለስምንት ወራት ያደረገው “የሕግ ማስከበር” ጦርነት፣ ባሳለፍነው ሳምንት የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር ባቀረቡት የ “ሕዝባዊ ጦርነት” ጥሪ፣ ወደ “ሕዝባዊ ጦርንት” የመቀየር አዝማሚያዎች እየታዩበት መጥቷል፡፡ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጉዳዩን የሕግ እና ወታደራዊ ባለሙያዎች አነጋግሮ የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ከመጋቢት 2010 ጀምሮ መንግሥታቸውን በአዲስ አደረጃጃት ማዋቅር መጀመራቸውን ተከትሎ በህወሓትና በፌደራል መንግሥት መካከል ልዩነት መፈጠሩ የሚታወስ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አሠራር ኢትዮጵያን በበላይነት ለ27 በመራው ህወሓት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ የመጣ ቅሬታ መፍጠሩን ተከትሎ፣ በፌደራል መንግሥት እና በወቅቱ የትግራይ ክልል መንግሥት በነበረው በህወሓት መካከል ልዩነቱ በግልጽ ጎልቶ አሁን ላይ ለተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ሆኗል።

ህወሓት እና የፌደራል መንግሥት በልዩነት ጎዳና ማቅናት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ልዩነታቸው ከቀን ወደ ቀን እያደገ በመምጣቱ በቃላት ጦርነት ተወስኖ የነበረው የኃይል ፍትጊያ ወደ ጥቅምት 24ቱ ጦር መማዘዝ ተሸጋግሯል። በኹለቱ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ከቃላት ጦርነት ወደ ጦር መማዘዝ ማምራቱን ተከትሎ፣ በየጊዜው የሚቀያየሩ ክስተቶች ታይተዋል።

በትግራይ ክልል በህወሓት ላይ ጥቅምት 24/2013 የተጀመረው ጦርነት ከ“ሕግ ማስከበር” ወደ “ሕዝባዊ ጦርነት” መሸጋገሩን በአማራ ክልል መንግሥት እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት በኩል በግለጽ ተነግሯል። በዚህም በ “ሕግ ማስከበር” የተጀመረ ጦርንት ወደ “ሕዝባዊ ጦርነት” መሽጋገሩን በአንድ በኩል እንደ ስጋት በሌላ በኩል ደግሞ እንደ መልካም ነገር እየታየ ነው።

በአማራ ክልል መንግሥት በኩል ክልሉ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር የሚያደርገው ጦርነት “ሕዝባዊ ጦርነት” እንዲሆን ባሳለፍነው ሳምንት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። ርዕሰ መስተዳደሩ ጦርነቱ “ሕዝባዊ” እንዲሆን ጥሪ ያቀረቡት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ጦርነቱን “ሕዝባዊ” ስላደረገው መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ትግራይን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ዳግመኛ ተባብሶ የቀጠለው ጦርነት “ሕዝባዊ” መሆኑን በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በተደጋጋሚ ለሚዲያዎች በሚሠጣቸው ማብራሪያዎች ሲገልጽ ተደምጧል።

በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ጥቅምት 24 የተጀመረው ጦርነት ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተገድቦ ከቆየ ብኋላ፣ የፌደራል መንግሥት ሰኔ 21/2013 የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ከ15 ቀን አፍታ በኋላ በአዲስ መልክ መቀስቀሱ የሚታወስ ነው።
የተኩስ አቁም ዐዋጅን ተከትሎ ትግራይ ያስተዳድር የነበረው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ከወጡ ከ15 ቀን በኋላ ህወሓት እራሱን አደራጅቶ በአማራ እና በአፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጥቃት መሰንዘሩን እና ጦርነቱ እንደ አዲስ ማገርሸቱ ይታወቃል።

በዚህም የአማራ ክልል መንግሥት ህወሓት በክልሉ አጎራባች አካባቢዎች ላይ ጥቃት መክፈቱን በማስታወቅ የክተት ዐዋጅ ጥሪ አድርጓል።
የክልሉ መንግሥት በህወሓት የተከፈተበትን ጥቃት ለመከላከል ባወጀው የክተት ዐዋጅ መሠረት ሌሎች የክልል መንግሥታት ጭምሮ ልዩ ኃይላቸውን ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል መላካቸው የሚታወስ ነው። የ“ሕዝባዊ ጦርነት” ጥሪ ያቀረቡት የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር፣ በወቅቱ በሠጡት መግለጫ ላይ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በአማራ ክልል በሶስት ግንባሮች ማለትም በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ እና ሰሜን ጎንደር ወረራ ፈጽሟል ብለዋል።

ህወሓት በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ በሴቶች ላይ የመድፈር ጥቃት፣ የግለሰብና የመንግሥት ንብረት ዝርፊያ እንዲሁም ወጣቶችን አፍኖ የመውሰድ ተግባራት መፈጸሙን ርዕሰ መሥተዳደሩ አረጋግጠዋል።
በአማራ እና በአፋር ክልል ህወሓት በፈጸማቸው ጥቃቶች ከሰዎች ሕይወት ማለፍ እስከ ንብረት ውድመት መድረሱ ቢገለጽም፣ አንዳንዶች ለችግሩ መከሠት የፌደራል መንግሥት ተጠያቂ እንደሆነ ሲገልጹ ይሰማል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ጽሑፎችን ስታዘጋች አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካና ወታደራዊ ባለሙያዎች፣ የፌደራል መንግሥት ስህተት ለአማራ እና አፋር ክልል የጸጥታ ችግር መባባስ አስተዋጾ ማድረጉን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የፌደራል መንግሥት ስህተት መከላከያን ከትግራይ ሲያስወጣ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ አድርጎ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎችን መጠበቅ ሲገባው፣ አዋሳኝ አካባቢዎችን ባለመጠበቁ ችግሩ መከሰቱን እና መስፋፋቱን ይገልጻሉ።
የአማራ ክልል መንግሥት በመጀመሪያ የክተት ዐዋጅ እንዲያውጅ እና በመቀጠልም ጦርነቱ “ሕዝባዊ” እንዲሆን ለክልሉ ሕዝብ ጥሪ ያቀረበው የፌደራል መንግሥት ያደረገው የተናጠል ተኩስ አቁም መክሸፉን ተከትሎ መሆኑ ይገልጻል።
የፌደራሉ መንግሥት ከስምንት ወራት የትግራይ ክልል ቆይታ በኋላ ሰኔ 21/2013 የወሰነው የተናጠል ተኩስ አቁም ብዙ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፣ የተጠበቀውን ውጤት ሳያመጣ ቀርቷል።
የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጁን ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱ ለህወሓት የዝግጅት ጊዜ እንደፈጠረለት የመከላከያ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአማራ ክልል መንግሥት የክተት ዐዋጅ ጥሪ ያስተላለፈው በሽብርተኝንት የተፈረጀውን የህወሓትን ጥቃት ተከትሎ ሲሆን፣ ጥቃቱን ለመመከት የተደራጀ ኃይል እንደሚያስፈልግ በማመኑ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው። የክተት ዐዋጅ ጥሪውን ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር አገኘሁ ተሻገር ሲሆኑ፣ በክተት ዐዋጅ ጥሪያቸውም ላይ “በክልሉ ውስጥ ማንኛውም የመንግሥትን መሣሪያ የታጠቀ፣ የግል መሣሪያ ያለው፣ ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ይክተት” ብለው ነበር።

ሽብርተኛው ህወሓት በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ሕዝቡ ተደራጅቶ እንዲመክት ጥሪ ያስተላለፉት ርዕሰ መሥተዳድሩ፣ አያይዘውም “ከተሠለፈብን ጠላት አኳያ ብዙ ኃይል የምናሰልፍበትና ሎጅስቲክስ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው” ብለዋል።
ምንም እንኳ ክልሉ ያቀረበውን ዐዋጅ ተከትሎ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ልዩ ኃይሎች ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያቀኑ ቢሆንም፣ ህወሓት ከዕለት እለት የማጥቃት ሥራውን በማጠናከር በአፋርና በአማራ ክልል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

ህወሓት፣ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን የተናጠል ተኩስ አቀሙ ባለመቀበሉ፣ በአፋር ክልል ሕጻናትን ጨምሮ 240 ሰዎችን መግደሉን ዩኒሴፍ ገልጿል። በጤና ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው በነበሩ ንጹሐን ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ240 በላይ የሚሆኑት መጨፍጨፋቸውን የገለጸው ዩኒሴፍ፣ ከእነዚህም መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው ብሏል። በክልሉ ከንጹሐን ሰዎች ግድያ በተጨማሪ ህወሓት ለ30 ሺሕ ሰዎች የሚበቃ እርዳታ በከባድ መሣሪያ ማውደሙ መገለጹ የሚታወስ ነው።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ለድህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ወታደራዊ ባለሙያ እንደሚሉት፣ የፌደራል መንግሥት ኃላፊነቱን ወደ አማራ ክልል አሽሽቷል ይላሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት የፌደራል መንግሥት ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ከህወሓት ጋር ሲዋጋ ከቆየ በኋላ ወታደሩን ከትግራይ አስወጥቶ ህወሓት የአማራ ክልል አካባቢዎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም የተናጠል ተኩስ አቁም ላይ ነኝ በማለት በሕዝብ ላይ ጥቃት ሲፈጸም ዝም ማለቱን በማንሳት ነው።

ባለሙያው አክለውም የፌደራል መንግሥት ችግሩን በበላይነት መምራት ሲገባው፣ ከተናጠል ተኩስ አቁም በኋላ እንደገና ያገረሸው ጦርነት በአማራ ክልል ላይ ጫና በማሳደሩ ክልሉ እራሱን ከጥቃት ለመከላከል የክተት አዋጅ ለማወጅ እና አለፍ ሲልም የ“ሕዝባዊ ጦርነት” ጥሪ ለማቅረብ መገደዱን ይገልጻሉ።

ሌላኛው ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕግ ባለሙያ ካፒታል ክብሬ እንደሚሉት ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52 መሠረት ክልሉ፣ የክልሉን የፖሊስ ኃይል በማደራጀት ሠላምና ጸጥታ የማስጠበቅ መብት እንዳለው ገለጸዋል። ይሁን እንጅ አሁን ላይ ያለው ችግር በአንድ ክልል ብቻ የተገደበ ባለመሆኑ፣ ችግሩን በበላይነት መምራት የነበረበት የፌደራል መንግሥት እንደሆነ ጠቁመዋል።

በህወሓትና በፌደራል መንግሥት መካከል የተጀመረው “የሕግ የማስከበር ዕርምጃ” ወደ “ሕዝባዊ ጦርነት” እስከሚሸጋገር ድረስ የፌደራል መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም የሚል ሐሳብ ይነሳል። ይህም ችግሩ በአንድ ክልል ብቻ የተገደበ ባለመሆኑ እንደሆነ የሕግ ባለሙያው ይገልጻሉ። ጸጥታን የማስከበር ኃላፊነት በሕገ-መንግሥቱ ለፌደራል መንግሥትም ለክልል መንግሥታት የተሰጠ ቢሆንም፣ የችግሩ የበላይ መሪ የፌደራል መንግሥት መሆን እንዳለበት ባለሙያው ይመክራሉ።

ከችግሩ ይዘት አንጻር ጦርነቱን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት የፌደራል መንግሥት ነው ወይስ የክልል መንግሥት ነው የሚለው ጉዳይ ወደ ፌደራል መንግሥት ማመዘን ያለበት ቢሆንም፣ የአማራ ክልል መንግሥት የተሰነዘረበትን ጥቃት ለመከላከል የክተት ዐዋጅ ማወጅ እና የ“ሕዝባዊ ጦርነት” ጥሪ ማድረጉ ከሕገ-መንግሥት አንጻር ከፍተት እንደሌለበት ካፒታል ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ሕግ-መንግሥት ድንጋጌ መሠረት የፌደራል መንግሥት እና የክልል መንግሥታት ሥልጣንና ተግባር በግለጽ ተቀምጧል። በሕግ-መንግሥቱ ላይ የፌደራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር የሚደነግገው አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 14 ላይ “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መሥተዳድር ጥያቄ መሠረት የአገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል” ይላል።

የክልል መንግሥትን ሥልጣንና ተግባር የሚደነግገው ደግሞ አንቀጽ 52 ሲሆን፣ በአንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ ኹለት “የክልሉን የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፤ የክልሉን ሠላምና ጸጥታ ያስጠብቃል” ይላል። በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠው የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሥልጣንና ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ከተፈጠረው ችግር ገጽታ አንጻር ጦርነቱን በበላይነት መምራት ያለበት የፌደራል መንግሥት መሆን እንዳለበት የሕግ ባለሙያው ያብራራሉ።

የአማራ ክልል መንግሥት የክትት ዐዋጅ የማወጅ እና የ“ሕዝባዊ ጦርነት” ጥሪ የማድረግ ሕገ- መንግሥታዊ መሠረት ቢኖረውም፣ “ሕዝባዊ ጦርነት” በራሱ ጥሪውን ካስተላለፈው አካል ማብራሪያ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ይገልጻሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት “ሕዝባዊ ጦርነት” ሲባል፣ የተለያየ ትርጓሜ የሚሰጠው በመሆኑ ዝርዝር ማብራሪያ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

“ሕዝባዊ ጦርነት” ሲባል ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን የሚጠቁሙት የሕግ ባለሙያው፣ የአማራ ክልል መንግሥት ለክልሉ ሕዝብ ያቀረበው የ“ሕዝባዊ ጦርነት” ጥሪ “ሕዝባዊ ትብብር ፈጥሮ የጸጥታ ማስከበር ሥራ ለመሥራት ከሆነ ትክክል ነው። ነገር ግን በጸጥታ ኃይል ውስጥ ያልተካተተ ሕዝብን ልክ እንደ ጸጥታ አስከባሪ የጦርነት አካል አድርጎ ማየት ከሆነ ትክክል አይሆንም” ሲሉ ባለሙያው ያብራራሉ።

በመሆኑም የአማራ ክልል መንግሥት ላቀረበው የ“ሕዝባዊ ጦርነት” ጥሪ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት በተጨማሪ “በሕዝባዊ ጦርነት” ስም ስህተቶች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ባለሙያው ጠቁመዋል። “ሕዝባዊ ጦርነት” በዓለም ዐቀፍ ሕግ ጭምር ገደቦች የተቀመጡለት መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፣ በንጹሐን ዜጎች ላይ ለሚደርሱ ችግሮች ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ወታደራዊ ባለሙያው በበኩላቸው “ሕዝባዊ ጦርንት ሲባል ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተባብሮ በተቃራኒ በኩል የቆመውን ጠላቴ ነው ብሎ ያሰበውን አካል ከሚዋጋበት ከወታደራዊ ጦርነት ስልት የተለየ ነው” ይላሉ።
የአማራ ክልል መንግሥት ያቀረበው የ“ሕዝባዊ ጦርነት” ጥሪ በኹለት ተቃራኒ ጎራ በቆሙ አካላት መካከል በሚፈጠር ጦርነት ውስጥ ሕዝብን የጦርነት አካል አድርጎ ማሳተፍ እንዳይሆን ወታደራዊ ባለሙያው ስጋት አላቸው። ይህ እንዳይሆን የፌደራል መንግሥት ጦርነቱን በበላይነት በመምራት ከተቻለ ችግሩን በጸጥታ ኃይሎች ብቻ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ቢችል የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት፣ የአማራ ክልል መንግሥት በህወሓት ጥቃት ሲፈጸምበት፣ የክተት ዐዋጅ አውጆ እራሱን ከህወሓት ጥቃት መከላከል ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ ቢሆንም፣ ችግሩ የአማራ ክልል ብቻ ባለመሆኑ የፌደራል መንግሥት የመሪነት ሚናውን በሚገባ መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል። በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት የጥፋት ዓላማ በአንድ ወይም በኹለት ክልሎች ላይ የተገደበ አለመሆኑ የፌደራል መንግሥት የጦርነቱን መሪነት ሚና እንዲወርስ ከሚደርጉ ጉዳዮች አንዱ መሆኑንም ባለሙያው ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here