ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራትም ጭምር የሥጋ ምርትን ለማቅረብ ያግዛል የተባለውና በ2010 በጀት ዓመት ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ የነበረው የድሬ ዳዋ ዘመናዊ ቄራ ግንባታ በመጪው ሐምሌ 2011 ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
በ1972 የተገነባውንና አሁን ላይ በድሬዳዋና አካባቢው ያለውን የእርድ አገልግሎት ፍላጎት ማሟላት አልቻለም በሚል ዘመናዊ ቄራን መገንባት የጀመረችው ድሬ ዳዋ አዲሱን ቄራ በ2010 ሥራ ለማስጀመር አቅዳ ነበር፡፡ ይሁንና ከዓለም ባንክና ከከተማ አስተዳደሩ በተገኘ 200 ሚሊዮን ብር በጀት ይገነባ የነበረው ቄራ በተባለለት ጊዜ መጠናቀቅ አልቻለም፡፡
ለከተማው ነዋሪ ከሚያቀርበው የሥጋ ምርት ባለፈ ዘመናዊ ቄራው በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የሚስተዋለው የቁም እንስሳት ወጪ ገበያ ላይ እሴት ጨምሮ የሥጋ ምርትን ወደመላክ ለመሻገር ያግዛል የሚል ተስፋ የተጣለበት ነው፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው ያለውን እንስሳትን ወደ ወጪ አገራት በሕገ መንገድ የመላክ ተግባርም ለመከላከል አንድ አማራች ይሆናል በሚል ነበር ግንባታው የተጀመረው፡፡ በዋናነትም ሥጋን ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ገበያ ለመላክ እቅድ አለ፡፡
አሁን ላይ የዘመናዊ ቄራው ግንባታ የሲቪል ምኅንድስና ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ የኤልክትሮ መካኒካል ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን እና በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር የቄራው የተረፈ ምርት ዝግጅትና የገበያ አቅርቦት ኃላፊ አሰበ ኮራነ ገልፀዋል።
ይሁንና የድሬ ዳዋ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ነሐሴ 2009 ላይ ‹‹የሲቪል ሥራው የተጠናቀቀ ሲሆን ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ብቻ ይቀራል፣ ይህንንም በፍጥነት ጨርሶ በ2010 በጀት ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው›› ማለቱ ይታወሳል፡፡
ስለዚህ ጉዳይ አዲስ ማለዳ የጠየቀቻቸው አሰበ የሲቪል ምኅድስና ሥራው ቢጠናቀቅም የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን ለመሥራት ከተማ አስተዳደሩ ያወጣውን ከቀረጥ ነፃ ጨረታ የኢንቨስትመት ቢሮው ፈቃድ በመከልከሉ ለአራት ወራት መዘግየቱን ገልጸዋል፡፡ በነሐሴ 2010 በሱማሌ ክልልና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭትና አለመረጋጋት የተፈናቀሉ ዜጎች ቄራውን ከኹለት ወር ለበለጠ ጊዜ እንዲያርፉበት መደረጉም በወቅቱ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን ለማስራት እንዳላስቻለ አክለዋል፡፡ ይሁንና የፈናቀሉት ዜጎች ተጠለሉበት የተባለው ጊዜ በ2010 መጀመሪያ ላይ ይሰራል ከተባለው የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ ጋር እምብዛም የሚቀራረብ እንዳል ሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
ቄራውን የሲቪል ምኅንድስና ግንባታ የከወነው አደብ ኢንጅነሪግ በውሉ መሠረት በ14 ወራት ግዜ ውስጥ ሰርቶ ማስረከቡንና ወደ ሥራ ሳገባ የዘገየበትን ምክንያት እንደማያውቅ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የነበሩት ችግሮች ተቀርፈው የሙከራ ሥራዎች የተጀመሩ ነው የሚለው የቄራዎቸ ድርጅት በበኩሉ የሚያስፈልጉትን አምስት ዘመናዊ የዕርድ ማሽኖች መግዛቱንና የኤሌክተሪክ መስመር ዝርጋታን በአራት ወር ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አክሏል፡፡ መበደኛ ሥራውን ሐምሌ 2011 ለማስጀመርም እቅድ ተይዟል፡፡
በከተማዋ መውጫ 15 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ፕሮጀክቱ በአካባቢው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ተገቢው ጥናት የተደረገበት መሆኑና የአረንጉዴ ልማት እሳቤን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡
ከሚያጋጥም የኃይል መቆራረጥ ለመዳን 500 ኪሎ ዋት ጀነሬትር መገዛቱን፣ እንዲሁም የውሀ አቅውርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ የጉድጓድ ቁፋሮ መደረጉ ተገጿል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 12 ጥር 25 ቀን 2011